Saturday, 03 April 2021 19:24

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር

Written by  ድርሰት፡- አዚዝ ኔሲን ትርጉም፡- ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(10 votes)

  ከዕለታት አንድ ቀን ከዚህ ዓለም ሀገራት በአንዱ አንድ ንጉሥ ነበር፡፡ እንደማናቸውም ንጉሦች ይህኛውም ንጉሥ የራሱ ሙዚቀኞች ዳንሰኞች፣ ውሽሞች፣ ባሮች፣ ጫማ ሳሚዎችና የመሳሰሉት ነበሩት፡፡ እንደ መክፈቻ ሥነ ሥርዓቶች ላይ መሳተፍ፣ ወታደራዊ ሰልፍ መመልከት፣ ከሌሎች የተጻፉ ንግግሮችን ማንበብና ጉብኝት ማድረግ ከመሳሰሉ በርካታ ኦፊሴላዊ ተግባራቱ የተረፈ ጊዜ ሲያገኝ አደን ይሄዳል፡፡
ሆኖም የአየር እርጥበት ምቾት የማይሰጠው በመሆኑ የሚገጥመውን የአየር ሁኔታ በደንብ ሳያረጋግጥ መቼም ቢሆን አደን አይወጣም። ዋናውን ኮከብ ቆጣሪውን ያስጠራና ስለ አየር ሁኔታው ትንበያ ከእሱ ይሰማል፡፡
ዋናው ኮከብ ቆጣሪም ዘወትር ‹‹በእርሶ ምክንያት የአገራችን አየር ሁኔታ ሁልጊዜም ብሩህና በፀሐይ ብርሃን የተሞላ ለሆኑት ሞገስ ለተሞሉት ግርማዊነትዎ ረጅም ዕድሜ፡፡ የአየር ሁኔታው ግርማዊነትዎ እንደሚፈልጉት ጥሩ ይሆናል፡፡››
ንጉሡ እንደ ሁሉም ነገሥታት ተጠራጣሪ በመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጠርቶ የአየር ሁኔታው ምን እንደሚሆን ይጠይቀዋል። የጆሮው ፀጉር ሳይቀር  የሸበተውና ከሆዱ በታች የተንጠለጠለ ጢም ያለው ኃያሉ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጢሙ የንጉሡን እግር እስኪነካ ድረስ ይንበረከክና፤ ‹‹በግርማዊነትዎ ሩህሩህ ጥላ ስር በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጪ ያለው ፖለቲካዊ ሆነ ፖለቲካዊ ያልሆነ የአየር ሁኔታ በፈጣሪ ፍቃድ በጣም ጥሩ ይሆናል፡፡”
ተጠራጣሪው ንጉሥ ከዛም እያንዳንዱን ሚኒስትር በየተራ ስለ አየር ሁኔታ ይጠይቅና ከሞላ ጎደል እንዲህ የሚል ምላሽ ያገኛል፡-
‹‹አድማሱ ሐምራዊ፡ አየሩ ግሩም ነው። ፈጣሪ ሁልጊዜም የግርማዊነትዎ ርህሩህ ጥላ ራሳችንን እንዲከላክልልን ያድርግልን። ግርማዊነትዎ እስካሉ ድረስ የአየሩ ሁኔታ መልካም እንጂ ሌላ የመሆን ዕድል የለውም፡፡››
በመጨረሻም በራስ መተማመኑና በገደብ የለሽ ስልጣኑ በመመካትና የባለሙያዎቹን የፖለቲካ መሪዎች ምክር በመንተራስ ንጉሡ በልዩ ሁኔታ የተባዙ እንስሳት ወዳሉበት ልዩ ጫካ ይሄዳል፡፡ የአደን ቁሳቁሶቹ በተመረጡ ሰዎች ትከሻዎች ላይ ይጫናሉ። ሁሉም ሕይወታቸውን ለንጉሡ ለመሰዋት ፈቃደኛ በሆኑ ከፊት ፖሊሶችና ዘቦች፣ ከጎን ጎን የጦር ኃይል ክፍሎች በተጨማሪም በመንገዱ የተበታተኑ በርካታ በጎ ፈቃደኞች፣ መሀል ላይ ንጉሡ፡፡ በተጨማሪም በእንደዚህ አይነት ንጉሡን የሚያጅቡ በርካታ የሲቪልና ወታደራዊ ባለስልጣናት አሉ፡፡
ሁኔታዎች በመልካም ሁኔታ እየሄዱ ነበር፡፡ አንድ ቀን ንጉሱ በተከታዩ ቀን አደን ለመሄድ ይወስናል።
ዋናውን ኮከብ ቆጣሪ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን፣ እያንዳንዱን የካቢኔ ሚኒስትር፤ የኃይማኖት መሪውን፣ ዋናው ፀሀፊን፣ የውሽሞች ሀላፊን፣ የቤተ መንግሥቱ የእልፍኝ አስከልካዩን እያለ በደረጃ ተዋረድ የአየር ሁኔታው እንዴት እንደሚሆን ጠየቀ፡፡ ከሁሉም የተለመደውን መልስ በማግኘቱ ወደ አደኑ አቀና፡፡
የንጉሡ አጀብ የሚያልፍበት መንገድ ሁሉ በደህንነት ሰዎች ተበጥሮ የተፈተሸ ቢሆንምና ማንም ተራ ሰው የንጉሡ አጀብ በሚያልፍበት ዝር እንዳይል ቢደረግም አንድ መንደረተኛና አህያው እንደምንም በመንገዱ ላይ አንድ ዛፍ ስር ተጠልለው መቆየት ችለው ነበር። ንጉሡ በህይወቱ ሙሉ አንድም መንደረተኛ አይቶ አያውቅም፡፡ በቡቱቶ የተጠቀለለና ባዶ እግሩን የሆነ ፍጡር ሲያይ ምን እንደሆነ ተገረመ፡፡ ህይወት ከሌለው ግዑዝ ነገር ሌላ ይሆናል ብሎ ሊያስብ አይችልም ነበር፡፡ ለማወቅ በመጓጓት ወደ መንደርተኛው ተጠጋ። ፊት ለፊቱ ያለው እንግዳ የሆነ ፍጡር ህይወት ያለው መሆኑን ሲገነዘብ ንጉሡ በመገረም፤ ‹‹አንተ ማነህ? ሰብአዊ ፍጡር ወይስ መንፈስ?›› ሲል ጠየቀው።
‹‹መንፈስ አይደለሁም›› ሲል መንደርተኛው መለሰ፡፡ ‹‹ልክ እንደ እርሶ የአዳም ልጅ ነኝ፡፡››
ንጉሡ ይህን ስርአት የለሽ መልስ ሲሰማ ተናደደ። ‹‹ምን አይነት ብልግና ነው! እንዲህ አይነት ነገር ከእኔ ዘር ሊመጣ አይችልም። ቶሎ በሉና አንገቱን ቀንጥሱት፣›› ሲል አዘዘ። ጎራዴው መንደረተኛው አንገት ላይ ከማረፉ በፊት ንጉሡ፣ ‹‹ቆይ!›› ብሎ ጮኸ። መንደረተኛውንም አናገረው፡፡
‹‹አንተ ቃላቶችህ የሰውን ልጅ ንግግር የሚመስሉ ልዩ ፍጡር፤ አንድ ነገር ልጠይቅህ እፈልጋለሁ፡፡ መልሱን ከሰጠኸኝ ትተርፋለህ፡፡ በዛሬው ቀን የአየር ሁኔታው ምን ይመስላል?››
‹‹ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ኃይለኛ ነፋስ መንፈስ ይጀምራል፡፡ ከዛ ዶፉን ይለቀዋል” ሲል መንደረተኛው መለሰ፡፡
ንጉሡ ከመንደረተኛው አንደበት እነኚህን ቃላት ሲሰማ ብው አለ፡፡ ‹‹አንተ ከሀዲ! እኔ አደን ለመውጣት ከወሰንኩ በምንም አይነት አየሩ መጥፎ ሊሆን እንደማይችል አታውቅም? እኔ አደን ወጥቼ እንዴት ብሎ ነው የሚዘንበው? ይህን ፍጡር ፍጠኑና ከበቅሎዋ ጭራ ጋር እሰሩልኝ!››
መንደረተኛውን ከራሱ አህያ ጭራ ጋር አሠሩትና አህያው ደግሞ ከበቅሎይቱ ጋር ታሠረ፡፡ የአንዲት ጦር ርዝመት ያህል እርቀት ሳይጓዙም ሰማዩ ጠቆረ። ከባድ የጠቆሩ ደመናዎች ይጥመለመሉ ጀመር፡፡ የንጉሡም አጀብ በመብረቅ ነጎድጓድ ተተራመሰ። ከዛም ኃይለኛ ዶፍ በመውረዱ አካባቢው በጎርፍ ተጥለቀለቀ፡፡ ከባድ ነፋስም እያፏጨ ያገኘውን ነገር ሁሉ አተረማመሰ፡፡ ንጉሡ ከዚህ ድብልቅልቅ የወጣው በመከራ ነው፡፡ በጣም ከመናደዱ የተነሳም ቤተ መንግሥቱ እንደደረሰ ስለ አየር ሁኔታው የተሳሳተ መረጀ የሰጡትን ሁሉ አባረረ፡፡ ከነዚህም መሀል ዋናውን ኮከብ ቆጣሪ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በጠቅላላ ሚኒስትሮችና ከአየር ትንበያ ጋር ግንኙነት ያላቸውን የቤተመንግሥት ባለስልጣናትም ነበሩበት፡፡
ስለ መጥፎው አየር ሁኔታው ተንብዮ እውነት የሆነለትን መንደረተኛ ንጉሡ አስጠራው፡፡ አህያው ጭራ ላይ ታስሮ ረጅም መንገድ ስለተጎተተ ሙሉ ለሙሉ ተዳክሟል፡፡ ንጉሡም ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሾመው፡፡
‹‹ከአሁን ጀምሮ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ አድርጌ ሾሜሀለሁ፡፡››
መንደረተኛው ለጥቂት ቀናት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ እንደሠራ፣ ንጉሡ ሀሳቡን ሰብስቦ ወደ ቤተ መንግሥቱ አስጠራው፡፡
‹‹እስቲ ንገረኝ፣ ያን ዕለት እንደሚዘንብ እንዴት አወቅህ?››
‹‹ግርማዊነትዎ ሆይ፣›› ሲል ጠቅላይ ሚኒስትሩ መለሰ፡፡ ‹‹የአየር ሁኔታውን በትክክል ለመተንበይ የሚረዱኝን የአህያዬን ጆሮዎች እከታተላለሁ። የሚዘንብ ከሆነ ቀጥ ያሉ የአህያዬ ጆሮዎች ያዘነብላሉ፡፡ ያን ዕለት ጆሮዎቹን በዚህ አይነት አቋም አየኋቸውና እንደሚዘንብ ነገርኩዎት፡፡
‹‹ምን አይነት የማልረባ ሰው ነኝ!›› አለ ንጉሡ፡፡ ‹‹የአየር ሁኔታውን በትክክል የተነበየው መንደረተኛው ሳይሆን አህያው ነው፡፡ አህያው የሚያውቀውን ያህል እንኳን የማያውቁ ሚኒስትሮችና ጠቅላይ ሚኒስትር አሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ለመንደርተኛው በመስጠቴ አህያው የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የመሆን መብቱን ነፍጌዋለሁ?››
ንጉሡ ጊዜ ሳያጠፋ መንደረተኛውን ሻረና አህያውን አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሾመው። ከዛ ጊዜ ጀምሮ አየሩ ጥሩ በሚሆንበት ጊዜ አህያው በደስታ ያናፋል፣ ንጉሡም መልእክቱ ይገባዋል። አውሎ ነፋስ እየመጣ ከሆነም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጭራውን ቀጥ ያደርጋል፣ የሚዘንብ ከሆነ ደግሞ ጆሮዎቹ ወዲያውኑ ያዘነብላሉ፡፡
ከዛ በኋላ ንጉሡ በደስታ ኖረ። የአዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ምክር መቼም ቢሆን፤ በተለይ አደን መውጣት በፈለገበት ጊዜ ችላ ብሎት አያውቅም፡፡
ምንጭ፡-
(‹‹ራሴን አጠፋሁ እና ሌሎችም››  ከሚለው መድበል የተወሰደ)
Read 2037 times