Saturday, 03 April 2021 18:19

በንፁሀን ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች ሊቆሙ ይገባል ተባለ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

 - ጥቃቶቹ ከመንግስት አቅም በላይ ሳይሆን ሆን ተብለው የሚፈፀሙ ናቸው
        - ኦነግ ሸኔ በሚል ስም የተደራጀ ቡድን የለም
        - የሚፈፀሙ ጥቃቶች ሁሉ በኦነግ ሸኔ ስም ማሳበቡ ተገቢ አይደለም
               
            ሰሞኑን በምዕራብ ወለጋ የተከሰተውን ጥቃትና የንፁሃን ሞት ተከትሎ በንፁሀን ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችሊቆሙ እንደሚገባና መንግስት ንጹሃንን ከሞት እንዲታደግ ተጠየቀ። የአብን ሊቀመንበር አቶ በለጠ ሞላ ለአዲስ አድማስ በሰጡት አስተያየት በተለይም በምዕራብ ወለጋ በተደጋጋሚ በአማራ ተወላጅ ንፁሃን ዜጎች ላይ የሚፈጸመው ግድያ ከመንግስት አቅም በላይ እንዳልሆነና በኦሮሚያ ብልፅግና አመራር መዋቅር ውስጥ ይህን ድርጊት የሚደግፍ አካል በመኖሩ ግድያና ጥቃቱን ማስቆም አልተቻለም ብለዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንቱ  ጨምሮ በተዋረድ ያሉ አመራሮች በየአደባባዩ የሚያስተላልፏቸው ሃላፊነት የጎደላቸው ንግግሮችና ጸረ አማራ በሆነው ህገ-መንግስት ውስጥ ያሉ አንቀጾች ለአማራ ንፁሃን መገደልና ጥቃት ምክንያቶች ናቸው ብለዋል።
የኦነግ አዲሱ ም/ሊቀመንበር አቶ ቀጀላ መርዳሳ በበኩላቸው የንጹሃንን ግድያ ከዘርና ከማንነት ጋር ማያያዝ አገርን ለከፋ ችግርና ቀውስ የሚከት ጉዳይ ነው ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በመላ አገሪቱ እየተፈፀመ ያለውን ግድያና ጥቃት በኦነግ ሸኔ ማሳበብ ተገቢ አይደለም ያሉት አቶ ቀጄላ “እኔ እንደውም ኦነግ ሸኔ በሚል ስም ተደራጅቶ የሚንቀሳቀስ ሃይል አላውቅም ብለዋል፡፤
ህግን የማስከበር ሃላፊነት ያለበት መንግስት ጉዳዩን ከስር መሰረቱ  ፈትሾና አጣርቶ አጥፊዎችን ለህግ ማቅረብ አለበትም ሲሉ አሳስበዋል አቶ ቀጄላ።
የህግ ባለሙያው አቶ ሞላልኝ መለሰ በበኩላቸው በምዕራብ ወለጋ በተደጋጋሚ ሚፈጸመው ጥቃትና ግድያ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ባሉ አመራሮች የሚደገፍ ስለመሆኑ ጥርጣሬ እዳላቸው ገልጸው ይሄ ባይኖር ኖሮ ከመንግስት አቅም በላይ የሚሆን ነገር ሊኖር አይችልም ባይ ናቸው።
መንግስት በተደጋጋሚ የሚፈጸሙትን ጥቃቶች ሳይመረምርና ምርመራ ውጤቱ ሳይታወቅ ኦነግ ሸኔ ነው ድርጊቱን የፈጸመው እያሉ መፈረጅ ከተጠያቂነት ማምለጫ ስለሆነ የተሳሳተ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
እንደ ህግ ባለሙያው ገለጻ ለተደጋጋሚ ጥቃቱና ግድያው መልስ የሚሰጠው፤ ማነው ድርጊቱን የሚፈጽመው? ለምንድን ነው ተይዞ ለህግ የማይቀርበው? የሚለው ጥያቄ ምላሽ ሲያገኝ ነው ብለዋል። መንግስት ጥቃት ፈጻሚዎቹን በቁጥጥር ስር አውሎ ለህግ ማቅረብ እንዳለበትም ተናግረዋል።

Read 10542 times