Saturday, 03 April 2021 18:12

ዳሸን ቢራ ለገበታ ለሀገር ፕሮጀክት 25 ሚ. ብር አበረከተ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 ባለፉት 20 ዓመታት ለማህበራዊ ሃላፊነት 600 ሚ.ብር ወጪ አድርጓል
              
            ዳሸን ቢራ ፋብሪካ በአማራ ክልል ጎርጎራ፣ በኦሮሚያ ወንጪ እንዲሁም በደቡብ ኮይሻ ለሚገነቡት ፕሮጀክቶች የ25 ሚ. ብር ድጋፍ አድርጓል። ፋብሪካው ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ላይ በቤስት ዌስተርን ፕላስ ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ ላይመግለጫ እንዳስታወቀው፤ ባለፉት 20 ዓመታት በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በመሰረተ ልማት ዝርጋታ፣ በትምህርት ተቋማት ግንባታ፣ በስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታ፣ በስፖርት ክለቦች ድጋፍ፣ በባህል ማዕከላት ግንባታ፣ በቢራ ገብስ አምራች አርሶ አደሮች ድጋፍ፣ በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ አደጋዎች ድጋፍ ፣በአረጋዊያን መጠለያ ግንባታ ድጋፍ፣ በትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም ድጋፍ፣ በቱሪዝም ዘርፍ እድገትና በሌሎችም የማህበራዊ ጉዳይ የድጋፍ ስራዎች በአጠቃላይም ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ማህበራዊ ሃላፊነቱን ሲወጣ መቆቱን ተገልጿል።
ፋብሪካው ከመጠነ ሰፊ ማህበራዊ ድጋፍ ባሻገር በየደረጃው ለሚገኙ የመንግስት ግብር ሰብሳቢ ተቋማት በየጊዜው ህጉ የሚጠይቀውን የግብር ክፍያ ሳይሸራርፍና በታማኝነት በመክፈል በጎ ስም ያፈራ መሆኑን የገለጹት ሃላፊዎቹ፣ ከታማኝነቱም ባሻገር በየዓመቱ መጠኑ ከፍተኛ የሆነ ግብር በመክፈልም ጭምር በሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ላይ የራሱን አስተዋፅኦ እያደረገ እንደሚገኝም ተገልጿል።
ዳሸን ቢራ ፋብሪካ በ2012  የበጀት ዓመት በአጠቃላይም  እንደተለመደው ለመንግስት ከፍተኛ ግብር ከከፈሉና ታማኝ ከሆኑ ጥቂት የንግድ ተቋማት ዝርዝር ውስጥ በመግባት የወርቅ ተሸላሚ መሆን መቻሉ ለታማኝነቱና በአገር ኢኮኖሚ ላይ እያደረገ ላለው ወደፊትም ለሚያደርገው አስተዋፅኦ ምስክር ነው ብለዋል ሃላፊዎቹ።
በአዲስ አበባ ከተማ የአንድነት ፓርክን ጨምሮ በሌሎች ፓርኮች በመንግስት ሃሳብ አመንጪነት የሀገር ገጽታ፤ በማስዋብ የታየውን ግንባታ ወደ ክልሎች በማስፋት ለታቀደው የጎርጎራ፣ ወንጪና ኮይሻ ልማት ዳሸን ቢራ ፋብሪካ 25 ሚ.ብር በመለገሱ ኩራት እንደሚሰማውና የታሪኩ አካል በመሆኑ እንደሚደሰት ገልጸዋል።
ፋብሪካው እንደ አንድ ግዙፍ የንግድ ተቋም ህልውናው በህዝብ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ወደፊትም ህዝቡን ይጠቅማሉ፣ ለሀገር ልማት ያግዛሉ በሚባሉ ጉዳዮችም ላይ አቅም በፈቀደ መጠን ሃፊነቱን ለመወጣት ወደኋላ እንደማይልም አስታውቋል።


Read 1019 times