Monday, 29 March 2021 00:00

“ሊቁ ጎጋቶ” መፅሀፍ ተመረቀ

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(0 votes)

   በተወለዱበት አካባቢ ከመጀመሪያዎቹ 12 የሚኒስትሪ 6ኛ ክፍል ተፈታኞች አንዱ የሆኑት፣ በፅናት ተምረው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በፔዳኮጂካል ሳይንስ መጀመሪያ ዲግሪያቸውን  የያዙትና በሀዋሳና በጂማ የመምህራን ማሰልጠኛ የተማሪዎች ዲንና መምህር እንዲሁም ምክትል አስተዳደሪ፣ ዋና አስተዳዳሪና መምህር በመሆን ለ16 ዓመታት ያገለገሉት የመምህር መለሰ ወልደሚካኤል  ሳዳሞ “ሊቁ ጎጋቶ” ታሪካዊ ልቦለድ መጽሐፍ ለምርቃት በቃ።
እኚሁ መምህር በተወለዱበት ጉራጌ ዞን ምሁር አካባቢ ጨዛ ሰፈር የመጀመሪያው ትምህርት ቤት ሲመሰረት ከቤተክርስቲኒቱ ሊቅነትና የግብረገብ መምህርነት በተጨማሪ ሁሉንም ዘመናዊ የትምህርት አይነቶች በማስተማር ፋና ወጊ ስለሆኑት አለቃ ገብረስላሴ ህይወት፣ አገልግሎትና የህይወት ጉዞ የሚተነትነውን “ሊቁ ጎጋቶ” የተሰኘውን መጽሀፍ በመጻፍ ስነ-ጽሁፍ ችሎታቸውን አስመስክረዋል።
እኚሁ እውቅ መምህር የአለቃ ገ/ስላሴን ታሪክ አስታከው የጉራጌን ባህል የህዝቡን ስነ-ልቦና፣ ቋንቋ፣ ወግና ሁለንተናዊ ማንነት በመጽሀፋቸው አብራርተዋል። መምህር መለሰ ወልደ ሚካኤል ከዚህ መፅሀፋቸው ቀደም ብሎ በ1994 ዓ.ም የታተመና በፌደራል ደረጃ ለት/ቤቶች የተከፋፈለ “የጥናት ዘዴ”  የተሰኘ አስተማሪ መጽሐፍ ፣ ከሶስት የጉራጌ ምሁራን ጋር በመሆን የታተመ የጉራጊኛ አማርኛ እንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት መፅሐፍ በማዘጋጀት ለማህበረሰባቸው ባህልና ቋንቋ እድገት ጉልህ ሚና የተጫወቱ ሲሆን፣ በተለያዩ መፅሄቶችና ጋዜጦች ላይ መጣጥፎችን፣ ግጥሞችንና አስተማሪ ሀሳቦችን በመጻፍ ትልቅ ሀገራዊ ሚና ሲጫወቱ ቆይተዋል።
 እኚሁ ምሁር በወልቂጤ ከተማ አስተዳደር የወልቂጤ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ (በአሁኑ አበሩስ) ት/ቤት ዳይሬክተር፣ ከመዋዕለ ህፃናት እስ ሁለተኛ ደረጃ ያሉ ትምህርት ቤቶች ትምህርት ጥራት ተቆጣጣሪና በወልቂጤ ከተማ አስተዳደር የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ሱፐር ቫዘር በመሆን ያገለገሉ ሲሆን በአሁን ሰዓት በጡረታ ቢገለሉም የአንድ የትራንስፖርት ድርጅት ስራ አስኪያጅ በመሆን እያገለገሉ ይገናሉ። “ሊቁ ጎጋቶ” መፅሐፋቸው በ196 ገፅ ተቀንብቦ በ100 ብር ለገበያ ቀርቧል።

Read 9000 times