Saturday, 27 March 2021 13:51

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(0 votes)

 “ብትመርጥ ምረጥ፤ ባትመርጥ አንድ ባንድ አገኝሃለሁ”
                         
             አንድ ወዳጄ ሲያጫውተኝ ቀደም ባለ ጊዜ አውቶብስ ተራ የሚገኘው የልዑል መኮንን ት/ቤት ተማሪዎች፤ ለተማሪዎች መማክርት (student Council) ጉባኤ አባልነት ብቁ ናቸው የሚሏቸውን አባሎች ለመምረጥ አጠቃላይ ስብሰባ ያደርጋሉ። ተማሪዎቹን አሳምኖ የካውንስሉ አባል መሆን ቀላል ጉዳይ አልነበረም… ያኔ። ዓላማው የተማሪውን የግል ችሎታና እውቀት፣ ልምድና ማህበራዊ ግብብነትን ይጠይቃል። ቀልድና አድቬንቸር በፖለቲካና ሌሎች ማህበራዊ ንቅናቄዎች ውስጥ ያላቸው ሚና ሳይዘነጋ፣ ያኔም ቢሆን አንዳንድ ተፎካካሪዎች ወደ ከፍታ ለመውጣት  የሚጓዙበት እርምጃ ያስገርማል።
የልዑል መኮንኑ በቀለ ጉልቤም ከላይ ላነሳነው ጉዳይ የማይናቅ ምሳሌ ሆኗል። በቄ ባደረገው መሳጭ  ንግግር፣ ቃሉን እንደሚጠብቅ ደጋግሞ አስረግጧል።
“ውድ ተማሪዎች!”
“አቤት!”
“ጥያቄዎቻችሁን ለሚመለከታቸው አካላት አቅርቤ ካላስፈፀምኩ እኔ ´በቀለ´ አይደለሁም”… በማለት። በቄ በዚህ አባባሉ ተጨብጭቦለታል። ከመድረክ ሊወርድ ሲል ንግግሩን ያጠቃለለበት መቋጫ ግን የበቄን እውነተኛ ማንነት ቁልጭ አድርጋች አሳይታለች።… መጨረሻ ላይ እንመለስበታለን።
*   *   *
የቀድሞ ሰፈሬ በቅሎ ቤት ከሉቃስ ፋርማሲ ጀርባ በተለምዶ ውሃ ልማት ተብሎ በሚጠራው መንደር ሲሆን መስሪያ ቤቴ አንጋፋውና ዝነኛው ኩባንያ የኢትዮጵያ አማልጋሜትድ ሊሚትድ ዋና መስሪያ ቤት ህንፃም በወቅቱ የአካባቢው ሞገስ ነበር። ቃሊቲ ከሚገኘው ከመንገድ ትራንስፖርት መስሪያ ቤት ጋር የሚዋሰነው ሰፊ ግቢም የዚሁ ኩባንያ ንብረት ሆኖ በውስጡ ትልቅ ወርክ ሾፕና ሰፊ ጋራዥ እንዲሁም አስር ቋቶች ያሉት የዱቄት ፋብሪካና ላቦራቶሪ ነበረው። ዛሬ ሁሉም የሉም።
ወዳጄ፡- አንድ ጊዜ ንጉሡ “ከፈላስፋዎች ማንን ያደንቃሉ?” ተብለው ሲጠየቁ “ችሎ ማለፍ ጥሩ ያለውን ነው” በማለት ታላቁ ቮልቴርን ጠቅሰዋል ሲባል ሰምቻለሁ። ምክንያቱም አባዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ብሶተኛ ነው። ህመማችንን በመቻቻል ካልተቋቋምነው የልጆጃችን ነገ ይበላሻል። ኢትዮጵያ አማልጋሜትድን  ያነሳሁበት ቁም ነገር፣ በአገራችን ለምናየው ኢ-ፍትሃዊነት ዋናው ምክንያት በህዝብ ፍላጎት ያልተመረጠን መንግስት አናታችን ላይ መሸከማችን እንደሆነ የየራሳችንን ልምድ ምስክር መሆኑን በመግለጽና መጪው ምርጫ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄና ማስተዋል ሊኖረን እንደሚገባ ማሳሰብ የንቁ ዜጋ ሃላፊነት መስሎ ስለተሰማኝ ነው።
ወዳጄ፡- “ከሁለት ሰይጣናትም ቢሆን የተሻለውን መምረጥ ብልህነት ነው” ይላሉ ሊቃውንት። ይህንን እሳቤ መሰረት በማድረግ ነበር ለ1992 ዓ.ም ምርጫ የተመዘገብነው። ምርጫው በሚደረግበት ቀን ከጎረቤቴ ጋር ወደ ንዑስ ጣቢያው ጎራ ስንል ብዙ ነገሮች በአእምሮዬ ይመላለሱ ነበር። ዋናው ያሳሰበኝና ያጠራጠረኝ ጉዳይ፣ አብሮኝ የነበረው ሰው ለሌሎች ጎረቤቶቻችን ያልሰጠውን ትኩረት እኔ ላይ ሰብስቦ፣ ወደ ምርጫ ቦታው እንድንሄድ ከፍተኛ ግፊት ነበር። ያኔ ተፎካካሪ ሆነው ለምርጫ የቀረቡት ሶስት የፖለቲካ ድርጅቶች ነበሩ። የመላው አማራ ህዝብ ድርጅት (መኢአድ)፣ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) እና ኢህአዴግ። እያንዳንዱ ተመዝጋቢ ሰባት ሰዎችን የመምረጥ ዕድል ነበረው።  አንዱ ለተወካዮች ምክር ቤት፣ ስድስቱን ደግሞ ለሌሎች ምክር ቤቶች።
ወግ አልቀረም፤  ፎርማሊቲዎችን ጨርሰን ድምጽ በስውር ወደ ሚሰጥበት መጋረጃ እንደገባሁ የምርጫ ወረቀቱን ገልብጬ ጀርባውን ተመለከትኩ። እንደ ጠረጠርኩት በእርሳስ ምልክት ተደርጎበታል። ኢህአዴጋውያኑ ማንን እንደምመርጥ ለማወቅ ያደረጉት ሸፍጥ ነበር። ምንም እንዳልተፈጠረ አስመስዬ ከሶስቱም ድርጅቶች ሁለት ሁለት ሰዎችን መርጬ ወጣሁ።
ወዳጄ፡- ነፃ የፍትህና የዴሞክራሲ ተቋማት ባልነበሩበት፣ ምናልባት ለዴሞክራሲ ምርጫ ልምድ ግብዓትነት ተደርጎ ካልተቆጠረ በስተቀር አገራችን ውስጥ የተካሄዱት ምርጨዎች “Fake” ነበሩ ቢባል እውነት ነው። ይህ ማለት ግን የተቀማነውን የ1997 ዓ.ም ህዝባዊ ምርጫ አያጠቃልልም። በ1997 ዓ.ም ምርጫ ሊደረግ ፓርቲዎች ጎንበስ ቀና ማለት ሲጀምሩና ቅስቀሳው ሲጧጧፍ፣ አንዳንድ የመንግሥት ተቋማት ከወዲሁ የዜጎችን መብት ማክበር ችለው ነበር። ለምሳሌ ማንኛውም ሰላማዊ ዜጋ በተወሰነ አካባቢ ለስድስት ወራት መቆየቱ ከተረጋገጠ መታወቂያ ካርድ ይሰጠው ነበር። ያ መሰረታዊ መብት ውሎ አድሮ በገዢው ፓርቲ ተደፍጥጧል። ገዢው ፓርቲ በሌሎች ከተሞችና ክልሎች እንኳ ለሚኖሩ አባሎቹ ያለ አዲስ አበባ ነዋሪነት መታወቂ የኮንዶሚኒም ቤት ባለቤት ሲያደርጋቸው፣ ብዙ ምስኪን የከተማዋ ነዋሪ ግን “መታወቂያ የለህም” በሚል ሰበብ የዜግነት መብቱን ተነፍጓል።
ወዳጄ፡- በዚህ የምርጫ ዘመን ተመሳሳይ ስህተት እንዳይደገም ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ሆኑ ህጋዊ ስልጣን የሚጨብጠው መንግስት፣ ጥንቃቄ ሊያደርግ ግድ ይለዋል። አለበለዚያ ፈረንሳዮች እንደሚሉት “ደዠ” እና “ደ ፋክቶ” እንደ ተነፋፈቁ ይተላለፋሉ። እዚችጋ  ፋታ ወስደን ወደ ዋናው ቁም ነገር እንለፍ።
የሰውየው በር ተንኳኳ…
“ማነው?”
“እኔ”
“እኮ ማ?”
ዝም።… በሩ ሲከፈት
አጅሬው ነበር።… ሰውዬው ነቃ።
“አንተ ነህና ?”
“እንዴታ”
“ከፍተህ መግባት እየቻልክ ማንኳኳት ለምን አስፈለገህ?”
“ይኸ´ኮ  ነው ናንተ ችግር … በጨለማ እየሄዱ ነገረኛ ያደርጉኛል” አለ አሉ ጅብ።
“ሃ!ሃ!ሃ!... ለመሆኑ በደህና መጣህ? “
“በሚቀጥለው ምርጫ ስለምወዳደር ደጋፊ እያሰባሰብኩ ነው”
“የመወዳደሪያ ምልክትህ ምንድን ነው?”
“የሞባይል ስልክ”
“ዓላማህስ?”
“ዓለምን አንድ ማድረግ”
“ዓለም አንድ ከሆነ አንተ እንዴት ይመችሃል?”
“ሰይጣን ማለት´ኮ ከእውነት በተቃራኒ ማሰብ ማለት ነው። “
ብዙ የአገራችን ሰዎች በተቃራኒ ስለሚያስቡ በተዘዋዋሪ መንገድ ደጋፊዎቼ ናቸው። ከፋፋይ ነኝ ብዬ እውነቱን ብነግራቸው ግን አንድ ሆነው ማረፊያ ያሳጡኛል።… ለዚህ ነው የማስመስለው።
“ቢያንስ እውነት በመናገርህ ትመሰገናለህ”
“የእውነት ተቃራኒ መሆኔን ግን እንዳትረሳ”
“ሰዎች የሚረባረቡብህ ገበናቸውን እያወቅህ ዝም ስለምትል የሌለህ እየመሰላቸው ነው”
“አሁን ግን ልወዳደር መጥቻለሁ”
“ካ! ካ! ካ”
ወዳጄ፡- አንድን ነገር ከሌላው ጋር የምናነጻጽረው አንደኛው ከሌላኛው ጋር ያለውን ተወራራሽነት ፣ ዝምድናና ተጋግዞ የመኖር ተፈጥሯዊ ባህሪ ወደ ጎን ገለል በማድረግ ወይም ልዩነታቸውን ከሚገባው  በላይ በማጉላት ወይም አንዱ ፍጡር በሌላው ላይ የበላይነት እንዳለው በማሰብ ነው። ለምሳሌ ሰዎች ድህነትና ድንቁርና በኑሯቸው ላይ በፈጠሩባቸው ምክንያቶችና ውጣ ውረዶች ሳቢያ እርስ በርሳቸው እንዳይግባቡ የሚያደርጓቸው ሳንካዎች ይበዛሉ። እነዚህ አለመግባባቶች ምንም ያህል ቢገዝፉ ሰውን “ሰው” የሚያሰኘው መሰረታዊ ባህሪውን አይሽሩትም። የመገዳደርና የመገፈታተር ባህሪ የሚመነጨው ምናልባት በሰዎችና በዱር አራዊት መካከል “አለ” ብለን ከምናስበው ዓይነት ቅራኔና መጠራጠር በመነሳት ሊሆን ይችላል።
ወዳጄ፡- አንዳንድ ጊዜ “እውቀት” የምንለው ነገር በጊዜ ሂደት፣ በሳይንስና ስልጣኔ ዕድገትና በአዳዲስ ግኝቶች መበራከት ሊያድግ፤ ሊለውጥና ጨርሶ ሊቀየር እንደሚችል ማሰብ አንዘናጋለን። ሌሎች ነገሮችን ወደ ጎን ትተን እኔ እንደሚመስለኝ ማናቸውም ፖለቲካዊ ጉዳዮች መታየት ያለባቸው “ይመስላሉ ወይም ይቃረናሉ”ብሎ ከማሰብ አኳያ ብቻ ሳይሆን ከመሆንና ካለመሆን ተፈጥሯዊ ዕውነት ጋር በማዛመድ ቢገመገም ተገቢ ነው፡፡ ለምሳሌ በቅርብ ጊዜ በተደረገና በቢቢሲ ሬዲዮ ይፋ በተደረገ ጥናት፤ ዛፎች ተጋግዘው እየተመጋገቡ የሚያድጉ የተፈጥሮ በረከቶች እንጂ እያንዳንዳቸው እራሳቸውን ለማቆየት የሌላውን ድርሻ እየተሸሙ የሚኖሩ እንዳልሆኑ ተረጋግጧል፡፡  colaborators itors በማለት። ይህንም ለዘመናት በቅጡ ሳንረዳ እስከ ዛሬ የዘለቅንበትን የቻርልስ ዳርዊን survival of the fittest  ፅንሰ ሀሳብን እንደገና እንድናስብበት አድርጎናል፡፡
ወዳጄ፡- ሌላኛው  ልብ በማለት የሚገባን ዋና ነገር ቢኖር፣ ሳይንስም ሆነ ጥበብ የሰው ልጅን የኑሮ ጫና የሚያቀሉ አጋዦቹ መሆናቸውንና ከተፈጥሮ ጋር ያለውን ግንኙነት መልክ የሚያሲዙ የስልጣኔ መንገዶች እንደሆኑ ነው፡፡ ሁሉቱም የዕውቀት ዘርፎች የሚተላለፉበት ድልድይ መሰረት የቆመው በሰብአዊነት ዋልታ ላይ ነው፡፡ ሰብአዊነትን መሰረት ያላደረገ የፖለቲካ ፉክክርና ምርጫም በኪሳራ እንደመንገድ ሆኖ ይሰማኛል!!
*   *   *
ወደ ጨዋነታችን ስንመለስ፡-በቄ ለተማሪዎቹ መልስ ካላገኘ እሱ ´በቀለ´ እንዳልሆነ መናገሩንና ይህም አባባል አድናቆትን እንዳተረፈለት አውርተናል፡፡ ችግሩ የተፈጠረው አጅሬው ንግግሩን ጨርሶ ከመድረክ ሊወርድ ሲል ካፉ ያመለጠውና ማንነቱን ያጋለጠው ዓረፍተ ነገር ነበር፡፡
“ብትመርጥ ምረጥ ባትመርጥ አንድ በአንድ አገኝሃለሁ!”
ሠላም!


Read 1046 times