Saturday, 27 March 2021 13:41

"የድንቁርና ጌቶች" - የሀገር ድህነት ሰበቦች

Written by  ከእሱባለው ካሳ
Rate this item
(0 votes)

"--የሦስት አስርት ዓመታት ተቋማትን አጥፍቶ የመጥፋት ስልትና ደባ ሰለባ ነበር ያለውን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መነሻ አድርጎ የዩኒቨርሲቲውን ማኅበረሰብ መንፈስ በፍራቻ፣ በጥላቻ፣ በንቀት፣ በባይተዋርነትና በስግብግብነት የመረዘበትን መንገድ ያሳያል፤ ይለናል--"
            
              ብርሃኑ ደቦጭ የታሪክ ባለሙያነቱን ያህል፣በመጽሐፍ ሂስ ስራዎቹ የሚታወቅ ሰው ነው፡፡ በርካታ መጻሕፍትን ገምግሞ አስነብቦናል፡፡ አሁን ደግሞ የሚገመገምበት ሥራ ይዞ ብቅ ብሏል፡፡ አነጋጋሪው የብርሃኑ ደቦጭ መጽሐፍ፤ ወዳጅም ጠላትም አፍርቷል፡፡ የመጽሐፉ ወዳጆች፤ እንዲህ ያለውን ነውር ትውልድ ካልሰማው፣ ሀገር አንክሳ መቅረቷ ነው ባይ ናቸው፡፡ ነውርና በደል እንዲህ ተጽፎ ካልኖረ፣ ባለጌም አያፍርበት፣ ልጆቹም አይሰጉበት በሚል መጻፉን የወደዱት ብዙ ናቸው፡፡
የሦስት አስርት ዓመታት ተቋማትን አጥፍቶ የመጥፋት ስልትና ደባ ሰለባ ነበር ያለውን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መነሻ አድርጎ የዩኒቨርሲቲውን ማኅበረሰብ መንፈስ በፍራቻ፣ በጥላቻ፣ በንቀት፣ በባይተዋርነትና በስግብግብነት የመረዘበትን መንገድ ያሳያል፤ይለናል መጽሐፉ፡፡
ደግሞ የሚቃረኑ አሉ፤ አንዳንዶቹ ምክንያታቸውን ሲያስቀምጡ፤ የሰው ክብር ይነካል ይላሉ፡፡ የሰው ክብር ይነካል ብሎ መጽሐፍን መቃወም፣ በእርግጥ ከሀገር ክብር ይልቅ የዘራፊ ሞገስ ተሰቅሎ ይኑር አይነት ትርጉም ይሰጠናል፡፡
የሰውዬው ክብር ሊኖር የሚገባው ከሚያስከብር ስራው ጋር ነው፡፡ የሚያዋርድና ሀገርን የሚያወርድ ስራ ሲሰራ ለኖረ ሹመኛ ስምና ሰብእና መጨነቅ፣ ሀገር የመግደል ያህል ነው፡፡ በዚህ መጽሐፉ ባይታማ ደስ ይለኛል፡፡
ይልቁንስ ሌሎች የሚሉት ደግሞ አሉባልታ ሆነ ማስረጃ የለውም የሚል አለበት፡፡ አሉባልታ ነው እውነት የሚለውን ለመሞገት ብርሃኑ እንዲህ ተደረገ፣ እንዲህ ሆነ፣ እንዲህ ተባለ እያለ የተነተነውን እንዲህ አልሆነም የሆነው እንዲህ ነው እያሉ መሞገት ያስፈልግም ይመስለኛል፡፡
ብርሃኑ ደቦጭ የታሪክ ሰው ነው፡፡ እነኚህን መረጃዎች በተጨባጭ ሰብስቦ ከሆነ መጽሐፉን ያሰናዳው የተቋማት ነውር ላይ አድፍጦ ታሪክን የሚያኖር የታሪክ ስራ ቢያንስ በሚሞቱ ተቋማቶቻችን ህይወት ታሪክ ውስጥ ከባዱ ደዌ የቱ ጋር እንደጀመራቸው ፍንጭ የሚሰጥ እውነት ያኖርልናል፡፡
የብርሃኑ ዕይታዎች መንደርደሪያቸው፣ የፖለቲካ ደባና የፖሊሲ ቅሌቶች ናቸው፡፡ እንደ ጸሐፊው፤ ትንንሽና ሀገር ያሳነሱ ተራ ሹማምንት ሁሉ የዚህ ውጤት ናቸው። በአካዳሚክ ክብራቸው ከፍ ያለ ስም የነበራቸው ሰዎችም ቢሆኑ በተሾሙ ማግስት የፈጸሙት ቅሌት መነሾው ይህ የፖለቲካ ደባ ነው፡፡ ያደባው ትህነግ ነበር፤ ውጤቱ ግን በድንቁርና ጌቶች በኩል፣ ህዝቡ ሁሉ የጨለማ ተገዥ ሆነ፡፡
ስለ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚተርከው የድንቁርና ጌቶች፤ ለሌሎቹና ለተከታዮቹ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መስታወት ሆኖ የሆኑትን ያሳያል፡፡ ማንጸሪያው የቀድሞው የቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ፣ የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ይሁን እንጂ ተቋም የማክሰሙ ወረርሽኝ በተከታታዮቹ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ግንባታ ላይ ያደረሰውን ስቆቃ ያሳየናል፡፡
ፖለቲካ ክብሩ ነውር ሲሆን ሀገር ምን እንደምትሆን የድንቁርና ጌቶች ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ትውልድ ትናንትን ይመለከትበታል። የተበላሸ ትውልድ እንዴት እንደተሰራ ለማየትም ያስችላል፡፡ ደግሞ ለተቋማት ታሪክ ስነዳ አርአያም ነው፡፡
የድንቁርና ጌቶች ምሳሌም ነው፡፡ ነገ የቴሌ መብራትና ውሃ ተቋማት በእነማን እንዴት እንደተመሩና እንዴት እንደወደሙ አነሳስቶ ታሪክ ለሚያስቀር ሰው ጉልበት ይሆናል፡፡ በኢትዮጵያ በአሰራርና በፖለቲካ ደባ አፈር ድሜ የበሉት ተቋማት፣ ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ አይደሉም፡፡ የዩኒቨርሲቲዎችን ከባድ የሚያደርገው ተስፋ አምራች፣ ብቃት አፍሪ፣ ሊቅ ፈልፋይ መሆናቸው ነው። እንዲህ ካሰብን ዩኒቨርሲቲዎቹ ለሀገር ህልውና መሰረት ናቸው፤ ልንል እንችላለን። መሠረቱ እንደምን ሲፈርስ እንደቆየ፣ የድንቁርና ጌቶች የሚነግረን ብዙ ነገር አለ፡፡ ውስጡ ከነበረ አንድ የዩኒቨርሲቲ መምህር በማስረጃ ጭምር ተደግፎ ሰማነው እንጂ ዳር ቆሞ ለሚያነፍንፍም ቢሆን ሲሰነፍጥ የኖረ እውነት ነው፡፡
የድንቁርና ጌቶች በነጻነት ስማቸውን እያነሳ ግብራቸውን እያወሳ ሀገር ስትፈርስ እንደምን ድርሻቸውን እንደተወጡ የሚናገርላቸው ሰዎች አሉ፡፡ በተቃራኒው በግብራቸው ስማቸው ከተነሳው ያላነሰ አስተዋጽኦ ኖሯቸው ወይ በደራሲው ዝምድና ወይ ድግሞ በልዩ ርህራሄ ስማቸውን ያላነሳቸውን በውክልና የገለጻቸው አሉ፡፡ የመጽሐፉ ድክመት የሚመስለኝ ይሄ ነው፡፡
መጽሐፉ አንዳንዶቹን በገለጸበት ርቀት ሌሎቹ ጋር ልክ ያልሆነ ጥንቃቄ ክብካቤና ገበና ሽፈና ይታይበታል፡፡ አንዳንዶቹ ጋር ያለው ዕይታ ደግሞ መስጠት ወደሚፈልገው ትርጉም የቀረበ እንደሆነ ታይቷል፡፡ ለምሳሌ የሰው ስም ያነሳና አንዳች ፋካሊቲ እንኳን የመምራት ልምድ ሳይኖረው ብሎን ሌላውን ሰው ደግሞ ተመሳሳይ ልምድ ሳይጠይቅበት በውድድር መሸነፉን እንደ ዩኒቨርሲቲው ውደቀት ቆጥሮ ይነግረናል፡፡ ለታሪክ ምሁራኑ ውግንና ያለው ሰፊ ልብም ቢሆን ሳያሳማው የሚቀር አይመስለኝም፡፡
የመጽሐፉ ህትመት ጥራት እጅግ የሚደንቅ ነው፡፡ የአጻጻፍ ቋንቋውና የመረጃ አቀማመጥ ስልቱ ደግሞ ጎራውን ምሁራዊ ያደርገዋል፡፡ ከምንም በላይ እንዲህ ባለው ተቋማዊ ታሪክ ስነዳ ሀገራዊ ልማድ ቢኖረን ግለሰቦች ተቋም ገድለው ተቋም መሩ በሚል ቀልድ ክብር አግኝተው አያዋርዱንም ነበር፡፡ ብርሃኑ ደቦጭ በድንቁርና ጌቶች የሚበልጥ ነገር የሰጠን ልማዱ ከተስፋፋና ከቀጠልንበት ሀገር የመስራት አንድ አድራሻው ተቋማዊ ግንባታውና የግዙፍ ተቋማት ጤናማነት እንደሆነ ያሳየናል፡፡ የድንቁርና ጌቶች ጭምቅ ሲደረግ የድህነት ምክንያቶቻችንን ጠባይ ግብርና ውጤት ያሳየናል፡፡ እያንዳንዱ የዩኒቨርሲቲ መሪና የሥራ ሃላፊ ሊያነበውና ራሱን የቱ ጋ ነኝ ብሎ ሊፈተሸበት የሚገባ መጽሐፍ ነው፡፡


Read 1035 times