Tuesday, 30 March 2021 00:00

አቶም (ምናባዊ ወግ)

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(0 votes)

  እኔ አቶም ነኝ፡፡ ብዙ ነገር አይገባኝም። ምን መሆን እንደምፈልግ ገና አላውቅም። … ዳንኤል ያውቅ ነበር፡፡ እሱ ሁሉንም ነገር ያውቅ ነበር፡፡ ወይንም አውቃለሁ ይል ነበር። ስለሚያውቅ ያስጨንቃል፡፡ ያስጨንቀኝ ነበር፡፡ ስሜን እንኳን እኔ ሳላውቅ አይደል እሱ ቀድሞ አውቆ ያወጣልኝ፡፡ ምን ያደርጋል… ሞተ፡፡ ሁሉንም ነገር ያውቃል፤ መሞቻውን ቀን ብቻ አላወቀም። ዳንኤል አባቴ ነው፡፡ ከሞተ አንድ አመት ከአራት ወር ሆኖታል፡፡ ሙት አመቱ ደንብ ተደግሷል፡፡
…ሰዎች ያዝኑልኛል፡፡ ዝም የምለው በአባቴ ሞት ምክኒያት ስለሚመስላቸው ነው፡፡ እኔ በቃ አቶም ነኝ፡፡ ምንም የምለው ነገር የለኝም፡፡ ዝም ብዬ መኖር ነው ስራዬ።… አቶም ባልሆን ማንን መሆን ነበር ፍላጎቴ?... እኔን’ጃ ምናልባት አጎቴን!
ተማም የእናቴ ወንድም ከአባቴ በጣም ይለያል፡፡ ሲጀመር ስለምንም ነገር አይጨነቅም። ስራ የለውም፡፡ አባቴ በህይወት እያለ ቤት አውልም ነበር፡፡ ከአስራ አንድ ሰዐት በኋላ ነበር ያኔ የሚገባው። ገብቶም ከቤተሰቡ ጋር አይቀላቀልም። እዛው ክፍሉ ይደበቃል፡፡… አባቴ ሲሞት ቤቱ የእናቴ ሆነ፡፡ ወንድሟ ትንሽ ዘና ማለት ጀመረ፡፡ … ድሮውንም አይጨነቅም ግን ይባስ ዘና አለ፡፡ ቤት መዋል ጀመረ፡፡
“ምንድነው የምትሰራው?” ተብሎ ሲጠየቅ፣ የማያፍር ወይንም የማይኮራ የሰው አይነት በምድር ላይ የለም፡፡ ብቸኛው የእሱ አይነት፣ በኩራት “ስራ አልወድም” የሚል ሰው የማውቀው ተማምን ብቻ ነው፡፡
አባቴ ሁሌ እናደተጨነቀ ኖሮ የሞተ ይመስለኛል፡፡ እድሜ ልኩን ሰርቶ ያተረፈው፣ የምንኖርበትን ቪላ ቤት እና አንድ ሚኒ ባስ ታክሲ ብቻ ነው፡፡ አባቴ ምንም ሳይኖር ሞተ፤ አጎቴ ደግሞ በጣም አብዝቶ በመኖር ሊሞት ነው፡፡ ብዙ ሱስ ነው ያለው፡፡ ውጭ ሲወጣ ይጠጣል፤ ቤት ሲቀመጥ ይቅማል፡፡ ሲተኛ ህልም ያያል፣ ሲነቃ ያነባል፡፡  አባቴ “ቦዘኔ” ነው ይለው ነበር፡፡ እናቴ “አርቲስት” ነው ብላ ነው የምትናገርለት፡፡ … ለእኔ ደግሞ…የሚመች፣ የማይረብሽ፣ የማያስጨንቅ… በተለይ በተለይ የማይንኮሻኮሽ ሰው ነው፡፡
ሁሉም ሰው ይንኮሻኮሻል፡፡ … አስተማሪዎቼ ይንኮሻኮሻሉ፡፡ “በአጭሩ ልግለፅላችሁ” ብሎ አርባ ደቂቃ የሚያወራ ሰው ሁሉ ለእኔ ይንኮሻኮሻል፡፡ የደረቀ ቅጠል በጫማ ስትረግጠው ተንኮሻኩሾ እንደሚደቀው፡፡… እናቴ ቡና አፍልታ የምታወራው ወሬ በሙሉ መንኮሻኮሽ ነው። እጣኑን በማጨሻው ላይ ስትበትን፣ ልክ እንደ አራት ነጥብ ነው፡፡ የአንድ ሀሜት ምእራፍ መዝጊያ፡፡
እኔ አቶም ነኝ፡፡ የሚወራውን አልሰማም። የፕሪፓራቶሪ ውጤት ቢመጣልኝ ባይመጣልኝ… አያስጨንቀኝም።… ለሁሉም ሰው ፈገግ እላለሁኝ፡፡ ፀሐይ የሆንኩ ይመስለኛል አንዳንዴ። የሰዎች ፊት ደግሞ እንደ ስጥ፡፡ የተሰጣ ፊታቸውን በፈገግታ አነቃቅቼ… በዝምታ ወደ ቤቴ እጠልቃለሁኝ። ሰዎችም ያንን ስጥ ፈታቸውን ጠዋት አውጥተው አስጥተው ማታ ያስገቡታል፡፡… ሲቆሉ፣ ሲወቀጡ፣ ሲበጠሩ… በአጠቃላይ ሲንኮሻኮሹ እኔ አልሰማቸውም፡፡
ፀሐይ ግን አንዳንዴ ጠባይዋ ይለወጣል። እኔን ጨምራ ምድርን ታቃጥላለች፡፡ እኔ አተም ነኝ፤ አልታይም፡፡ አልደመጥም። አለሁም፤ የለሁምም፡፡ ትምህርት ቤት አስተማሪ ሲጠይቅ አልንቀዠቀዥም፣ እጄን አላወጣም፡፡ በቀላሉ አልታይም፡፡ ሁሉንም መምሰል እችልበታለሁ፡፡
“ራዕያችሁ ምንድነው?” ብሎ የማንከሽከሻ ጥያቄ አስተማሪው ሲያነሳ፣ ተማሪው መንኮሻኮሽ ይጀምራል፡፡ “የሀገር መሪ” ወይንም “ባለሀብት” የሚል ተመሳሳይ መልስ ለመስጠት…እንደ ፈንዲሻ ይዘላል፡፡ እኔ መመለስ የምፈልገው “አቶም መሆን” ብዬ ነው፡፡ ግን ሌላውን መስዬ፣ የማይመስል መልስ እሰጣለሁኝ፡፡
“መነጠል በዚህ ህዝብ መሀል አደገኛ ነው” ይላል ተማም፡፡ እሱ ብቻ የተነጠለ ሰው ነው። ሰው ስለመሆኑ አይጠራጠርም። እሱ ጥሩ መደበቂያ አግኝቷል፡፡ “አርቲስት ነው” ትላለች እናቴ፡፡ በእሱ ፊት ግን እንደዛ ብላ ጠርታው አታውቅም፡፡ እንደዛ ብትለው ፀባዩ ይለወጥ ይሆን? … አርቲስት መሆኑን ለማሳወቅ ይንኮሻኮሽ ይሆን?
አንድ ስዕል አለች ደጋግሞ የሚስላት። ደግሞ በደንብ መሳል አይችልም፡፡ የሆነች ራቁተቷን የሆነች ሴት ነገር ናት፡፡ በግራጫ ቀለም ነው የሚስላት፡፡ ከሳላት በኋላ ግርግዳ ላይ ይሰቅላታል፡፡ የጡቷን ቅርፅ በተለያየ ጊዜ ይለዋውጠዋል፡፡… ከማን ወይንም ከምን ላይ እንደሚገለብጣት አይታወቅም። … ቤታችን ውስጥ ያለውን ማንኛውንም የጥገና ስራ የሚሰራው እሱ ነው፡፡ በፊት ዳንኤል ሳይሞት በፊት የቤት ውስጥ የጥገና ባለሞያነት ፉክክር ያደርጉ ነበር፡፡
“…ማናለ በፍላጎት ቢሰራው!?” ብሎ አባቴ የተሰራውን የመታጠቢያ ሳህን ሽቅብ-ሽቅብ እየተነፈሰ ይፈታዋል፡፡ አባቴ ከእናቴ በእድሜ ከፍ ይላል፡፡ እኔ ስወለድ ሀምሳ አራት አመቱ እንደ ነበር ድምጿን ዝቅ አድርጋ ሜላት ነግራኛለች፡፡ ሜላት እናቴ ናት፡፡ የሁለት እርምጃ ያህል ርቀት እንኳን የማትርቀው ሰራተኛችን፤ አጋር ነው ስሟ። ስሟ ይሁን ስራዋ… ወይንም ስራዋ ስሟ ግልፅ አይደለም፡፡
ድሮ… ሰው ሁሉ ሲያድግ እንደ አባቴ ኮት እሚለብስ፣ዣንጥላ የሚይዝ እና ሽማግሌ ሆኖ ባርኔጣ የሚጭን ይመስለኝ ነበር። እኔ ሳድግ እንደ አባቴ መሆኔ የማይቀር ነበር የሚመስለኝ። እናቴ ድሮ የተነሳችው ፎቶግራፍ ላይም እንደአሁኑ ረጅም ባለ አበባ ቀሚስና  ነጠላ ነበር የምትለብሰው፡፡ አባቴ ወጣት በነበረበት ወቅት የተነሳቸው ፎቶዎችም ላይ የሚለብሰው እስከሞተበት ጊዜ እንደነበረው ነው፡፡ እኔም ሳረጅ “እስኪኒ” ሱሪዬን ለብሼ መሆኑ ተገለፀልኝ። የመጪው ዘመን አባቶች ጥብቅ ያለ ቲሸርት እና ቁምጣ ለብሰው የሚሸመግሉ ናቸው፡፡ … ተማም ልጅ የለውም እንጂ የአባተነት እድሜ ላይ ደርሷል፡፡ እንዲያውም አልፎታል፡፡ የእሱ አይነት ሰዎችም በእሱ ዘምን ላይ ብቻ የሚገኙ ናቸው፡፡ አይደገሙም፡፡
አባቴ በህይወት በነበረ ጊዜ ቤታችን ጭር ያለ ነበር፡፡ በሰርቪስ ቤቶቹ ውስጥ ተከራይ አልነበረም፡፡ ጊቢው ፀጥ ያለ ነበር፡፡ የአባቴ መንፈስ አሁን ቡሉ ለሙሉ ጠፍቷል፡፡ ትልቁ በር አሁን ቀኑን ሙሉ ክፍት ነው፡፡ ሰው ሲገባ እና ሲወጣ ይውላል፡፡ አምስት ተከራዮች አሉ። ሁለት ልጆች ያሉዋቸው ሰውዬ እና ወጣት ሚስታቸው ትልቁን ባለሁለት ክፍል በአንድ ጥግ ይዘዋል፡፡ ከእነሱ ቀጥሎ አንድ ጴንጤ ሰውዬ ብቻውን የሚኖርባት ክፍል አለች፡፡ ከእሱ ቀጥሎ ሾፌር ሰውዬ ይኖራል። ሾፌሩ በሳምንት ወይንም በሁለት ሳምንት አንዴ ነው የሚመጣው፡፡ አንድ ወይ ሁለት ቀን ቆይቶ… አንድ ወይ ሁለት ሳምንት በተከታታይ ይጠፋል፡፡ ሁለት ቀን ሲያድር ሁለት የተለያዩ ሴቶች ይዞ ይመጣል፡፡ አባቴ በህይወት ቢኖር ይሄ ሁሉ አይታሰብም፡፡ ግን አባቴ እያለ ቤቱ ይጨንቅ ነበር፡፡ አሁን ግን ቤቱ ይንኮሻኮሻል፡፡ የድሮው ፀጥታ በአጎቴ ላይ ብቻ ነው ሳይፈርስ የቀጠለው፡፡
እኔ አተም ነኝ፡፡ ማንም ላይ አልፈርድም። ሁሉም ሰው ጥሩ ይመስለኛል፡፡ ሁሉም ሰው መወደድ ይፈልጋል ብዬ አስባለሁኝ፡፡ አባቴም ጭምር፡፡
አባቴ የኖረው እና የሞተው ለእኛ ህይወት ዋስትና ለመስጠት ሲል ነው፡፡ እኛ እንደሱ ሳንጨናነቅ መኖር እንድንችል ብሎ ነው። … ዘና ብለናል በእርግጥ፡፡ አሁን ቤቱ አይጨንቅም፡፡ ስለ እኔ የወደፊት ህይወት በጣም ይጨነቅ የነበረው አባቴ ነው፡፡ ከእኔ ስኬት የሚገኘው ደስታ፣ ለእኔ ሳይሆን ለአባቴ አንገት ቀና ማድረጊያ፣ በኩራት በማህበረሰቡ መሃል ለመራመጃነት የሚውል በመሆኑ… ህልሙ የአባቴን ያህል አላጓጓኝም፡፡ አሁን ጉጉቱ ከእሱ ሞት ጋር አብሮ ተቀብሯል፡፡ እኔ ነፃ አተም ነኝ፡፡ እናቴም ነፃ ሰው ናት፡፡ … ቡናዋን በእየ አንድ ሰዐት ልዩነት እያፈላች… በልጅነቷ ከወጣችበት የገጠር መንደር ይዛ የመጣችውን ታሪክ እየደገመች… እየከለሰች ታወራለች፡፡ እጣኑን እየበተነች… ወሬዋን በአሰኛት ምዕራፍ ላይ ትቋጫለች፡፡
ተማምም… ያንኑ ስዕል እየደጋገመ ይስላል፡፡ ያንኑ መፅሐፍ እየደጋገመ ያነባል።  ፀጉሩን እያከከ… እናቴን እኩለ ቀን ላይ በሚጠይቀው ብር እንደ ልማዱ ይኑር። ደረጃውን ያልጠበቀውን ፍልስፍናውን መገባው መጠን ይፈላሰፍ፡፡
የቤተሰቦቼ ብቸኛ ልጅ ነኝ፡፡ ወንድም ወይንም እህት ስለሌለኝ አላዝንም። የማላውቀው ነገር አይናፍቀኝም፡፡ ሁሉም ሰው ይገባኛል፡፡ ከመጠን ያለፈ ግን እንዲገባኝ አልፈልግም፡፡ አባቴ ይሰብከኝ ነበር፡፡ የሚለኝን አስታውሳለሁ፤ ግን…አልሰበክም። እናቴ የምትለኝንም እሰማለሁ። “ላንተው ነው” ትለኛለች፡፡ እሰማታለሁ፡፡ ተማም የሚያወራውን የበለጠ እሰማለሁኝ፡፡ ግን አልሰበክም፡፡
እኔ አቶም ነኝ፡፡ ጴሬዲክ ቴብል ላይ ካሉ የአተም አይነቶች የትኛውን ነኝ ብዬ ብፈልግ…አይነቴን ላገኝ እችላለሁኝ፡፡ ምናልባት አሁን ባለኝ ጠባይ “ግሩፕ ዋን ኤ” ውስጥ ካሉት አተሞች አንዱ ልሆን እችላለሁኝ፡፡… በዚህ ግሩፕ ውስጥ ያሉ አተሞች መስጠት እንጂ መቀበል የማይወዱ ናቸው፡፡ ጠባያቸውም በቀላሉ አይለዋወጥም፡፡ ክብደታቸው አነስተኛ ነው፡፡
ጠባይ ነው ያለው አቶም፡፡ ግብ እና አላማው ከጠባዩ በመከተል የሚመጣ እንጂ ሰው ሰብኮት የሚላበሰው አይደለም፡፡
እና እኔም አተም ነኝ ጠባይ አለኝ። ጠባይ እና አጋጣሚ እና ሌሎች አተሞች የሚያሳድሩብኝ ተፅእኖ ቀጣዩን ህይወቴን አቅጣጫ ይወስናሉ። ፀሐይ በፈገግታዋ ቅጠል ታደርቃለች፡፡ ፀሐይም አተም ናት፡፡ የአተሞች ክምችት - እቶን።  ወደፊት ምን እንደምሆን አይታወቅም። መሆን ምችለውን ሳስብ ያስፈራኛል፡፡ ምድርን አቅልጬ ላፈሰው ወይንም በጥብጬ ልቀርፀው እችላለሁኝ፡፡ ወደ ላይም ወደታችም የከፍታም ሆነ የአዘቅት መጨረሻ የለውም፡፡ የተነሳሁበት ቤተሰቤ… አባቴ፣ እናቴ ፣ ተማም እና አጋር… መሃል ቤት ናቸው፡፡ በሃከለኛ መነሻዎቼ፡፡


Read 188 times