Print this page
Saturday, 03 April 2021 18:41

ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ - ከአብን ሊቀመንበር ጋር

Written by 
Rate this item
(0 votes)

• በ1997 ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በፍልስፍና የመጀመሪያ ዲግሪ
    • በ1998/99 በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር፤
    • በ2000 መጨረሻ ላይ የአውሮፓ ኢኮኖሚ ኮሚሽን በሚሰጠው የራመስ ምንደስ ስኮላርሺፕ፣ በኖርዌይና ስዊድን በApplied Ethics ልዩ ዘርፍ 2ኛ   ዲግሪ፤
    • በ2005 ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በፍልስፍና 2ኛ ዲግሪ፤
    • ከወራት በኋላ በሚመረቅበት (አሁን በጥናትና ምርምር ላይ) በፍልስፍና 3ኛ ዲግሪውን እየሰራ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ  (አብን)ን በሊቀ መንበርነት እየመራ ይገኛል፡፡

             ቴዎድሮስ፡- የአማራ ንቅናቄን (አብን) መቼ ነው የተቀላቀልከው?
አቶ በለጠ፡- አብንን ከመሰረቱት ውስጥ አንዱ ነኝ፡፡ በ2010 ዓ.ም የመጀመሪያ ወራት አካባቢ (ለውጡ ከመምጣቱ በፊት) የህቡዕ  እንቅስቃሴ እናድርግ ነበር፡፡ በወቅቱ በፖለቲካው መድረክ ላይ የአማራው ወኪል የፖለቲካ ድርጅት ስላልነበረና በአማራም ሆነ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የተጫነው አምባገነናዊ ስርዓት መውደቅ አለበት ብለን ስለምናምን፣ አንዳንድ ጓደኛሞች ተገናኝተን እንነጋገር ነበር፡፡ በወቅቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስለነበረም፣ በግልጽ ተገናኝቶ ሰብሰብ ብሎ ለመወያየት የሚያስችሉ ሁኔታዎች ስለነበሩ፣ በየካፌው 5/6 ሆነን እየተገናኘን እንነጋገራለን፡፡ የደህንነት ሰዎች ይከታተሉናል፡፡ ቤት ውስጥ እንገናኛለን፡፡ እኔ ቤት ውስጥ 5 ስብሰባዎች አድርገናል፡፡
መጨረሻ ላይ በግልጽ የምንወያይበት ሰፋ ያለ ቦታ ስላልነበረ ማንንም ላለመረበሽ (መንግስትንም  ጭምር) ቦታ ፍለጋ ባህርዳር ጣና ላይ ሔደን ከደሴ፣ከደብረ ታቦር፣ ከባሕርዳር፣ ከአዲስ አበባም ተገናኝተን፤ አብንን የመመስረቻ የምክክር ስብሰባ፣ ጣና ሀይቅ ጀልባ ላይ  ስናደርግ  “የአስቸኴይ ጊዜ አዋጁን ጥሳችኋል” ተብለን ለ2 ሳምንት አስረውናል፡፡ ማሰር ብቻ ሳይሆን ደብድበውናል፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ንግግር ሲያደርጉ፣ እዚያው እስር ቤት ሆነን ነው ያዳመጥናቸው፡፡ እንግዲህ ከዚያን ጊዜ ወዲህ በአብን ውስጥ ግንባር ቀደም ተሳታፊና አሁን ደግሞ ሊቀ መንበር ሆኜ በማገልገል እገኛለሁ፡፡ አብን ሰኔ 2 እና 3 ቀን 2010 ዓ.ም በባህር ዳር ሙሉ ዓለም አዳራሽ በተደረገው ጉባኤ ነው በይፋ የተመሰረተው፡፡ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህጋዊ የእውቅና ምስክር ወረቀት ያገኘው ደግሞ በታህሳስ /2011 ዓ.ም ነው፡፡
ቴዎድሮስ፡- አብንን በንቅናቄ ቅርፅ ለመመስረት ለምን ፈለጋችሁ? ለምን ፓርቲ አላደረጋችሁትም?
አቶ በለጠ፡- የአማራ ሕዝብ ሁለንተናዊ መገፋት ደርሶበታል ብለን ነው የምናመንው። ላለፉት 30 ዓመታት በርካታ ገጽታዎች ያሉት መገፋት ደርሶበታል፡፡ ወደ ፓርቲ ከመሄዳችን በፊት አጠቃላይ ሕዝባዊ ንቅናቄ መፍጠር ነበረብን፡፡ ህዝቡ በኢትዮጵያዊነት እሳቤ ውስጥ የሚኖር በመሆኑ፣ በአማራነቱ እየደረሰበት ያለውን ጉዳት በአማራነቱ ለመተርጎም ስለተቸገረ፣ እኛ በአማራነቱ መደራጀት አለበት የሚለውን ሀሳብ አነሳን፡፡
ቴዎድሮስ፡- የአማራ ሕዝብ ራሱን እንደ ኢትዮጵያዊ ብቻ ቆጥሮ መቀመጡ ችግር  ነው?
አቶ በለጠ፡- አይደለም፡፡ እንደ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱ አምኖ መቀመጡ ጤናማነቱን የሚያሳይ ነው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያን በመገንባት ሂደት ውስጥ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር ሆኖ ሰፊ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ ትናንት እኮ አማራው ብቻ ሳይሆን ሌላውም ሕዝብ በኢትዮጵያዊነት ጥላ ውስጥ ነበረ፡፡ ግን ደግሞ ሌሎች በማንነታቸው ተደራጅተው ፖለቲካውን ሲሰሩ፣ አማራው በኢትዮጵያዊነቱ ብቻ ተሰልፎ በመገኘቱ ከባድ መስዋዕትነት ከፈለ፡፡ በማንነታቸው የተራጁ ሀይሎች የመንግስት ስልጣን ተቆጣጠሩ፡፡ አድራጊ ፈጣሪ ሆኑ፡፡ ይህ ሕዝብ (አማራው) ወኪል አጣ፡፡ ኢትዮጵያዊ ኃይል መንበር ላይ አልመጣም፡፡ ስለዚህ በማንነት የተደራጁ ኃይሎች ስልጣን ሲያገኙ፣ በኢትዮጵያዊነቱ የቆመውን ሕዝብ በአንድም ሆነ በሌላው መንገድ ገፉት፡፡ በማንነቱ ተደራጅቶ፣ግን ደግሞ ኢትዮጵያን እያለመ፣ ትግል ማድረግ አለበት የሚል እንቅስቀሴ አደረግን፡፡ ይህ አጠቃላይ እንቅስቃሴ፣ በንቅናቄ መልክ መካሔድ መቻል ነበረበት፡፡
በፖለቲካ ብቻ ሳይሆን ማህበራዊ ጉዳዮችንም እንዲገነዘባቸው ማስቻል ነበረብን፡፡ ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶችም ጉልህ በሆነ ሁኔታ ህዝቡ ላይ ተፈፅመዋል፡፡ እነዚህን ትርጓሜ ሰጥቷቸው በዚያ ልክ ሰፊ ንቅናቄ ፈጥሮ፣ አንድ ወጥ የሆነ ትግል ማድረጉ አስፈላጊ ስለነበር፣ ከዚያ አጠቃላይ ሁለንተናዊ የሆነ የመገፋት ማዕቀፍ እንዲወጣ ሰፊ ንቅናቄ መፈጠር ነበረበትና፣ ፓርቲ በማደራጀት አስቻይ የሆነ ተጨባጭና ፈጣን  ለውጥ መምጣት ይችላል ብለን አላሰብንም፡፡ የአማራው ሁኔታ ሲታይ እንደ ኢትዮጵያዊነቱ ተጎድቷል፡፡ ከኢትዮጵያዊነቱ እንዲወርድ ሰፊ የሆነ ዘመቻ ሲከፈትበት ቆይቷል፡፡ በግልፅ በአደባባይ ነው የሚነገረው፡፡ በኢትዮጵያዊነቱ ጠንካራ የሆነ አደረጃጀት እንዲፈጠር አይፈቀድለትም ነበር፡፡ በዚህ ሂደት ብዙ ወንድሞቻችን አማራዎችም፣ ከአማራነት ውጭ ያሉትም፣ በአንድነት ፖለቲካ ውስጥ ተሳትፈው ብዙ ዋጋ ከፍለዋል፡፡ ይህ ዋጋ ግን ወደ መንበር እንዲቀርቡ አላደረጋቸውም፡፡ በኢትዮጵያ አሁናዊ ፖለቲካ፣ መሬት ላይ ያለው የማደራጃ መርሁ፣ የብሔር ፖለቲካ ነው፡፡ የብሔር ፖለቲካ ይዘትና ቅርጽ ኖሮት የሚሰራበት ፖለቲካ ነው፡፡ ይህን ማንም አይክደውም፡፡ መሪ የሆነውም ግለሰብ ለመሪነቱ የሚያበቃው የሆነን የብሔር ድርጅት ወክሎ ነው የሚመጣው። አቶ መለስ ዜናዊም፣ አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝም፣ ዐቢይ አህመድም የብሔር ድርጅት ወክለው ነው የመጡት፤ ስለዚህ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የሚጋብዘው፣ ማደራጃ መርሁ እንደዚህ ያለውን የብሔር ፖለቲካ ነው፡፡ ይህን ተገነዘብን፡፡ አማራ መደራጀቱ የግድና አስፈላጊ ነበር፡፡ ተደራጅቶ ሰፊ ንቅናቄ መፍጠር ነበረበት፡፡ አብን ተፈጠረ፡፡
ቴዎድሮስ፡- ስለዚህ አብን የተፈጠረው ለአማራው መብትና ጥቅሞች ሲል ብቻ ነው? ኢትዮጵያዊነትንስ የት አስቀመጠው?
አቶ በለጠ፡- የትም አላስቀመጠውም። እንደያዘው ነው፡፡ በአማራነት ስንደራጅ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ገፍተን አይደለም፡፡ ኢትዮጵያን ከእሳቤያችን አውጥተን አይደለም፡፡ ብንፈልግም አንችልም፡፡ መጨረሻችን ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ በእርግጥም አማራ ጠንካራ ሆኖ ባልተደራጀባቸው ጊዜያት ኢትዮጵያ አጠቃላይ ቁመናዋ ዝቅ ብሎ መታየቱን አይተናል፡፡ አማራ ተጎዳ ማለት ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ተጎዳች ማለት ነው፡፡ ኦሮሞም ተጎዳ ማለት ነው፡፡ ጠንካራ የአማራ አደረጃጀት ከተፈጠረ፣ ምናልባትም ባለመፈጠሩ የመጣውን ጉዳት መቀልበስ የሚችል እድልም ይዞ ይመጣል፣ የሚል እምነት ይዘን ነው እንደ ንቅናቄ ልንፈጠር የቻልነው፡፡
ቴዎድሮስ፡- ባለንበት ነባራዊ ሁኔታ፣ የብሔር ድርጅቶች እያሸነፉ፤ ሀገራዊ ፓርቲዎች ደግሞ አቅም እያነሳቸው የመጣው የብሔሮቹ ከሀገራዊዎቹ በምን ተሽለው ነው?
አቶ በለጠ፡- የብሔር ፓርቲዎች ተሽለው ነው ማለት አልችልም፡፡ ኢትዮጵያዊ ፓርቲዎችም ሳይሻሉ ቀርተው አይደለም። ወቅቱ ነው ማለት  እችላለሁ፡፡ ለ27 ዓመታት ሀገሪቱን እየመራ የነበረው ህወሃት፣ ቀደም ሲል በብሔር ንቅናቄ የተፈጠረ ድርጅት ነበር፡፡ ትግራይን ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ማዕቀፍ ገንጥሎ ራሱን የቻለ ሀገር ለማድረግ የተጠነሰሰ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ነበር፡፡ 1950ዎቹ፣ 60ዎቹ እና 70ዎቹ በብሔር የተደራጁ ድርጅቶች ተፈጥረዋል፡፡ ዛሬ ላይ በዚህ ሂደት መጥተው ነው ስልጣን የተቆጣጠሩት፡፡
እነዚህ ሰዎች ሲደራጁ የእነሱን ጥቅም ለማስጠበቅ ብቻ ሳይሆን ያልተደራጀውና በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር የተሰበሰበውን ኃይል ለመጉዳትም ጭምር እንደነበር ለመገንዘብ ጊዜ ወስዷል፡፡ እነዚህ አናሳ ቡድኖች ስልጣን ከያዙ በኋላ ተቋቁመው መቀጠል የሚችሉት ጠንካራ የሆነ የኢትዮጵያዊነት አደረጃጀት እስካልመጣ ድረስ ብቻ ነበር፡፡ ስለዚህ ህዝቦች እርስ በእርስ እንዲጋጩ እንዳይተማመኑ፣ እንዲጠራጠሩ፣ በታሪክ እንዲጣሉ፣ በምልክቶቻቸው እንዳይስማሙ፣ በታሪክ ውስጥ በምናውቃቸው ታላላቅ ሰዎቻችን ላይ ወጥ የሆነ መረዳት እንዳይኖረን፣ እንድንጣላበቸው የሚያደርጉ ትርክቶች መፍጠር ነበረበት፡፡ ህዝቡ በራሱ ጉዳይ ባተሌ መሆን ነበረበት፡፡ ስለዚህ ይህ ሂደት ጠንካራ የሆነ ኢትዮጵያዊ ኃይል ጉልበት አግኝቶ፣ ወደፊት እንዳይመጣ አንድ ምክንያት ነው ማለት እችላለሁ፡፡
ቴዎድሮስ፡- አብን መጀመሪያ ወደ ፖለቲካው መድረክ ሲመጣ ከአሁን አንፃር ድምፁን ጮክ በማድረግ ነበር፡፡ ይህን እንደ አንድ ፖለቲካዊ ስልት አድርጎ መውሰድ ይቻላል? ወይስ ሌላ ምክንያት አለው?
አቶ በለጠ፡- ልክ ነው፡፡ በወቅቱ አብን ሲመሰረት በጣም ክፍ ያለ ድምጽ ነበረው። ይህን በሁለት መንገድ ማየት ያስፈልጋል፡፡ አንደኛ፤ ይህ ሕዝብ አማራ ተብሎ ተፈርጆ፣ “ነፍጠኛ” እና “ትምህክተኛ” እየተባለ በአደባባይ በመሪዎች ጭምር ይዘልፉት የነበረ ሕዝብ ነው፡፡ አማራን በአደባባይ መዝለፍ አንዳንዴ የስልጣን ማግኛ አቋራጭ መንገድ ነበር፡፡ በዚህ ብቻም አላበቃም። የአማራ ልጆች በአደባባይ ጥያቄ ያነሱ፣ የሞገቱ፣አምባገነኑን ስርዓት የጠየቁ ሁሉ “ቶርች” ተደርገዋል፤ ተሰቃይተዋል፤ ተገድለዋል፤ የጠፉት ጠፍተዋል፡፡
በአጠቃላይ በኢትዮጵያ እስር ቤቶች በአማራው፣ በሌላውም ህዝብ ላይ የተፈፀመውን ግፍ ሕዝብ ስለሚያውቀው መዘርዘር አያስፈልግም፡፡ ይህ ግፍ  ተጠራቅሞ ህዝቡ ላይ የአዕምሮ ቁስለት (Trauma ) ፈጥሮ ኖሯል ብዬ አምናለሁ። መደረግ የሌለበት ግፍ ተፈፅሞባቸው ከእስር ቤት ሲወጡ፣ ያን ምስክርነት ሲሠጡ ህዝብ ስሜት አለው፡፡ ከፍ ያለ የህዝብ ቁጣ ፈጥሯል፡፡ አብንም ይህ ስሜት የወለደው ነው፡፡ ከሕዝብ የወጣ ድርጅት ነው። ሕዝባዊ ንቅናቄ እየፈጠረ ያለ ድርጅት ስለሆነ፣ የሕዝቡ ህመም የሚሰማው ነው፡፡ ወደ ፖለቲካው መድረክ ስንመጣ፣ እንዲህ ከፍ ያሉ ድምጾች ሲሰሙ፣ ከዚህ አንጻር መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ከዚያ ውጪ እንደ ስልትም ከታየ በእርግጥም ልክ ነው፡፡ እንደ ስልት መውሰድም አለበት፡፡
በተለይ መጀመሪያ ስንመጣ “በአማራነት መደራጀት አስፈላጊ አይደለም; የሚለው እሳቤ፤ ከአማራ ውጭ ካሉት ብቻ ሳይሆን ከአማራ ልሂቃንም ይሰማ ነበር፡፡ አብዛኛው የአማራ ልሂቅ “የብሔር ፖለቲካ አያስፈልግም፤ በኢትዮጵያዊነት ነው መደራጀት ያለባችሁ” ብሎናል፡፡ የደገፉንም አልጠፉም፡፡ የእኛን አስተሳሰብ ተደራሽ ለማድረግና ንቅናቄው ትኩረት እንዲሰጠው እንደ ስልት ብንጠቀምበትም ትክክል ነበር። በአማራነት መደራጀት አማራጭ መሆኑን እንዲነቃና እንዲያስበው፣ የትኛውንም ስልት መጠቀም ያስፈልገን ነበር፡፡ ይሁንና ምክንያቱም አንድ ሳይሆን የተለያየ ነው። አሁን ላይ በተነሳው ደረጃ ተግዳሮት አለብን ማለት አልችልም፡፡ መጀመሪያ ላይ ግን የአማራው እንደ አማራ መደራጀት፣ ለኢትዮጵያ አንድነት ህልውና ስጋት ነው ብለው ከተቃወሙን ውስጥ ሰፊ የአማራ ልሂቃን ነበሩ፡፡
(ከጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ "ፍልስምና" የተሰኘ አዲስ መጽሐፍ የተቀነጨበ)


Read 2089 times
Administrator

Latest from Administrator