Tuesday, 30 March 2021 00:00

ደግ ደራሲ ይኑር!

Written by  መሳይ ደጉ
Rate this item
(1 Vote)

   “መቼ ነው ግን ይሄን ማጨስ የምታቆመው? በፉጨት መተንፈስ እስክትጀምር ነው እንዴ የምትጠብቀው? “
ከፊት ለፊቱ አስተካክሎ ያስቀመጠላት ወንበር ላይ ጉልበቷ ድረስ የጠቀለላትን ጥቁር ኮት አውልቃ እያጋደመች ተነጫነጨችበት...
ሲጋራውን ከከንፈሩ ባላቀቀበት እጁ ገና የኮቱ ሙቀት ያልለቀቀውን ቀጫጫ ክንዷን ቀጨም አድርጎ ጎተት አደረጋትና...
“አንቺ መጠየቅ ሲሰለችሽ ፍቅር... አንቺ መጠየቅ ሲሰለችሽ...” አላት ጭስ የተፋ ከንፈሩን ጆሮዋ ስር እያሻሸ...
በየተራ ፈገግ ብላለትና ገላምጣው፣ እግሮቹ መሀል ተመቻችታ ቆም አለች...
እሱ፤ የሲጋራ ጢስ ከምትጠላው በላይ ስለምትወደው ደስስ እያለው ፈገግ ይላል...
እሷ፤ ባር ላይ ቢሞት የማይቀመጥ ልጅ በጊዜ ተሰይሞ፣ የሚመቻትን ቦታ ይዞ ሲጠብቃት ስለሚያመሽ፣ እየኮራች ፈገግ ትላለች...
የሚያመሹበት ቤት ከሰኞ እስከ ሰኞ ሰው የሚበዛበት... ፈረንሳይኛ ሙዚቃ የሚዘወተርበት ቤት ነው...
“ለምን ይሄን ቤት መረጡ?”
ምናልባት መዋደድ የጀመሩ ሰሞን ይመቻቸው ስለነበር ይሆናል...
ምናልባት እሷ mojito፤ እሱ ደሞ በሁለት ሶስት ሀበሻ ምርቃናውን ከሰበረ በኃላ፣ ፓስቲስ  የሚባል በውሃ የሚበረዝ የፈረንሳይ አረቄ መጠጣት እንደሚያዘወትሩ አውቀው፣ በምልክት ብቻ የሚታዘዟቸው አስተናጋጆ ስላሉበት ሊሆን ይችላል ...
ብቻ it really doesn’t matter ነገር... አንዴ የዕለቱ ርዕሳቸው ውስጥ ከገቡ በኋላ ዘፈኑም... ሰዉም... ግርግሩም... ድብዝዝ ብሎ ማጀብያ ብቻ ይሆናል! ሁለቱ ብቻ ይደምቃሉ... ሁለቱ ብቻ ይቀራሉ... ዐይኖቻቸው በሚናበቡበት ትኩረት ውስጥ ከቧቸው የሚንጫጫ መዐት ቢኖርም የለም... ቢጮኽም አይሰማም...
ዞር ብሎ ባይቃኝም የቤቱ ጎረምሳ እኩሌታው፣ ዐይኑን ከሷ ላይ መንቀል እንደማይችል ያውቃል።
“...ምን አይነቱ እድለኛ ነው?... ምናባቷ ሆና ነው?... ምናባቱ ታይቷት ነው?...”
እያሉ በሚጨነቁ ምስኪኖች ተከብቦ፣ እንደሚጨብስ ያውቃል። ግን ደንታው አይደለም፡፡ እንኳን አሁን ጋል ብሎ... ቀን በስራ ተወጥሮም አንደኛ ጉዳዩ... ለሚታይ ለሚዳሰሰው ዐለም ገዝፋ መንፈስ የሆነችው... አሻቅበው የሚያዩት ዐይኖች ውስጥ የምትኖረው... ተዐምረኛ ሴት ናት።
ካፈጠጠባት ሁሉ ተለይቶ እሱ ብቻ ምን ያህል አፍ ከሚያስከፍት ቁንጅናዋ እንደምትገዝፍ ያውቃል... ስራው ነውና ከዛ ሁሉ ገልጃጃ ብኩን፣ በሰፊ ትከሻው ሽፍን... ሽሽግ... ድብቅ... ያደርጋታል።
“ባክሽ ትወጂኛለሽ!”  ይላታል፤አንዳንድ ቀን ስታዝገው...
“እህ... በምንድነው እንደዚህ እርግጠኛ የሆንከው”?” ትለዋለች፤ የምታውቀውን መልስ በፈገግታ እየጠበቀች...
“አገጩን ዝቅ አድርጎ በፍቅር የሚያፈጥብሽም... ወገቡን ይዞ የኑሮ ፍልስፍናሽን የሚሞግትም ሰው አንድ እሽግ ውስጥ የታባሽ ታገኛለሽ?” ይላል፤ አፍንጫውን እየነፋ...
“I know me love...I kno” ብላ ግማሽ ከንፈሩን ሳም ታደርገዋለች... ፈገግታዋ ወደ ሳቅነት እየተሽኮረመመ...
ሙሉ ቀኗን ደረቷ ላይ አፍጥጠው ከሚያዋሯት በድኖች ጋር ባትውል ምናልባት...ለለውጥ እንዲሆን የምር የምታስበውን በስሜትና በዕውቀት በሚሞግት...ሙሉ ቀኑን የኒያላና የሽቶ ቅልቅል ሲሸት በሚውል አንድ ጎረምሳ፣ ይሄን ያህል አትወሰወስ ይሆን ነበር...
“ምንድነው ቅድም ሲያነጫንጭህ የነበረው?” ተንጠራርታ ወንበሯ ላይ ቁጭ ብላለች፤ አሁን...
“ከሆኑ ሰዎች ጋ ተጨቃጭቄ ነው ባክሽ... ያው ይሄንን ህዝብ በፍቅር አይደል የምወደው...?”
አዲስ ሲጋራ በፍቅር እየለኮሰ ፈገግ አለ...አፉን አንሻፎ ፍፍፍፍ... እያለ ቀጠለ...
“ምን እባክሽ... these days ብቻ ቆሞ ምንም ማለት አልተቻለም እኮ... ስለ በርበሬ መወደድ በተነሳ ርዕስ የሆነ ነገር ስትዪ፣ አንዱ ደምስሩን ገታትሮ፤ ‘አይ አንተ ከእነ’ንትና አንዱ ነህ... ፀረ እነ’ንትና ነህ’ ይልሻል... ከገበያ ወደ phobia ባንዴ...”
ብርጭቆዋ ውስጥ ያለ ቅጠል በ’ስቶሮው እያማሰለች ድክም ብላ ትስቃለች...
“እንደው ምን ይሻልሀል? ለምን ደራሲ አትሆንም ግን? በገፀባህሪዎችህ ያሻህን እስከ ጥግ ብለህ ይወጣልሀል...”
ሳቋን ትቀጥላለች...
ፊቱን ጭምድድ አድርጎ ሊናደድባት ይሞክራል...
“ማለት የሚፈልገውን በገፀባህሪዎቹ ብቻ ማለት የሚችል ደራሲ ነው ነፃ ወይስ ነፃነቱን ያገኘበት ገፀባህሪ?... ጭራሽ ደፋሩ ፍጥረቱ ባለለት ነገር ህይወት አግኝቶ በነፃነት ሲኖር፣ ፈጣሪው በሰቀቀን የልብ ህመም ነው የሚሸምተው... እና ከደራሲው ተደራሲውን መሆን አይሻልም?” ዐይኖቿ ውስጥ የምትኖረውን... የሚያምናትን ውበት ጠየቀ...
“Do you remember that incident I told you about ከSunday school ቲቸሬ ጋ? አጉል theology ተማርኩ ብሎ ሲያስቀባጥረው ‘እግዚአብሔር በፍጥረቱ ስህተት ሊኖርበት አይችልም’ ምናምን ብሎን ‘እና የመሳሳት አምሮት ነዋ የሚሳሳት ሰው ያስፈጠረው’ ብዬ የጨለለው ነገር... አፈር ይብላ... እሱ ነው ይኸው አሳግዶ ስድ ያደረገኝ... “
ስትሮዋን እየመጠጠች ቀጠለች...
“... እውነትህን ነው! ለነፃነቱ ከደራሲው ተደራሲውን መሆን ሳይሻል አይቀርም...”
ቅልጥ እያለ ያያታል...
ቁምነገሩን ይተዉታል...
ማን ቤት ደረስ ብለው እንደሚደበቁ ይቀምራሉ...
ከለሊቱ ስንት ሰዓት ተለያይተው፣ ነገ ከምሽቱ ስንት ሰዐት እንደሚገናኙ ይጨቃጨቃሉ...
ይስማማሉ...
ቀጭኗን አስተናጋጃቸውን አጣድፎ ጠራትና ሂሳብ ጠየቃት... የነፍሱን ቀጫጫ እጅ ጨብጦ የማምሻቸውን ቤት ደረጃ ወረደና በር ላይ ወደቆመ አሮጌ Lada እየጎተተ ወሰዳት...
ሲያልፉኝ በቅሬታ ወደኔ ዞር አለና...
“አሁን ቀንተህ ነው አይደል የሚጨስ Lada ውስጥ ህልምህ ከሆነች ቆንጆ ጋ የምታጉረኝ?”
አለኝ ፈገግ ብሎ...
ቀጭኗን አስተናጋጃቸውን አጣድፎ ጠራትና ሂሳብ ጠየቃት... የነፍሱን ቀጫጫ እጅ ጨብጦ የማምሻቸውን ቤት ደረጃ ወረደና በር ላይ ወደተገተረው ነጭ Lincoln suv ተንደረደረ...
“እንዳንተ ኑሮ የተመቸውም ያማርራል እኮ...” አለችው ፍልቅልቅ እያለች...
“ደግ ደራሲ ይኑር ፍቅር! ደግ ደራሲ ይኑር!” አላት ፈገግ ብሎ!Read 165 times