Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 18 August 2012 13:15

ፆምና የጨጓራ ህመም

Written by 
Rate this item
(10 votes)

የጨጓራ በሽታ አንድ አይነት ብቻ ባለመሆኑ የትኛው ዓይነት በሽታ እንደሆነ ለማወቅ ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህም ህመምተኛው ችግሩ ያለበት በምግብ መዋጫ ቱቦው፣ በትንሹ አንጀቱ፣ ወይም በጨጓራው ውስጥ መሆኑን ለመለየት ያስችላል፡፡ ህክምናውም ምርመራ በተደረገለትና ችግሩ ተለይቶ በታወቀ በሽታ ላይ በመሆኑ ውጤታማ ይሆናል፡፡ በግምታዊ ህክምና የሚታዘዙ መድኃኒቶች እጅግ አደገኛ የሆኑ ችግሮችን ያስከትላሉ፡፡ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የፆመ ፍልሰታ፣ በእስልምና እምነት ተከታዮች ደግሞ የታላቁ ረመዳን ወር ፆም ከተያዘ ሰንበትበት ብሏል፡፡የሁለቱም እምነት ተከታዮች እንደየእምነታቸው ህግና ትእዛዛት ፆሙን ተያይዘውታል፡፡ በዚህ የፆም ወቅትም ጿሚዎቹ ከምግብና ከመጠጥ (ከውሃ) ታቅበው ረዘም ያለ ሰዓታትን ያሳልፋሉ፡፡ ይህ ሁኔታም የጨጓራ ህመማቸውን የሚያባብስባቸው እንደሆነና ለጨጓራ ህመምም እንደሚዳርጋቸው አንዳንዶች ይናገራሉ፡፡

ፆም (ምግብ በወቅቱ አለመመገብ) ሁሉንም ዓይነት የጨጓራ ህመሞች ለማባባስ ይችላል?  ለጨጓራ ህመምስ መንስኤ ሊሆን ይችላል? ለሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ፈለግንና መረጃዎችን ማገላበጥ ጀመርን፡፡ በጨጓራ ህመም ዙሪያ ከተደረጉ ጥናቶች ያገኘናቸውን መረጃዎችንና የጤና ባለሙያዎች ስለ ጉዳዩ ያሉትን ይዘን እነሆ ቀረብን፡፡

የጨጓራ በሽታ የምንለው የምግብ መዋጫ ቱቦንና የትንሹ አንጀት መግቢያን ለህመም የሚዳርግ በሽታ ነው፡፡ የተለያዩ አይነቶች የጨጓራ ህመሞች አሉ ከእነዚህ መካከል የጨጓራ መቆጣት (ጋስተራይትስ) የጨጓራ መላጥ (አልሰር) እና የጨጓራ ካንሰር ይጠቀሳሉ፡፡ ለጨጓራ በሽታ መንስኤ ከሆኑ ነገሮች መካከል ዋንኛው የባክቴሪያ ኢንፌክሽን ነው፡፡ ይህም ሔሊካባክተር ፓይሎሪ ተብሎ በሚጠራው ባክቴሪያ አማካኝነት የሚከሰት ነው፡፡ ይህ ባክቴሪያ የሚተላለፈው በምግብና በመጠጥ ውሃ ነው፡፡

በምግብና በውሃ አማካኝነት ወደ ሰውነታችን ውስጥ የገባው ባክቴሪያ የጨጓራን የመከላከል አቅም አልፎ ወደ ጨጓራችን ውስጥ በመግባት ይባዛል፡፡ ከዚህ በኋላ የጨጓራን ህመም ያስከትላል፡፡

የጨጓራ በሽታ በተለይ በቂና ንፁህ የመጠጥ ውሃ እንደልብ በማይገኝባቸው ታዳጊ አገራት ችግሩ የጐላ ነው፡፡

90 በመቶ የሚሆነው የታዳጊ አገር ህዝቦች የዚህ ባክቴሪያ ተሸካሚ ናቸው፡፡ ሁለተኛው የጨጓራ በሽታ መንስኤ በሰውነታችን ውስጥ የሚገኘው አሲድ መጨመር ነው፡፡ ይህ ሁኔታም ሊከሰት የሚችለው ለተለያዩ በሽታዎች ማስታገሻነት የምንወስዳቸው መድሃኒቶች የአሲድ መጠኑን ከፍ ሲያደርጉት ነው፡፡

ለዚህም አስፕሪንን እንደምሳሌ ማንሳት እንችላለን፡፡

በአገራችን ከጨጓራ መላጥ ይልቅ የትንሹ አንጀት መላጥ ችግር ልቆ የሚገኝ ሲሆን ወንዶች ከሴቶች ይልቅ በበሽታው የመያዝ ዕድላቸው በሁለት እጥፍ ከፍ ያለ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የደም አይነታቸው ኦ የሆነ ሰዎች በጨጓራ በሽታ የመያዝ እድላቸው ከፍ ያለ መሆኑን የሚጠቁሙት መረጃዎች እነዚህ ሰዎች በተጥሮአቸው የደም አይነታቸው ኦ ካልሆነ ሰዎች ይልቅ ከፍ ያለ አሲድ የማመንጨት ባህርይ አላቸው፡፡ ይህ አሲድ ከጨጓራ የመከላከል አቅም በላይ በሚሆንበት ወቅት ጨጓራና አንጀት ላይ የመላጥ ችግርን ሊያስከትል እንደሚችል ይገልፃሉ፡፡

የጨጓራና የአንጀት መላጥ በሽታዎች ምልክት ሊኖራቸውም ላይኖራቸውም ይችላል፡፡ ይህ ችግር ካለባቸው ሰዎች መካከል 30% የሚሆኑት ምንም አይነት ምልክቶችን የማያሳዩ ሲሆን 70% የሚሆኑት ግን ከእምብርት በላይ የማቃጠል፣ የማግሳት፣ የማቅለሽለሽና የማስመለስ፣ የምግብ አለመስማማትና የቃር ስሜት ምልክቶችን ሊያሳዩ ይችላሉ፡፡

የጨጓራ መላጥና የአንጀት መላጥ በሽታዎች በጊዜውና በወቅቱ ታውቀው ህክምና ካልተደረገላቸው የአንጀት መበሳትን ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡ መላጡ የደም ስርን ካገኘ ደግሞ ደም ሊደማና የከፋ አደጋ ሊያስከትል ይችላል፡፡ ተገቢ ህክምና ሳያገኝ የቀረው የጨጓራ መላጥ በሽታ ከዚህ በተጨማሪ ሲላጥ ሲድን ተመልሶ ሲላጥ ሲድን ይቆይና ጠባሳ ይፈጥራል፡፡ ይህ ጠባሳ ደግሞ ከጨጓራ ወደ አንጀት ምግብ የሚያስተላልፈውን ቱቦ በመዝጋት ምግብ ጨርሶ እንዳይደርስ ሊያደርገው ይችላል ያስመልሰዋል፣ የአፍ ጠረንን ይቀይራል ቀስ እያለም ጨጓራው ሊበሳ ይችላል፡፡

በዚህ ምክንያትም ጨጓራ ውስጥ ያለ አሲድ ወደ ሆድ እቃ ይሰራጭና ሰውየውን ሊገድለው ይችላል፡፡ ይህ ሁኔታ በአገራችን በተለይም በገጠሪቱ የአገሪቱ አካባቢዎች በስፋት ይታያል፡፡

የጨጓራ በሽታ አንድ አይነት ብቻ ባለመሆኑ የትኛው ዓይነት በሽታ እንደሆነ ለማወቅ ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ይህም ህመምተኛው ችግሩ ያለበት በምግብ መዋጫ ቱቦው፣ በትንሹ አንጀቱ፣ ወይም በጨጓራው ውስጥ መሆኑን ለመለየት ያስችላል፡፡ ህክምናውም ምርመራ በተደረገለትና ችግሩ ተለይቶ በታወቀ በሽታ ላይ በመሆኑ ውጤታማ ይሆናል፡፡ በግምታዊ ህክምና የሚታዘዙ መድኃኒቶች እጅግ አደገኛ የሆኑ ችግሮችን ያስከትላሉ፡፡

ፆም፣ ንዴት፣ ብስጭት፣ የሥራ ብዛት፣ ቅመም የበዛባቸውን ምግቦች መመገብ ለጨጓራ ወይንም ለአንጀት መላጥ በሽታዎች ምክንያት ወይንም መነሻ ሊሆኑ ባይችሉም ችግሩን ሊያባብሱት ይችላሉ፡፡

ለዚህ ለዛሬው ፀሐፌ መነሻ ወደ ሆነኝና ፆም (ምግብ በወቅቱ አለመመገብ) የጨጓራ በሽታን ሊያባብስ ይችላል ወደሚለው ጉዳይ እንመለስ፡፡ በዩኒቨርሳል ከፍተኛ ክሊኒክ ቴዎድሮስ ቅርንጫፍ ሜዲካል ዳይሬክተርና ሐኪም የሆኑት ዶ/ር ምክሩ ታረቀኝ ይህንኑ ጉዳይ አስመልክቶ በአንድ ወቅት የሰጡን ማብራሪያ ነበር፡፡ ዶ/ር ምክረ እንደሚሉት ዲአዲን አልሰር የተባለውን የጨጓራ በሽታ ፆም ወይንም (ምግብ አለመመገብ) ሕመሙን ሊያባብሰው ይችላል፡፡ የዚህ በሽታ ተጠቂ የሆኑ ሰዎች ምግብ ሳይመገቡ ሲቀሩ የህመም ስሜት የሚባባስባቸው ሲሆን ምግብ ሲመገቡ ግን የህመም ስሜቱ ይጠፋል፡፡ ጋስተሪክ አልሰር የተባለው የጨጓራ በሽታ ችግር ግን ህመምተኛው ምግብ ሳይመገብ ሲቀር የህመም ስሜቱ የማይኖር ሲሆን ምግብ በሚመገብበት ጊዜ ግን የህመም ስሜቱ ይቀሰቀስበታል፡፡ የጨጓራ ህመምተኛ የሆነው ሰው እንደበሽታው አይነት ምግብ መመገቡ ወይም አለመመገቡ ችግሩን ሊያባብሱበት ስለሚችሉ እነዚህን ነገሮች በአግባቡ ማጥናትና ለበሽታው ህክምና ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

በፆም ወቅት በአብዛኛው ከቅባት ምግቦች የመቆጠብ ሁኔታ ይታያል፡፡ የጨጓራ ህመም ችግር ያለባቸው ሰዎች ቅባት የበዛባቸውን ምግቦች በሚመገቡበት ጊዜ ህመሙ እንዲባባስባቸው ስለሚያደርግ የፆም ወቅት እነዚህ ሕመምተኞች የተሻለ ጤንነት የሚሰማቸው ጊዜ ይሆናል፡፡

ሆኖም ፆም ለጨጓራ በሽታ መንስኤ ምክንያት ሊሆኑ ይችላል የሚል መረጃዎች የሉም፡፡ እንደውም ለረዥም ጊዜያት ያለዕረፍት ሲሠራ የቆየውን ጨጓራና አንጀት ጥቂት እረፍት መስጠት ይሆናል፡፡ በፆም ሰበብ ለጨጓራችን ጥቂት እረፍት እየሰጠን ረዘም ላለ ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጠን ካላደረግን በስተቀር ጨጓራችን ተቆጥቶ ያኮርፋል፡፡ ጨጓራችንን ካስኮረፍነው ደግሞ ቅጣቱ ከባድ ነውና ፆም ጥሩ መፍትሔ ይመስለናል፡፡

መልካም የፆም ወቅት ለሁለቱም እምነት ተከታዮች እየተመኘሁ ጽሑፌን በዚሁ ቋጨሁ፡፡

 

 

 

Read 23244 times Last modified on Saturday, 18 August 2012 13:20