Sunday, 21 March 2021 00:00

በአለማችን ከ1.42 ቢሊዮን በላይ ሰዎች ከፍተኛ የውሃ እጥረት እንዳለባቸው ተነገረ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

     ኦስሎ በውሃ ዋጋ ውድነት ቀዳሚዋ ከተማ ሆናለች

            በመላው አለም የሚገኙ ከ1.42 ቢሊዮን በላይ ሰዎች ከፍተኛና እጅግ ከፍተኛ የንጹህ ውሃ እጥረት ተጠቂዎች እንደሆኑና 20 በመቶ የአለማችን ህጻናት በየዕለቱ የሚያስፈልጋቸውን በቂ ውሃ እንደማያገኙ ተመድ አስታወቀ፡፡
የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ ከትናንት በስቲያ ባወጣው ሪፖርት እንዳለው፣ በመላው አለም በሚገኙ ከ80 በላይ አገራት ህጻናት የከፍተኛ ወይም እጅግ ከፍተኛ የውሃ እጥረት ተጋላጭ ሲሆኑ፣ በምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ አገራት ከሚገኙ ህጻናት መካከል ከ58 በመቶ በላይ የሚሆኑት በየዕለቱ የሚያስፈልጋቸውን ውሃ ለማግኘት እጅግ አዳጋች የሆነባቸው ናቸው፡፡
በሌላ ውሃ ነክ ዜና ደግሞ፣ በመላው አለም ከሚገኙ ከተሞች መካከል የውሃ ዋጋ እጅግ ከፍተኛ የሆነባት ቀዳሚዋ ከተማ ኦስሎ መሆኗንና፣ በከተማዋ አንድ ጠርሙስ የታሸገ ውሃ በአማካይ 1.85 ዶላር እንደሚሸጥ ተነግሯል፡፡
ሆሊዱ የተባለው ኩባንያ በ150 የአለማችን ከተሞች የሰራውን ጥናት መሰረት አድርጎ ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው አለማቀፍ ሪፖርት እንዳለው፣ ቨርጂኒያ ቢች በ1.59 ዶላር፣ ሎሳንጀለስ በ1.54 ዶላር፣ ኒው ኦርሊያንስ በ1.48 ዶላር፣ እንዲሁም ስቶክሆልም በ1.47 ዶላር በመሸጥ እስከ አምስተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡
ውሃን እጅግ ዝቅተኛ በሆነ ዋጋ በመሸጥ በአንደኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠቺው ደግሞ አንድ ጠርሙስ የታሸገ ውሃ በ0.04 ዶላር የሚሸጥባት ቤሩት ስትሆን፣ የህንዷ ባንጋሎር በ0.13 ዶላር፣ የጋናዋ አክራ በ0.16 ዶላር፣ የናይጀሪያዋ ሌጎስ በ0.17 ዶላር፣ የቱርኳ ኢስታምቡል በ0.18 ዶላር በመሸጥ እስከ 5ኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውን ሪፖርቱ ያሳያል፡፡


Read 4404 times