Print this page
Saturday, 27 March 2021 12:10

“ቅርጫ በሆነ ምርጫ ውስጥ መሳተፍ አንፈልግም” - ፕ/ር መረራ ጉዲና

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(3 votes)

  የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) በ6ኛው አገራዊ ምርጫ እንዲሳተፍ ተደጋጋሚ ጥሪ ቢቀርብለትም ፍቃደኛ ሳይሆን መቅረቱን ጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ መግለፃቸውን ተከትሎ፤ የፓርቲው ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በሰጡት አስተያየት፤ ቅርጫ በሆነ ምርጫ ውስጥ መሳተፍ አንፈልግም  ብለዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጪውን ምርጫ አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ በመጪው ምርጫ ላይ ለመወዳደር ፈልገው ዝግጅትም እያላቸው የሚወጡ ፓርቲዎችን መንግስት  ከግማሽ መንገድ በላይ ሄዶ ማነጋገሩን ገልፀው “እኛ እናግዛችኋለን ከውድድሩ አትውጡ” ብለን በሽማግሌ ሁሉ አስጠይቀናቸዋል ብለዋል፡፡ እኔ ራሴ ኦፌኮ ከምርጫው ውድድር እንዳይወጣ፣ መታገዝ የሚገባውን ሁሉ ለማገዝ ዝግጁ መሆናችንን ገልጬ ጠይቄአቸዋለሁ፤እነሱ ግን ፈቃደኛ አልሆኑም ብለዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩን የእናግዛችሁና ተወዳደሩ ጥሪ ኦፌኮ ለምን መቀበል እንዳልፈለገ የፓርቲውን ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ጠይቀናቸው በሰጡት ምላሽ፤ “እኛ በምርጫው እንዳንወዳር ፍላጎት ያለው መንግስት ነው፤” በምርጫው ለመወዳደር የሚያስችሉን አምስት መሰረታዊ ጥያቄዎች አቅርበናል፤ ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ እስካላገኘን ድረስ በምርጫው አንወዳደርም ብለዋል፡፡
ፕሮፌሰሩ በምክንያት ካቀረቧቸው ጥያቄዎቻቸው መካከል ዋነኛው በእስር ላይ ያሉት የፓርቲው አመራሮች እንዲፈቱ የሚጠይቀው ሲሆን በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙና በመንግስት የተዘጉብን ከ200 በላይ ቢሮዎቻችን እንዲከፈቱልን፣ የጠበበው የፖለቲካ ምህዳር እንዲሰፋና የብሔራዊ መግባባት ውይይት እንዲካሄድ የሚሉት ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ባልተሟሉበትና ጥያቄዎቻችን ምላሽ ባላገኙበት ሁኔታ ወደ ምርጫው መግባት አንፈልግም ብላዋል፡፡
መንግስት ምርጫውን ከቀደሙት ምርጫዎች የተሻለ እንዲሆንና  ዘላቂ ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ከፈለገ ለጥያቄዎቻችን ተገቢ ምላሽ በመስጠት ወደ ምርጫ ውድድሩ እንድንገባ ሊያደርግ ይገባል ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ ይህንን ግን መንግስትና ፣ምርጫ ቦርድ ሊቀበሉት አይፈልጉም፤ እኛ ደግሞ ቅርጫ በሆነ ምርጫ ውስጥ ለመግባት አንፈልግም ብለዋል፡፡

Read 12890 times