Print this page
Saturday, 18 August 2012 13:23

የሲኦል ህልም

Written by  ዮናስ ነማርያም
Rate this item
(2 votes)

የመጨረሻዋን መለኪያ እንጥፍጣፊ ሳላስቀር መጨለጤን አስታውሳለሁ፡፡ ግሮሰሪዋን ለቅቄ ወጣሁ - በእኩለ ሌሊት፡፡ እየተደነቃቀፍኩ… እየተደነባበርኩ በውድቅት ቤቴ ደረስኩ፡፡…ሶፋው ላይ ዘፍ! ብዬ ተቀመጥኩ፡፡ የቤቱ ዕቃዎች ውልብ! ውልብ! እያሉ ተሽከረከሩብኝ፡፡ አጥወለወለኝ፡፡ ሕሊናዬን እንደመሳት አደረገኝ፡፡ ልቤም ደቅ! ደቅደቅ! ብላ እንደመቆም ቃጣት ልበል፡፡ …ብቻ ወሰድ አደረገኝ፡፡ ጨርሶ እንኳን አልወሰደኝም… መለስ አደረገኝ፡፡ ለማንኛውም በሕይወትና በሞት መሀል መለስ ቀለስ እያልኩ ነው፡፡…ስለ ድንገተኛ ጥሪ በብዥታ… በደብዛዛው ትዝ አለኝ፡፡ በጠጪዎች አለም ‘ድንገተኛ ጥሪ’ የሚል ያልተጠበቀ ሕልፈት ያጋጥማል፡፡ ምሽቱን በሰላም ሲጠጣ የነበረ አጣጭ ጓድህ፣ መሰዋቱን በማግስቱ ልትሰማ ትችላለህ፡፡ በቅርብ የመጀመሪያ ዲግሪ የምረቃ ፕሮግራም ላይ እንድንገኝለት ሲወተውተኝ የነበረው… ወሬው ሁሉ ምረቃ! ምረቃ! ሆኖ ያሰለቸን የግሮሰሪ ባልደረባችን በድንገተኛ ጥሪ ሕይወቱ በማለፉ… በሐውልቱ ምረቃ ላይ ለመገኘት ተገደናል፡፡

…በሰመመን ስልት እየተፍገመገምኩ ወደ አልጋዬ ብራመድም የሕልም ዓለም ጉዞ ሆኖብኝ - ወለሉ ላይ በቁሜ ተዘረርኩ፡፡ …የነፍሴ ክር ጧ!! ብሎ ሲበጠስ ለእዝነ ሕሊናዬ ተሰማኝ፡፡ ክው ክልትው አልኩ፡፡ ሁሉም ነገር ድፍን አለብኝ፡፡ አከተምኩ፡፡ ከዚህ ዓለመ በሞት ተለየሁ ነው የሚባለው…

ጧት ስራ ባለመግባቴ አለቃዬ የስራ ስንብት ደብዳቤ ሲፅፍብኝ በሙት መንፈሴ ታየኝ፡፡ አንድም ቀን መቅረት ክልክል ነው፡፡ በድርጅቱ መተዳደሪያ ቁጥር 44 “በስራ ሰዓት ቀብር ላይ መገኘት ክልክል ነው፡፡ የግለሰቡ (የተቀጣፊው) የራሱ ስርዓተ ቀብር ካልሆነ በቀር…”

…ድንገተኛ ያልተጠበቀ ህልፈቴ ሳያንሰኝ ዕጣ ፈንታዬ ሲኦል ላይ ጣለኝ፡፡ በሰፊው አዳራሽ የተኮነንን ነፍሳት ታድመናል፡፡ ሳጥናኤል ስለ ገሀነም ገለፃ ሊሰጠን ትብያ ላይ ተዝረክርኮ ተቀምጧል፡፡ …”እንኳን ደህና መጣችሁ አይባል ነገር…” አለና ሰይጣናዊ መሰሪ ሳቁን ለቀቀው… “ሲኦል ወይንም ገሃነም በተለምዶ እንጦሮጦስ ይባላል፡፡ ግዕዙ ደግሞ መካነ ሀጢያን ይለዋል፡፡”

…ብሎ ጀመረ…

አቆመ…

አዳራሹ ፀጥ፤ ረጭ፤ ጭጭ፤ ጭልል አለ፡፡ ሳጥናኤል በዝምታ አጐነበሰ፡፡ ለካስ ያጐነበሰበት ቅፅበት የሲኦል ሰርጥ… የገሃነምን እንብርት የማፈላለግ ሂደት ነበር፡፡ ቀና ብሎም አንበለበለው - በእሳት ምላሱ፡፡ ስለዘላለማዊ አሳር፤ ፍዳ፡፡ በማሳረጊያውም “በቅርቡ ምደባ ይካሄዳል - ለጊዜው ወደ ጊዜያዊ ማረፊያችሁ” …ዓይናችን እያየ ስልብ አለ፡፡ ሰላቢ - ጥላቢስ፡፡

አንድ የአጋንንት ጭፍራ እኔንና ከጐኔ የነበረ ሌላ ሰው እንደ ሕፃን እጃችንን ይዞን ወጣ፡፡ አመድ አመድ ይሸታል፡፡ አንዲት ጠባብ ክፍል (cell) አስገብቶን በሩን ከርችሞት ተመለሰ፡፡

ከሰውዬው ጋር ፊት ለፊት ተፋጠጥን፡፡ ልብ ብዬ አስተዋልኩት፡፡ ፊቱ በተለያየ ቅርፅና መጠን ባላቸው ነጠብጣቦች ተዥጐርጉሮአል፡፡ ከጠፍጣፋ ግንባሩ ቁልቁል የተሰመሩ የተሸነታተሩ ጭረቶች ፊቱን የተጨናነቀ ከተማ የመንገድ ካርታ ገፅታ አላብሶታል፡፡

ከሰውዬው ጋር ጨዋታ ለመጀመር “ይዞን የመጣው ጋኔል አመድ አመድ አልሸተተህም?”

“አንተ ደግሞ ጋን! ጋን! ነው የምትሸተው - እሳት የሆነውን አልኮል ለብሰህ ወደ ሲኦል እሳት… ‘ቅለጥ ያለው ቅቤ ከእሳት ይጠጋል’ ትለኝ ነበር አክስቴ “አለና የመጠጥ ሽታ እንዳንገሸገሸው በሚመስል ስሜት ያንን የተሞነጫጨረ ፊቱን ቁጥርጥር ሲያደርገው የተወሳሰበ መረብ ገፅታ ተላብሶ - ጭራቅ ሆነና አረፈው… ሰውዬው ፊቱን አስሬ ይጠርገዋል፡፡ ፊቱ ከመጠረግ ብዛት ያልቅ ይሆን በሚል እየተብከነከንኩ በዝምታ አስተውለው ነበር፡፡ ምንም ለውጥ የለም፡፡ አዝማናት ይቆጠሩ ይቀመሩ አይታወቅም፡፡ ጊዜ ልጓሙን እንደበጠሰ ፈረስ ይጋልብ አልያም እንደ ሰሜናዊ ተራሮች ቀጥ ብሎ ይቁም አይታወቅም፡፡

…በሩ በኃይል ተንኳኳ፡፡ ብርክ ያዘኝ፡፡ “ሊወስዱን ነው - ጌታ ሆይ ምህረትህን…”

ሰውዬው በቁጣ “ድንቄም ምህረት! ‘በየገደላገደሉ መቀደስ በሰላም የተኛን ሰይጣን ለመቀስቀስ’ ትለኝ ነበረ አክስቴ፤ እናም ዝም በል” የንግግሩ መዝጊያ በአክስቱ ተረት መቋጨቱ ተደጋገመብኝ፡፡ …የተንኳኳው በር አልተከፈተም…

“በቅርቡ ምደባ ይካሄዳል?” አልሰማኝም

ደግሜ ጠየኩት… “የሳጥናኤል ምደባ መቼ ይካሄዳል?”

“ምን ምደባ! ምደባ! ትላለህ - በገነት ያለህ መሰለህ… በሲኦል ወጥመድ ውስጥ ነን… ለነገሩ ‘በወጥመድ የተያዘች አይጥ ህልሟ ብዙ ነው’ - ትለኝ ነበር አሮጊቷ አክስቴ”

እኚህ ምላሰኛ አክስት አሁን ደግሞ አሮጊት ሆነው ብቅ አሉ…

…”ትርጉም ያለው ሕይወት ኖሬአለሁ በለህ ታምናለህ?” የሚል ድፍን ያለ ጥያቄ ጠየቀኝ፡፡

“የሕይወት ትርጉም ምንድነው?” በሚል እብከነከን ነበር - በመሃል ግን “ሕይወት ትርጉም ኖራት/አልኖራት የራሷ ጉዳይ” በሚል እርግፍ አድርጌ ተውኩት… እንኳን ሕይወት ደመወዜ ትርጉመ ቤስ ሆኖብኝ ነበር… እንደ ፔን ኪለር ለሰዓታት ብቻ ነበር የሚያገለግለኝ - በደመወዝ ማግስት ወደ ብድር አዙሪት እገባለሁ”

“ግን ለምን? ሱሰኛ ነበርክ… ሱሳሱስህን ድል ለመንሳት ደመወዝህ በቂ አልነበረም?”

“…እቅም ነበር - ምርቃናዬን ለመስበር እጠጣለሁ - ምርቃናዬን ብቻ ሳይሆን ቅስሜን ሰብሬ በውድቅት እገባለሁ… በዚያ ላይ እንደ ሰንሰለት እርስ በርሳቸው በፅኑ በተቆራኙ ማለቂያ የሌለው ቤተሰብአዊ ችግር! …አያቴ ስቅ! ሲላቸው - እህቴን ያስነጥሳታል - አባቴ ላይ ደረቅ ሳል ይተክልበታል… ወንድሜ ልቤ ወረደ ብሎ ሲያቃስት… አክስቴ ሳንባዬ ተጐረደ… እናም ብር አምጣ - እኔኑ… የውቅያኖስ ዋናተኛ ሆኜ ነበር - ነፍሴም ማረፊያ ወደብ አጥታ…”

“እነሆ ገሃነም አረፈች” ሲል አሽሟጠጠና… “ምን ሃጥያት ብትሰራ ነው ነፍስህ የተኮነነችው?” የሚል መስቀለኛ ጥያቄ ወረወረብኝ…

“…አመነዝር ነበረ… በሀሰት እመሰክር ነበረ… እሰክር ነበረ… ነበር…ነበር…ብቻ አስሩንም የሙሴ ሕግጋት ተላልፌአለሁ፡፡”

“አስር ከአስር ደፍነህ ነዋ ሲኦል የወረድከው”

“ለእኔ ግን ዱብዕዳ ነው የሆነብኝ”

“መረጃው አልነበረህም… ቢያንስ በልጅነትህ ነፍስ አባታችሁ ስለገሃነም አላስጠነቀቁህም… ወይንስ የዳንቴን Divine comedy ላይ… The voice of damned rose in bestial moan…

…He examines each lost soul as it arrive…

…Decide which place in Hell shall be its end… የሚለውን አላነበብክምን”

“አላነበብኩትም” ኮምጨጭ ብዬ መለስኩለት

“በሥነጽሁፍ ረገድ ምንም የማታውቅ ድንግላዊ ነህን? …ለመጨረሻ ጊዜ ያነበብከው ጽሁፍ የማንን ነው?”

“የሌሊሳ ግርማ ‘የንፋስ ህልም’ መድብል ውስጥ ፎቦስ እና ዲሞስን… ስለመሰልቸት የተፃፈ ደብዳቤ መሰለኝ - ከገነት ወደ ምድር…”

“በተቃራኒው አንተ ከምድር ወደ ገሃነም የተጻፍክ ደብዳቤ” ሲል አላገጠና “ለነገሩ እኔም አንብቤዋለሁ… አንድ ሱሰኛ ገፀባህሪ ትዝ ይልሃል - ሃጢያቱ በፅድቅ ኩነኔ ሚዛን እየተመዘነ ሳለ፣ ከሲኦል የወጣ አይጥን የምታባርር ድመት ሚዛኑን ገለባብጣ… ፅድቅና ኩነኔው ተደበላልቀው በግርግር ገነት የገባ… አንተ ግን ገሃ…”

አላስጨረስኩትም “ምን አንተ! አንተ! ትለኛለህ… አንተስ ገሃነም ውስጥ…”

አቋረጠኝና “እዚህ ነኝ ብዬ አላምንም… እንኳን ከአንተ ጋር ከራሴ ጋር እንዳልሆንኩ አውቀዋለሁ፡፡ የትም እንደሌለው አምናለሁ… ዘላለማዊ ቤቴ በገነትም ሆነ በሲኦል ሳይሆን በውስጤ ነው - አለበለዚያ የትም የለም… አይኖርምም… መቼም… የትም… ከቶውንም”

“የለሁም… አልነበርኩም… ቅብጥርስዬ… በምድር ላይስ በሕይወት አልነበርክም?”

“በሕይወት አልከኝ… ህይወት በምድር ላይ ለሚታይ ታላቅ ትርኢት የመግቢያ ትኬት ናት… እናም መወለድ - ማደግ - መሞት… አስቀድሞ የመንገድ ካርታ ስለወጣላት ምድራዊ ሕይወት ማለትህ ነው?” መልሶ እኔኑ በጥያቄ አፋጠጠኝ፡፡

ምን ህይወት ብቻ የተሞነጫጨረው ፊትህ የመንገድ ካርታ ይመስላል አይባል ነገር… ዝም፡፡

“ስለ ህልፈቴ እንጫወታለን… ግን ጆሮ ጠቢ አለመኖሩን በበሩ ሽንቁር እይልኝ”

በበሩ ሽንቁር አይኖቼን ላኩኝ፡፡

“ምንም የሚታይ ነገር የለም - ከጨለማ አዘቅት በቀር”

“የጨለማ አዘቅት ስትል?” ሰውዬው የጥያቄ ቋት ነው፡፡

“ብርሃን ይሁን ከመባሉ በፊት የነበረውን ጨለማ ማለቴ ነው”

ሰውዬው የሕልፈት ታሪኩን መተረኩን ቀጠለ…

…”…ይቺን ምድር የተሰናበትኩት በጥይት ተመትቼ… ህይወቴ ከማለፉ 15 ደቂቃ በፊት በታክሲ ወደ መስሪያ ቤቴ እያመራሁ ነበረ - 3፡15 አለቃዬ ደወሉልኝ - ወቀሱኝ… ወደ ፒያሳ መቅረቤን፣ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥም እንደምደርስ ተንተፋተፍኩ… አስር ብር ቀድሜ ለወያላው ሰጥቼው ነበርና እንደወረድኩ መልሴን ጠየኩ… “የምን መልስ? አስር ብር አልሰጠኸኝም” ሲል ሽምጥጥ አድርጐ ካደኝ - አፍ እላፊ ሲናገረኝ ደህና ቡጢ አሳረፍኩበት…” አለና ዝም አለ፡፡ ከአፍታም በኋላ ትረካውን ቀጠለ…

“ወያላው በሌባ ጐማ ጭንቅላቴን በረቀሰው - ቁልቁል ሮጠ - ተከተልኩት - በካልቾ ልመታው እግሬን አወናጨፍኩ… አመለጠኝ… በወጉ ያልታሰረው ጫማዬ ወደላይ ጉኖ በግንብ የታጠረ ግቢ ውስጥ ገባ - እንደ አንካሳ ዶሮ እየተወለካከፍኩ ወደ በሩ ተጠጋሁ - ደጋግሜ ባንኳኳ ማን ይስማኝ… በሩን ገፋ ሳደርገው ተከፈተልኝ - በሰቀቀን እርምጃ ወደ ግቢው ገባሁ - ጫማዬ ላይ ልደርስ ሁለት እርምጃ ሲቀረኝ…”

“…ከውስጥ በተተኮሰ ጥይት ሕይወትህ አለፈ” ስል ደመደምኩ፡፡

“የኔን ህልፈት ለመስማት ምንድነው ጥድፊያው… አትቸኩል፤ መሞት አይቀር” ሲል ገሰፀልኝና

“…እ… ሁለት እርምጃ እንደቀረኝ በሩ በንፋስ ኃይል ድርግም አለ - ዞር ብዬ መለስ ባልኩበት ቅፅበት ወደል ውሻ ወደእኔ ሲወነጨፍ ወደበሩ ተፈተለኩ - በሩን ለመክፈት ታገልኩ - ተከርችሟል… ውሻው ዘሎ ጉብ አለብኝ… ከትከሻዬ ሙዳ ሥጋ የዘነጠለ መሰለኝ - ወደኋላ በደመነፍስ ተደናብሬ የቆመ አሮጌ የሕዝብ ሎንቺን ላይ በመሰላሉ ተንጠላጥዬ ፎርቶ መጋላው ላይ ጉብ አልኩ - ውሻው ከስር አርድ አንቀጥቅጥ ጩኸቱን ለቀቀው… አለቃዬ ደወሉ

”ከታክሲ አልወረድክም?”

“ወርጃለሁ..”.

“ታዲያ የት ነህ!” አንባረቁ

“ፎርቶ መጋላ ላይ”

አለቃዬ የማሾፍባቸው ስለመሰላቸው ከስራ መሰናበቴን በንዴት ገልፀው ስልካቸውን ዘጉ - ከስራ ከተሰናበትኩ ጥቂት ሰከንዶች በኋላ ከሕይወት መዝገብ ላይ የተሰናበትኩበት ጥይት ተተኮሰብኝ፡፡”

“ከዚያስ?”

“ምን ከዚያስ ትለኛለህ… ከሕያዋን ወደ ሙታን ዓለም ተዘዋውሬ እራሴን ከአንድ ሰካራም ጐን አገኘሁት (ውድ አንባቢያን እኔኑ ነው) ‘ምን ለብሼ ልሳቅ’ አለች አክስቴ “አለና ከት ብሎ ሳቀብኝ፡፡ ሳቁ ከጤነኛ ሰው ለየት ያለ መሰለኝ፡፡ የእብድም ዓይነት ሆነብኝ፡፡ አክስቱም የምትስቅብኝ መሰለኝ

“የነፍሳችን ክር በመጠጥም ሆነ በጥይት ተበጠሰ… አረቄ! አረቄ! ሸተትንም… ባሩድ ባሩድ!... ፍፃሜአችን ሲኦል ሆኖአል ለዘለአ…”

አላስጨረሰኝም “…ዝጋ! ከአሁን በኋላ በእኔ ፊት ስለገሃነም ትንፍሽ እንዳትል፡፡ እንድያውም በመሃከላችን ንግግር አይኖርም - እያንዳንዱ ከዕጣ ፈንታው ጋር የራሱን ጥግ መያዝ አለበት… እንደ እሳትና ጭድ ተራርቀን መቀመጥ አለብን - “ቅቤ እራስ ከሆንክ ዳቦ ጋጋሪ አትሁን” …”ከአፉ ለቀም አድርጌ” ይሉህ ነበረ አክስትህ

“አክስቴን ታውቃታለህ እንዴ?” ሲል አፈጠጠብኝ

“በአካል ባላውቃቸውም ነፍሳቸው ተኮንና የአንተን ሥጋ ለብሳ እነሆ በሲኦል እየተረቱ ነው… “ምን ለብሼ ልሳቅ” በሚልም በእኔው ላይ እየተሳለቁ ነው - ሾካካ ምላሳም አሮጊት!”

ፊቱ ልውጥውጥ አለ፡፡ ገፁ ላይ የተሰመሩ የተሸነታተሩ ጭረቶች ዚግዛግ መቱ ልበል፡፡

“አክስቴን ሾካካ ምላሳም - አንተ የጊንጥ ልጅ!!” አለና በዚያ ጥፍጥፍ እጁ በቃሪያ ጥፊ! አጠናበረኝ… ያ! እንደነጐድጓድ የወረደብኝ መብረቃዊ ጥፊ! ከገባሁበት የገሃነም ህልም ስቃይ አባኖ አነቃኝ፡፡…

 

 

Read 4529 times Last modified on Saturday, 18 August 2012 14:01