Monday, 29 March 2021 00:00

«ተቃርኖ»

Written by  አፀደ ኪዳኔ (ቶማስ)
Rate this item
(1 Vote)

   መልዕክተ ይሁዳ
ፀፀት በጥፍራም እጆቹ ነፍስያዬን ሲቧጥጥ ይሰማኛል። ይህም ጉዳይ ከመኖር በላይ፣ ከእምነትም የላቀ እውነት እንደሆነ ልቤ ይነግረኛል። እውነታችሁ ነገሮችን በምታዩበት ብርሃን ይደር። የሃቃችሁን ፈረስ የእናንተ ነውና ልጓሙን ይዛችሁ ወደ አሻችሁ ቦታ ጋልቡት። ልገልፅላችሁ የምሻው ጥቂት እውነት ግን አለኝ። ከአይኔ የሚፈስ እንባ ሳያግደኝ፣ ልቤ ላይ የተሰካው የፀፀት ጦር ሳይበግረኝ፣ ሁሉንም እንዲህ ልንገራችሁ።
ኢየሱስን የተዋወቅኩት ዕለት ፀሃይ ደምቃ ወጥታ ነበር። ከፊቱ ላይ አንዳች ፀዳል እየተነሳ ሽቅብ ይነጉዳል። ቀጥ ብሎ የወረደ አፍንጫ አለው። ዓይኖቹ መሃከለኛ፣ ነገር ግን ሁናቴዎችን በትኩረት የሚመለከቱ ብልጣ ብልጥ ናቸው። ቢሆንም ይሄን ገፅታ ትቼ የዋህ በሚያስመስለው ሰፊ ግንባሩ ላይ ዓይኖቼን ተከልኩ። ከአፉ የሚወጡት ቃላት እንደ ማር ይጣፍጣሉ። በዚህም ቅን ልቤ ወደደው። እውነተኛ ንጉሳችን ይሄ ነው ብዬ ለራሴ ተናገርኩ። ህይወቴን ልሰጠው ፣ ነፍሴን ልሰዋለት ቃል ገባሁ። ያለኝን ሁሉ በደስታ ልሰጠው ፈለግሁ። ሁሉንም ነገሬን፣ ሁሉንም ሃብት ንብረቴን። ይሄን ሰው መከተል እንዳለብኝ አመንኩ። ይህንንም ለእናቴ ነገርኳት።
“እሱን አምነህ መሄድህ ልክ አይደለም” አለችኝ። ቀጥላም “አሁን ወደድኩት የምትለኝ ኢየሱስ አንገትህ ላይ የሞት ዲንጋይ ከማንጠልጠል የተረፈ ነገር አይሰጥህምና እኔ እናትህን ጥለህ አትሂድ “ አለችኝ። እናቶች ሁሉ የልጃቸው እጣ ፈንታ የሚታያቸው ነቢይ ቢሆኑም፤ በሰዓቱ ላምናት አልቻልኩም። እናቴ የዚህን መሲህ ገድል ታካኪስ ነበር። አምርራም የሚታየኝ የፅልመቱ ክፋይ እንጂ ፀዳሉ አይደለም ትላለች። በዚህም ንግግሯ አዘንኩ። ማንን የዚህን ያህል ወድጄ ነበር? ማንንስ ህይወቴን ልሰጠው ቃል ገባሁለት? ከኢየሱስና ከእናቴ በቀር አንዲትም ፍቅር ለሌላ አካል ሰጥቼ ባውቅ ለሃገሬና ለህዝቦቼ ነበር። ስወደው በንፁህ ልቤ ነው። ሳፈቅረው ላገለግለው ቃል እየገባሁ ነው። ይሄን የልቤን ንፅህና ከእግዚአብሔር በቀር ማን ሊያውቅ ይችላል? ምናልባት ኢየሱስ ያውቃል።
“ይሁዳ” አለኝ፣ አንድ ዕለት።
“ሁሉንም ነገር ጥለህ ልትከተለኝ ትፈቅዳለህን” ብሎ፣ ጠየቀኝ።
“አዎ! አንተ ንጉሳችን ነህና። በትዕዛዝህም ልኖር ቃል እገባለሁ” አልኩት።
ከልቤ ንፁህነት በመነጨ አምኜዋለሁ። አገራችንን እንደሚለውጣት፣ እንደሚነግስባትም ተማምኜ ነበር። ሁሉም ነገሮች ደስ ያሰኙ ነበር። ሁሉም ነገሮች የተቀደሱ ይመስላሉ። ሁሉም ነገሮች የኢየሱስን ንፅህናና አምላክነት የሚገልፁ ነበሩ። እምነቴን በኢየሱስ ላይ ጣልኩ። እናቴንም ጥዬ እሱን ልከተለው ወሰንኩ። በዚህም እናቴ ቅር አላት። ተዉ አለችኝ፣ “አይሆንህምና ልጄ ይሁዳ ሆይ ስማኝ” እሷን የምሰማበት ጆሮ አልበረኝም። ምክንያቱም መላው አካሌ በዚህ ሰው ተደፍኗልና። ምክንያቱም አገሬን ከትልቅ ማማው ላይ ያደርሳል ብዬ ያመንኩት ኢየሱስን ነበር። ህዝቦቼን ከባርነት የሚያወጣ እሱ ኢየሱስ ነበር። ለሃገሬና ለህዝቦቼ ትልቅ ፍቅር አለኝ። ሰው ያለ አገር ምንድነው? ሰው ያለ ህዝብ ማን ነው? ድንቁርና እንደሚመራቸው እንስሳት አይደለምን? እውነቴ በጊዜ ጀምበር እንደማትጠልቅ ተማምኜ ነበር። በአቁማዳዬ ውስጥ ያለ ሃቅ ኢየሱስን እንድከተለው ይመራኝ ነበር። ተከተልኩትም። በሄደበት ሁሉ ሄድኩ። በዞረበትም ቦታ ሁሉ ዞርኩ። ኢየሱስም የእውነት አምላክ ነበር። ከአፉ የሚወጡት ትምህርቶች እንዴት ደስ ይሉ ነበር። ሲያቅፈኝ ፍፁም ወንድምነት በሚገልፅ ፍቅር ነው። አጠገቡ እንድሆን ሲያደርገኝ ለእኔ ካለው ላቅ ያለ ፍቅር እንደሆነ አሁን ድረስ አምናለሁ። በዚህም ያለ አንዳች ፍራቻ ተከተልኩት። እናቴን ችላ ብዬ ከእሱ ጋር መዋል ጀመርኩ። ተአምራቱን ሁሉ አየሁ። በፍቅሩም ከተማ ተመላለስኩ። በትህትናው መስክ አደርኩ። “ከእንግዲህ ማን ያሰፈራኛል” ስል ለራሴ ዘመርኩ። የእምነቴም ፅላሎት እሱ እየሱስ ላይ ተጥሏል። በፍቅር እጆቹም ባረከኝ። በእቅፉ አኖረኝ። በእርግጥም ኢየሱስ እንደሚነግስ ፣ ዓለምን እንደሚገዛ አሰብኩ። ከእሱ የላቀ ማን አለ? ስል እራሴን ጠየኩ። በዚያ በከፋ ዘመን የምጠለልበት ጥግ ሆነኝ።
ሁሉም ነገሮች ደስ በሚል መንገድ የሄዱ መሰሉ።
አንድ ዕለት ቁጭ ብለን ስንጨዋወት አንድ ጥያቄ አነሳሁለት። እምነቴ በእሱ ላይ እንዳለ እንዲያውቅ። እናቴን ጥዬ መከተሌም በምክንያት እንደሆነ እንዲረዳ .... ጊዜው ሞቃታማ ነው። ወፎች ትልቅ የዋርካ ዛፍ ላይ ሆነው ይዘምራሉ። ኢየሱስን ከበን ተቀምጠናል።
“የአለም መንግስታት ሰፊ ናቸው። የዳዊት ከተሞች በሮማውያን ድል ይቀዳጃሉ። አንተ የአይሁድ ንጉስ ስትሆን እኛም ጦርና ጋሻ ይዘን ከጎንህ እንቆማለን። ባዕዳንንም እናባርራለን” አልኩት።
ኢየሱስም በቁም በተሞላ ዓይን አየኝ። ከዚያም እንደ መብረቅ በሚያስገመግም ድምፅ:- “ዞር በል ከፊቴ አንተ ሰይጣን። ይህን ሁሉ ዓመት አልፌ የመጣሁት የምስጥ ኩይሳ ለአንዲት ቀን ልገዛ ይመስልሃል?”² ብሎኝ አፈጠጠብኝ።
ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ነገሮችን በደንብ ማገናዘብና ማየት ጀመርኩ። ከኢየሱስ ጀርባ ስላሉት ነገሮች ይበልጥ አሰላሰልኩ። ቁጥብ፣ ተቆጪ ሆንኩ። ሁሉም ተሰባስበው ሲሄዱ ብቻዬን ሆኜ ቆዘምኩ። በእውነቱ ይህቺ ሃገር ከሮማውያን ባርነት የሚያወጣትን ንጉስ ትሻለች። ይሄን ንጉስ ኢየሱስ እንደሆነ ተማምኜ ነበር። አሁን የእሱ መንግስት ይሄ የሚታየው ጉሁድ ዓለም እንዳልሆነ... ሌላ የማትታይ፣ የማትጨበት መንግስት እንዳለችውና እዚህች ምድር ላይም ለመንገስ እንዳልመጣ ነገረኝ። ይሄም በልቤ ውስጥ የተሰነቀረ ትልቅ ጦር ሆነ። ቀን ከሌት ስለ ሃገሬ ማሰብ ጀመርኩ። ስለ ህዝቦቿ አሰብኩ። ከዚህ አስከፊ ህይወት የሚያወጣቸው ንጉስ ለመፈለግ ቆረጥኩ። ቢሆንም ይሄን ሊያሟላ የምችል ከኢየሱስ በቀር ማንም የለም። በዚህም ግማሽ ሆዴ እየሱስን ተቀየመው። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ያ የምወደው ኢየሱስ እና እኔ ሆድና ጀርባ ሆንን። የሚያስተምራቸው ትምህርቶች ጠቅላላ ስሜት የማይሰጡ ፣ ግራ የተጋባ የአንድ ፈላስፋ ድምፅ መሰሉኝ። ቅድሚያ በፍቅር የማየው አስተምህሮት እንደ ዝሆን ሀሞት ይመረኝ ጀመር። ይሄንንም ለማንም አልተናገርኩም። ሁሉንም ነገር በሆዴ ያዝኩ።
ሁሉም ነገሮች እንዳበቁ ይገለፅልኝ ነበር። ያ ያመንኩት ተስፋ እኔኑ ይዞኝ እንደጠፋ፣ ይሄም የጠፋ ተስፋዬ የእሳት ላንቃ ሆኖ ጅስሜን እንደሚያነድ አየሁ። እምነት ያልኩት ሲከዳኝ፣ እውነት ያልኩት ሲታጠፍ በእርግጥም እውነቶች ሁሉ እውነት እንዳልሆኑ ተረዳሁ። ሁሉም ሰው እውነቴ የሚልዉ ጊዜ የሚሽረው ቅጥፈት ነው። ሁሉም ወደ እራሱ ሲመለስ በኑፋቄ አየር ይበከላል። በሃሰት ጥላ ስርም ይውላል። ስለዚህም ነገር እርግጠኛ ሆኜ መናገር አለብኝ። እምነት የሚባል ቅጥፈት እንደሌለ ልነግራችሁ እወዳለሁ። ፀንቶ በሁለት እግሩ የሚሄድ እምነት ምድር ላይ የለም። ሁሉም እምነቶች በክህደት ይለወጣሉ። በዋሾነት ይቀጠፋሉ። የእኔም እምነት እንደ ሽማግሌ ጡንቻ ሟሸሸ። እንደ ተበላሸ እንቁላል ገነማ። እንደ ጥንብ ሸተተ። ይሄንን በትዕግስት ቆሜ ተመለከትኩ።
ጊዜ እያለፈ ሲመጣ ፍፁም በሚባል ደረጃ ከኢየሱስ ጋር ተራራቅሁ። ስለ እኔም ሲያነሳ “ አመፀኛና እልህኛ ነው” ማለቱን ሰማሁ። ይህ ፍፁም ውሽት ነበር። እንደ አምላኬ ከማየው ኢየሱስ የማይጠበቅ ውሽት ነው። በዚህም ብዙ አልተናደድኩም። ስህተቱ የእኔ እንደሆነ ገባኝ። ለእየሱስ ከፍ ያለ ቦታ መስጠቴን አውቅኩ። ያም በሱ ድርጊቶች እንድከፋና ከጠበኩት በታች እንዳስበው አደረገኝ። ሰዉን ሁሉ የሚሳስት ወንጀለኛ ሆኖ ታየኝ። እውነት እውነት እላችዃለው ኢየሱስን ጥቂት ተቀየምኩት። ያም ሆኖ ብዙ ነገሮች አለፉ። ቅር እንዳለው ልቤም ብዙ ሰነበተ። አንድ ከመንገድ ቆሞ ያገኘሁት ሰውም ስለ ኢየሱስ ጠላቶች እንዶህ ሲል ነገረኝ:
“ ፈሪሳዊያን እያሳደዱት ነው። በሰንበት ፈውሷል። በሰንበት አድኗል ይላሉ። ህጋቸውን መቀለጃ እንዳደረገ፣ በማይገባ ምሳሌ እንደተሳለቀባቸው ይናገሩ ነበር። ይህን ኢየሱስ ለፍርድ እናቅርበው እያሉም ሊይዙት እንደሚፈልጉ ሰማሁ። ላገኘላቸውም ሰው ገንዘብ እንደሚከፍሉ ይናገሩ ነበር።”
“እኔ እኮ ላገኝላቸው እችላለሁ” አልኩት። በእርግጥ ይሄ ቃል ከአፌ ስለመውጣቱ እርግጠኛ አይደለሁም። ማለት የፈለኩት በእርግጥም ኢየሱስ ወንጀለኛ እንደሆነ ነበር። “አዎ! መያዝ ይገባዋል፣ መታሰር ይገባዋል” ይል ነበር ውስጤ የተዳፈነው እሳት። ከሰውየው ጋር በተወሰነ መንገድ ተግባባን። የሚከፍሉትም ክፍያ ጥሩ እንደሆነና እሱ ሊያገናኘኝ እንደሚችል ገለፀለኝ።
እውነት ኢየሱስ ይሄ ይገባዋል? ስል እራሴን ጠየኩ። ታዲያ ከአፌ የወጣው “አዎ ይገባዋል” የሚለው ሃረግ ነው። በጥልቀትም ለማሰላሰል ሞከርኩ። ይሄ የምሰራው ስራ በእርግጥ ልክ ነበር። ኢየሱስ ይህቺን ሃገር ካልተረከባት፣ የአይሁድ ንጉስ ሆኖ ህዝቦቹን ከባርነት ካላወጣ የእሱ ሃያልነት ምኑ ላይ ነው? የእሱ አምላክነት መች ህዝቦቹን ከስቃይ ገላገለ? አገሩን ከጠላት አዳነ? መች? መች ጠቀመን ? አምላክነቱን የማየው እንደ ሰማይ ላም ነው።
ከነዚህ ጠላቶቹ ጋር ስገናኝ በስሜት ሆነው ኢየሱስን ይረግሙ ነበር። ኃጢያት የሚሉት ሁሉ ዘርዝረው በጣሙን ይበሳጩ ነበር። ይሄንንም በአይኔ አይቻለሁ። ኢየሱስ ብልህ አስተማሪ እንደነበር ግን መመስከር ነበረብኝ። አዎ! አስተምህሮቶቹ ከሆነ ጊዜ በዃላ ባይጥሙኝ በፊት በፊት ዓይኖቼ በእንባ እስኪሞሉ ድረስ እሰማው ነበር። ልቤ በፍቅር ማይ እስኪረሰርስ እሰማው ነበር። ይሄን ትምህርት ዓይኖቼ እንዳያዩ፣ ጆሮዎቼም ሰምተው እንዳይሰሙ፣ አዕምሮዬም ነገሮች በትክክል እንዳይረዳ የሚያደርግ ተዓምር ነበር። ሁሉም በተመስጦ ይሰሙታል። እኔ ግን ከዚህ ተዓምር ልወጣ ችያለሁ።
ከጠላቶቹ ጋር ሰላስ ዲናር ሊከፍሉኝ ተስማማን ። እኔ ግን የገንዘቡ ጉዳይ ምኔም አይደለም። ሰዎችን ስለሚያስት፣ በትምህርቶቹ አዕምሮን ስለሚፈዝ፣ ዐይኖችን ስለሚያውር ከዚህ ድርጊቱ ይታቀብ ዘንድ ብቻም ሳይሆን ዋናው ጉዳይ ህዝቦቼን ሊታደግ አለመቻሉ ላይ ነው። ስለ መንግስት የሚያወራው እኛ የምናየውን፣ የምንጨብጠዉን መንግስት ሳይሆን ሰማይ ላይ ስለተሰቀለው መንግስት ነው። ታዲያ ይህ ላም አለኝ በስማይ አይነት ጨዋታ አይደለምን? እስቲ ፍረዱ እኔ ያነሳሁት ጉዳይ ተጨባጭ አይደለም? እሱ የአይሁድ ንጉስ ማድረግ፣ ለንግስናው እኛ ዘብ መቆም አይገባንም። ከእሱ የተሻለ ንጉስ ማን ይመጣል? ከእሱ የሚልቅስ ማን ነው?
! ልሸጠው ነው። ይሄ ድርጊቴ ፀፀት ያስከትልብኝ አያስከትልብኝ የማውቀው ነገር አልነበረም። የማውቀው አንድ ነገር አለ - እሱም ጠላቶቹ ኢየሱስን በጥብቅ እንደሚፈልጉት ነው። ስለዚህ መፍጠን ይኖርብኛል ። አንዴ ከያዙት በዃላ የእኔ ስራ ይጠናቀቃል። ገንዘቡን ልጠቀምበት አልሻም። ለአንድ የተቸገረ ሃሚና እሰጠዋለሁ እንጂ እኔ በፍፁም ከዚያ ገንዘብ ላይ አልነካም። በእርግጥ ኢየሱስ የት እንዳለ ለማወቅ አልተቸገርኩም። ምክንያቱም ሰው ሁሉ የሚያወራው ስለ እሱ ነበር። ስሙ በሃገሪቷ ውስጥ ናኝቷል። ብዙ ሰው ይከተለዋል። የታመመ ፈውስ ፍለጋ ይከተለዋል። ያመኑት ገንዘባቸውን ንቀው - ሚስት - ልጆቻዉ ትተው ይከተሉታል።
ጉንጩን ስሜ አሳልፌ ሰጠሁት። ከሰው መሃል ለይቼ አሳልፌ ሰጠሁት። እነሱም ሊያሰቃዩትና ሊገድሉት ወደ ጨለማ ቦታ ወስዱት። ይሄኔ ጀርባዉን አይቼ በጣም አዘንኩ። ልክ ያለመሆን እውነቶች ሲከተሉኝ እንደኖሩ ሁሉ አሁንም ትላንቴ ስህተት እንደሆነ ፀፀቴ አረዳኝ። ይሄም ፀፀት ወደ ’ማልነቃበት ጥልቅ እንቅልፍ ይወስደኛል።

Read 239 times