Print this page
Monday, 29 March 2021 00:00

አብረን እንስከን - 2

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ያ! ታላቁ ባለቅኔ ሎሬቱ. . .
ያገር አድባር-የህዝብ ዋርካው «እ…!» እያለ፤
ስለጥበብ፥ ስለ ህዝበ-ዓለም እድሜ ልኩን እንደተብሰለሰለ
ቢቸግረው ”አብረን ዝም እንበል” እንዳለ፤
ከነቁጭቱ - ከነህልሙ እንደዋዛ ከንበል አለ፡፡
ግርምቴ . . .
ተፈጥሮ በነጠላና በህብር በፈጣሪ ጥበብ መዋቀሩን ላስተዋለ
የተነጣጠለ፥ የተቃረነ ቢመስልም
በፈጣሪና በተፈጥሮ ህግጋት ነው’ኮ ተገማምዶ፥ተሳስቦ  በአብሮነት የተሳለ፡፡
የሰው ልጅ ግና…!
«በህግ አምላክ!  . . .   በህገ መንግስት!” »  እየተባባለ
ቁርጥራጭ ብረታ ብረት እየሳለ፤
በሆነ ባልሆነው እርስ በርሱ አንገት ለአንገት ሲቀላላ ስለምን በከንቱ ዋለ?
የኛ ጉዶች፡-
በምላስና-ጠመንጃ እየተቋሰሉ¡
በዛቻ-በፉከራ ተጋግለው ሲገዳደሉ እየዋሉ
በየቤተ-ሃይማኖታቱ ደጃፎች ራሳቸውን ብፁዕ ለማስመሰል እየታገሉ፣
በየሸንጐው -በየፓርላማው እጃቸውን ሰቅለው <ፍትሐዊነት¡ እኩልነት¡> እየተባባሉ፤
በዕውንም ሆነ በህልማቸው ግን
 ለበቀል ለየጣዖታቱ-ለየአድባራቱ ሳይቀር ስለምን ስለት ተሳሳሉ፤
ስንት ሰውስ ሲሰዋ ይበቃ ይሆን? ዕርቅ ለማውረድ-ለአብሮነቱ ተባባሉ፡፡
ጡንቻ ለጡንቻ ተገጫጭተን
ትከሻ ለትከሻ ተለካክተን
በቃላት ድምቀት፥ በዲስኩር ብልጫ ተወናብደን
በባህል፥ በታሪከ ትርክት ተቀራርነን
ከእስራቱ-ግርፋቱ፥ ከደም አዙሪቱ መውጣት ቢያቅተን   
ምነው ለህዝቡ እፎይታ ብንሰክን አብረን።
ወገኖቼ . . .     
በማናውቀው፥ በማያስማማን ሚዛን ተመዛዝነን
በቃላት ጋጋታ በህግ መሰል አንቀጻት ተደናቁረን
መደማመጥ መግባባት ካልቻልን
እባካችሁ ህዝብ አናጫርስ፥ አገር አናፍርስ በደመ-ነብስ ተደናብረን፡፡
ከአልቦ በታች ቁልቁል እንዳይሆን ነጋ’ችን፤
ምናለ  ብንሰክን አብረን    
ህዝብና አገርን ለማዳን ብለን፡፡
ቃል-እምነት-መሀላ በስጋ ተበልጦ ቁልቁል ከምንወድቅ
በምድር በሰደድ፥በሰማይ በሲዖል እሳት ከምንነድ
አይሻልም እንዴ ወገኔ?
አብረን ሰክነን በአገራችን ፍቅርና ሰላምን ብናጸድቅ፡፡
ሁሉም በየጐራው እኔ ነኝ መነሻው፥ አቅኚው ካለ
ያም ይህም እርስ በርሱ ተጧጡዞ ያለልኬት «ገፋኝ-ጨቆንከኝ»  ከተባባለ
በጥላቻ . . . በንቀት አገር ምድሩ ከተበከለ
የሥነ- ሂሊና ሚዛኑ ከተከነበለ
ከዚህ በላይ ውድቀት- ድቀት- ሞትማ የታለ፡፡
ወገኖቼ . . .
ይሻል ይሆናል-ካልን እስቲ በጋራ እንሂድ
ወደ የ…ክልሎቹ አብረን  እንንጐድ…
ህገ መንግስት «ይቀደድ!...አይቀደድ!» ብለን፥ቸኩለን ሳንፈርድ
እባካችሁ! በቅድሚያ፥ የህዝባችንን ዕንባ፥ አብረን እናድርቅ፡፡
ከድምጽ ማጉያና ከእጅ መዳፍ ጭብጨባ እንገለል፡፡
ለአንድ አፍታ እንኳን-ከየአደባባዮቹና  ከየአዳራሾቹ እንነጠል፡፡
እንደጥንቱ በዛፎች ጥላ ስር እንጠለል፡፡
በጋራ ሆነን በየወጋችን-በየባህላችን  አብረን «ሰላም-እርቅ» እንበል፡፡
ከአባይ ማዶ ወደ ቤንሻንጉል-ጉሙዝ ወደ ህዳሴው ግድብ አብረን እንውረድ
እጅ ለእጅ ተያይዘን በፋሲል ግንብ . . .በጣና ዙሪያ እስክስታ እናውርድ፡፡
አብረን እንሂድ ጋምቤላ ከለማለሙ አገር
በባሮ ወንዝ ላይ በፍቅር መርከብ አብረን እንሸርሸር፡፡
ላሊበላ ሂደን «እግዚኦ ማረን» እንበል
የፈጣሪን ቡራኬ መለኮቱን እንቀበል፡፡
ወደጥንታዊቷ አክሱም እንዝለቅ …
ከአዴታቱ እጅ ተቋድሰን አንባሻውን
በበረከቱ እንፈወስ እርስ በእርስ ተመራርቀን፡፡
«ሆ!ያ ማሬዎ! -ማሬዎ!» አብረን እያልን
ቢሾፍቱ-ሆራ አርሰዲ ለእሬቻ እንውረድ
ሀባቦ-መርጋ ጉራቻ … እርቁን በእጃችን ጨብጠን፡፡
ወደ አርባ ምንጭ እንዝለቅ …  
ለህዝብ ክብር፥ ለወገን ፍቅር ብለን፥ ከኒያ ደጋግ ህዝቦች ጋር ሆነን
እርጥብ ሳር ይዘን፥ በመሬት ላይ  እንውደቅ አብረን፡፡
ወደ ቦረና ከአንጋፋዎቹ መገኛ አብረን እንዝለቅ
የገዳ-ዲሞክራሲ ችግኙ በሁሉም ሥፍራ እንዲጸድቅ፤
በአንደበተ ርቱዓኑ፥ በንፁሀኑ አባገዳዎቹ  እንመረቅ፡፡
ወደ ጅማ -ወደ ከፋ ሽምጥ እንጋልብ
ከቡና ረከቦት ዙሪያ እንሰብሰብ!
«አቦል ጀባ!» እየተባባልን እንዋዋብ፡፡
ሐረር ጀጐል፥ ደገሃቡር ሶማሌ፥ ድሬ ሼህ ሁሴን አብረን እንዝለቅ
«አስቶፍሩላህ!...አላሁ አክበር! »  ብለን ከፈጣሪያችን እንታረቅ፡፡
ግርምቴ . . .
እንሂድ አፋር፥ ከቅድመ ዘራችን ከእናታችን ሉሲ አገር
እንድትተርክልን በእሳተ ገሞራ የመኖርን ሚስጥር
ለሚሊዮን አመታት አጽሟ ሳይፈራርስ የመዝለቁን ቀመር፡፡
እኛው በየአምስት አመቱ «ውረድ!...አልወርድም!»  ከምንባባልበት
ለ4 ኪሎው ወንበር ከምንዶልት፥ ከምንፋጅበት
ለህዝባችን፥ ለአገራችን ብለን በቅድሚያ አብረን ብንሰክንለት፡፡
ምናለ ጐበዝ! ለዚህ ምስኪን ህዝብ በቅድሚያ ብናስብለት፤
በሰቀቀን ባይባዝንበት፥ በችጋር- በጠኔ ባይረግፍበት፣፣

ሎሬቱ እንዳለው፡-
« . . . . . . .
ዳግመኛ ሞት ሳንሞት፥ አዲስ ቀን ሳይጨልምብን
ድፍን ደመና ሳይቋጥር፥ክረምት ውርጅት ሳይወርድብን
. . . . . . . ፡፡»
ወገኖቼ . . .
በኮሮና እና በብረት መሃል ተወጥረን
ጦርነቱ ከሚፈጀን፣ በሽታና ረሃቡ ከሚያረግፈን
ምናለ ፉከራው ቀረርቶው ቢቀርብን፡፡
እናም፡-
ለአንድ አፍታ እንኳን «አሐዳዊ!...ፊዴራላዊ» ቃለ ግነቱን ገተን
ህዝባችንን-አገራችንን ብናድን አብረን ሰክነን
ለጊዜው እንኳን ባንስማማም «ሜ. . . ሃቡልቱ ዱቢን » ብለን ተስማምተን፡፡
 አሰፋ ጉያ
መታሰቢያነቱ፡-
የሥነ ጥበብ ፍቅርንና ለህዝብ የመቆርቆርን ቀናኢነት ላወረሰኝ፤
ለጋሽ ለማ፤ የክብር ዶክተር ሎሬት አርቲስት፣ ሻምበል ለማ ጉያ ይሁንልኝ፡፡

Read 1216 times
Administrator

Latest from Administrator