Saturday, 27 March 2021 13:35

"በባዶ አንጀት"

Written by  ሳሙኤል በለጠ(ባማ)
Rate this item
(10 votes)

   “ሳቅ አምርሬ እጠላለሁ፣ ሳቅ ጨለምተኞች ሊበሉት ያሰጡት የማይደርቅ ፍርፋሪ ነው። ሳቅ ከጥርስ አልፎ ሲንጠባጠብ ገላዬን አጣጥቦት የሚወስደው ይመስለኛል። ፍቅረኛዬ ስትለየኝ (ምናልባት) ሰዎች ከንፈራቸውን ከፍ ዝቅ እያደረጉ ከት ብለው ይስቃሉ፡፡ ግጥም ስገጥም ነብሳቸው ከአካላቸው የወለቀባቸው በግጥሜ ይስቃሉ፤ ሞት ትቢያ ሲያስግጠኝ መልአከ ሞት ሽንቱን ጥቁር ሱሪው ላይ እስቲለቀው ድረስ ይስቃል። ስለዚህ ሳቅ እጠላለሁ”
“አየህ ፍሬዘር፤ እኔ ማየት አልችልም ፤እንኳንም ዐላየሁ; አለ በሸካራ እጁ አጥብቆ በያዘው “White Cane” መሬቱን እየጫረ፣ ጥቁር መነጽር ዐይኑ ላይ ደፍቶ፣ ሽቅብ ወደማያየው ሰማይ አንጋጦ”
ዐይነ ቆሎ ዐይን ያላት መልኳን እንደ ነገሩ እግዜር በፍጽምና ጣቱ ያላቆጠው፣ ግን የደስደስ ያላት ልጅ፣ ጀበና በአንድ እጇ ይዛ ሁለት ፍሬ እጣን በጣቶቿ አፅቆች መሃል አጣብቃ፣ እኛ ወደተቀመጥንበት መጣች ፤እሷ ስትመጣ የቀጣጠልነው ጭውውት ተበጠሰ፤ ልጅቷ ቡናውን አንቆርቁራ ቀድታልን፣ እጣኑን አጫጭሳልን ሄደች፡፡
“ስለ ሴት ልጅ ምን ታስባለህ?”
“ስለ እኛ ዘመን ሴት?”
“አዎ”
“ግማሽ ወንድ ናቸው።”
ፈገግ አለ፡፡
መኮ ጠረጴዛው ላይ የተቀመጠውን የቡና ስኒ ለመጨበጥ ይዳስሳል።
ልናገር ስል ንግግሬን ሰንጥቆ በመሃል ገባ።
"ምነው ባልተፈጠርኩ ብለህ አታውቅም?!"
“አቃለሁ”
“ይሄ’ኮ የመጣው በሴት ሰበብ ነው።”
“እሱስ?”
"አልፈርድበትም፤ መኮ ዐያይም፤ አሁን እራሱ ፍቅረኛውን ቀጥሯት እየተጠባበቀ ነው። ሴት አምርሮ ይጠላል፤ እስከ አስራ አራት አመቱ ድረስ ሴት በዐይኑ በብረቱ አይቷል። ሴቶች ለሱ እንደ ተደፋ እጣቢ ናቸው። የተዋወቅነውም ከሰባት አመት በፊት ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሆነን ነው።
“እነዚህማ?!”
"እነማን?"
“ሴቶችን!”
“መርገጥ ነበር!”
“መርገጥ?”
“አዎ”
“ቆይ ሴቶችን እንዴት ጠላ? በጠረናቸው? በሳቃቸው? ወይስ በድምጻቸው?”
ፒያሳ ከኦስሎ ትንሽ ከፍ ብሎ የተሰየምንበት ሜሪ የጀበና ቡና፣ ቀስ በቀስ ሰው እየበዛበት መጣ፡፡
“በቃ አልመጣችም እንሂድ”
"አንደዜ አደውልላትም!?"
“ቆይ”
ስልኩን አወጣ፤ከእጅ ስልኩ የምትንተፋተፍ ድምጽ ይሰማል፤ ስልኳ ዝግ ነው።
 "እሺ በቃ እንሂድ፤"
መጽሐፌን በጣቴና በመዳፌ አጣብቄ ያዝኩ፤ እጄን ለመደገፍ እየተጠጋ "ነግሬሃለሁኮ፤ ሴቶች የቅርብ እሩቅ ናቸው።"
“እና ለምን ቀጥረህ ትጠብቃለህ?”
“እኔጃ”
ምንም መልስ አልሰጠሁትም ፤ለእኔጃ መልስ አይሰጥም፡፡
ከፒያሳ ወደ ሜክሲኮ በታክሲ ተጓዝን፤ በእግራችን እስከ አረቄ ፋብሪካ ሄድን፤ ከአረቄ ፋብሪካ ቤቱ ብዙ አይርቅም፤ ፀሐይ ውሏን ስታ ፍጥረትን ሁሉ ትታ እኔን እኔን የምትደበድበኝ እስኪመስለኝ ድረስ ሁለመናዬን አቃጠለችው፡፡
"ቲማቲም እንግዛና ቲማቲም ለብለብ እንስራ አይደል?"
"ሰነፍ"
"ማን እኔ?
"አንተም ትውልዱም"
“ከኑግ ጋራ የተገኘሽ መጭ አብረሽ ተወቀጭ ማለት ይሄኔ ነው። ለምን?”
“የምትበሉት ሳይርባችሁ ነው” ምናምን እያለ ሲፈላሰፍ፣ እኔ ቲማቲሜን አስመዘንኩ፤ ውስጥውስጡን ቅያስ በበዛበት መንገድ ጥቂት ተጉዘን ከቤቱ ደረስን፡፡
“ግቢ ማን አለ አንተዬ፤ ሶስት ወሬ’ኮ ቤቴ ከመጣሁ?”
“ማንም፤ ሁለት ሰው ብቻ”
“እድሞውን ስንከፍት የሰሙ አከራይ”
“መኮ መጣህ?”
“አዎ”
“እንካ ይህንን”
“ምንድነው እሱ?”
“ወረቀት”
“ማነው የሰጥዎት?” ከገጻቸው አፈር ብለው ዝም አሉ
“መቼ ነው የተቀመጠልኝ?”
“አንድ ሁለት ወር ሆነው”
ነጠቅ ነጠቅ እያሉ ወደ ግራ ወደ ቀኝ እየተገላመጡ፣ ወደ ቤታቸው ጠለቁ፤ እንደ ጀምበር ምድነው እስቲ እንካ ብሎ ሰጠኝ”
“ጽሑፍ ነው”
“አንብበው”
“መኮ የኔ ውድ የኔ መሪ እኔ ባይም እኔ አንተን መምራት ሲገባኝ አንተ ነበርክ እኔን የምትመራኝ ነፍሴ በነፍስህ ውስጥ አለች ግን ምን ያረጋል?”
“ብቻ ነው?
“አይ”
ትንሽ ደብዘዝ ብሎ ወደጥግ በኩል። መኩ የገዛሁልህን “White Cane” ከክቤ ምግቤት ውሰድ እዛ አስቀምጬልሃለሁ
ቻው ደህና ሁን!
አንብቤለት ስጨርስ መኮ እየተደናበረ  እድሞውን ከፍቶ ሄደ የገዛሁትን ቲማቲም ትርክዛው ላይ አስቀምጬ ብከተለውም ወዲያው ተሰውሯል። የትዝታዋ ሳቅ አፍኖ እንዳይገድለው ብዬ ሰጋሁ የስንብትን ምስል ቆሞ ማየት ልብ ያንሸራትታል። ምን ይሰማው ይሆን? የት ሄዶ ይሆን? በሰፈሩ ውስጥ ትንሽ በእግሬ ተላውሼ  ወደ አስፖልት ብቅ አልኹ ታክሲዎች ፊትለፊት ቃልቲን እያዩ ሽው ሽው ይላሉ።
አንዱን አስቁሜ ወደ ሜክሲኮ ሄድኹ ጭንቅ ጭንቅንቅ ብሎኛል። ጠርዝ ያልያስኳቸው ብዙ ሃሳቦች ይመላለሱብኛል። ሜክሲኮ ወርጄ ወደ የት አቅጣጫ እንደምሄድ ግራ ተጋባሁ ተፈጥሮ ትስቅበት ይሆን? ወይ የራሱን ዓለም ስሎ እዛው ቁጭ ብሎ ግጥም እየጻፈ ይሆናል። ሰው በተጨናነቀመት መንገድ መሀል ቀስ እያልኩ ተራምጄ ዓይኔ ወዳረፈበት ካፌ ገባሁ ርጭ ያለ ካፌ ነው። እስከምቀመጥ የተከተለኝ ክላሲካል። ድንገት ነፍሴን ይቧጥጠኛል። ክላኪካሉ ከግጥሙ ጋራ ሲቀላቀል። ሆዴ ተላወሰ ባለቅስ ደስ ይለኝ ነበር ግን...
“ሰው የሰው ሕመም ‘ሚያመው። ራሱን በዛ መስታወት ስለሚያይ ነው።” ለካ እኔም በመርሳት ቅጽበት ጫፍ ላይ ተደግፌ ስለምኖር እንጂ ከልብ የተጣበቀ ልብ ከልብ ሲገነጠል። የሚፈጥረውን ሰቆቃ በደንብ አውቀዋለሁ የመኩ ሴት ትሻላለች ቢያንስ ደብዳቤ ጽፉለታለች ልቡን ቆርጣለታለች የኔዋ ዝም ብላ ነው። የሄደችው እንዲህ እንዲህ እያልኩ ተጨንቄ በሃዘን ናዳ ተጨፍልቄ ያዘዝኹትን ማኪያቶ አጋምሼ ጀምበር ቁልቁል መውረድ ስትጀምር ፀሐይ ደማቅ የብርሃን ነጸብራቋ ሲደበዝዝ። በተስፋ እግር በባዶ አንጀት ወደ ቤቴ መራመዴን ቀጠልኹ
ሺሺሺሺሺ! እንደንፈስ ንፈስ መሰል መንፈስ
አ-አ-አፈልጋትም?
“ማንን?”
“ስታፈቅራት ስታፈቅርህ የኖረችውን”
“ማነህ? ማነሽ?”
“ስገላመጥ ከጥቂት መንገደኞ በቀር በቦታው ማንም አልነበረም መንፈሷ መንፈስ ለብሶ ይሆን? በንዴት ምንም ነገር ሳልቀምስ ሆዴን በእጄ ጨብጬ ተኛሁ”
(ሌት በምንጣፌ ላይ ነፍሴ የወደደችውን ፈለግኹት ፈለግኹት አላገኘኹትም መሓልየ መሓልየ ዘሰሎሞን 3፥1)
“ቀን ከሌት እየተቀላቀለ ጥቂት ቀኖች አለፉ አንድ ዕለት ማለዳ ላይ ስልኬ ጥዝዝዝ! ብሎ ከሰመመኔ አባነነኝ እየተጨናቦስኹ”
“ሄሎ”
“መኮ ነኝ ልቤ ስንጥቅ ነበር ያለው”
“እያለህ ነው የምታስጨንቀኝ? የት ነህ”
“የኑሮ መጀመሪያ”
“የት ነው?”
“ቦታ አይደለም ስሜት ነው። መርሳት ነው!”
“በል ለማንኛውም ከሰዓት ደብረ ብርሃን እንሄዳለን ነገ ፈተና አለኝ ያው አንተ ነህ የምታነብልኝ”
“እሺ”
“እሺ”
9:00....
“ላምበረት ተገናኘን የፊቱ ገጽ ሌላ ጥቁር ገጽ ሰርቷል። ትንሽ ተስፋ ትንሽ መውደቅ ይታይበታል በደንብ ሰላም ሳንባባል። ወደ መኪናው ገባን ርጭታ በሁለታችንም መንፈስ ላይ ሰፎ ነበር እሱን ሳይ ሃያት ትዝ ትለኛለች ሃያትን ሳስታውስ የኔዋ ማህሌት ውል ትልብኛለች እንደምንም ደብረ ብርሃን ደረስን አልጋ ያዝን ሊመሻሽ ሲል”
“እኔምለው አንድ ሁለት እንበላ?”
“ከመሸ መውጣት አልወድም!”
“እኔ ልውጣ”
“ተጠንቀቅ ከወዳጅ”
“እሺ”
“ደብረ ብርሃን በምሽት ስትታይ በነ ራስ አበበ አረጋይ ስጋ ውስጥ ያለች ነፍስ አትመስልም የካምፖስ ተማሪ ሆኜ ከአንዴም ሁለቴ የሄድኹበት አረቄ ቤት አለ እዛ ብሄድ ሳይሻል አይቀርም ብዬ ከራሴ ጋራ ተማክሬ ወደ አረቄ ቤቱ እግሬን ጉተትኹ እንደደረኩ ምን ነገረኝ የሲጋራ ሸታ፣ከበራፍ የተጣለ ገረባ፣ ከመጥፎ ጠረን ጋራ ወደአፍንጫ የሚመጣ የሰንደል ሽታ፣ ደጃፋቸውን ተደግፈው የቆሙ ሴቶች፣ የተራበ ዐይን፣ የተከፈተን ጉረሮ ለመዝጋት የተከፈተ ጭን፣ እኒህ ሁሉ እንደደረስኩ የሚጠቁሙኝ አቅጣጫ ጠቋሚዎቼ ናቸው። የጨረጨሰ ሰፈር ነው። አረቄ ቤቷ ውስጥ ገብቼ ተቀመጥኹ አረቄዬን ቅዉ እየሰጠኹ ወግ ሲጠርቁ መስማቴን ቀጠልኹ ትንሽ ቆየት ብሎ በሰፈሩ ሁከት ተፈጠረ ምንድነው? ምድነው? እያለች ወጣች የቤቱ ኮማሪት ተከትያት ወጣሁ “ትመልስልኝ በደም ፍላት አንዲት ልጅ ደምታ እድንክ ላይ ተቀምጣለች”
“አምሳ ብሬን ትመልስ ይላል። በሞቅታ”
“ሆሆይ ሰክሮኮ ነው። ልጅቷን ደበደባት ምስኪን ለራሷ ምንም የሌላት ድሃ አይ የእንጀራ ነገር እያሉ ሁሉም ከንፈራቸውን ይመጣሉ በሉ ወደየቤታችሁ ግርግር አትፍጠሩ አሉ አንድ የእድሜ ባለጸጋ ሴትዮ ጉድ ጉድ እያሉ ሁሉም ከቤት ወጡ”
“መጨረሻ ላይ ማህሌት ጠቆር ያለ ሻሽ አስራ ስትወጣ አየዃት ጭል ጭል በሚለው መብራት መሀል ዐይን ለዐይን ተያየን ማሂ እዚህ ምን ትሰሪያለሽ? ለምን መጣሽ? ዝም አለች ጠላልፎ ያሰረኝ ዘላለማዊ የሕመሜ ክር በዚህች ቅጽበት የሚበጣጠስ መስሎኝ ቀርቤ ላቅፋት ስጠጋ ሸሸችኝ”

Read 2276 times