Saturday, 10 April 2021 12:34

"በትግራይ የሚካሄደው ጦርነት ውስብስብና የተራዘመ ሊሆን ይችላል"

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(8 votes)

              
         አምስት ወራት ያስቆጠረው በትግራይ የሚካሄደው ጦርነት በፍጥነት ላይቆም እንደሚችል  የጠቆመው አለማቀፉ የግጭቶች አጥሪ ቡድን (ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ) በተለይ አዳዲስ ወጣቶች አማፂውን ቡድን እየተቀላቀሉ መሆኑ ጉዳዩን ውስብስብና የተራዘመ ያደርገዋል ብሏል፡፡
መንግስት በበኩሉ፤“ጦርነቱ ተጠናቋል፤ ሕወሃት የሚባለው ቡድን ተደምስሷል፤ የቀረው ርዝራዦችን የመልቀም ስራ ብቻ ነው” ብሏል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህወኃት በገጠሩ አካባቢ በድጋሚ የመሰባሰብና የመጠናከር ሁኔታ እያሳየ ነው የሚለው ክራይስስ ግሩፕ፤ እነዚህ ሁኔታዎች ጦርነቱ እንደታሰበው ባጭሩ እንዳይቋጭ ሊያደርጉት ይችላሉ ብሏል፡፡
ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ በፓርላማ ባቀረቡት ማብራሪያ፤ “ህወኃት በአሁኑ ወቅት አየር ላይ የተበተነ ሀይል ነው፣ በመሬት ላይ የለም፤ ይሄን ሃይል መለቃቀም ብቻ ነው የሚቀረው ማለታቸው የሚታወስ ነው፡፡ በቅርቡ መንግስት በትግራይ ወጣቶች በተሳሳተ መንገድ ወደ ታጣቂ ቡድኑ እየገቡ መሆኑን በመጥቀስ ራሳቸውን ከታጣቂው ቡድን የሚለዩበትና በምህረት ወደ ሰላማዊ ኑሮ የሚመለሱበትን የአንድ ሳምንት ጊዜ እድል መስጠቱ አይዘነጋም፡፡
 ባለፈው ረቡዕ  ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ የሠጡት የመከላከያ ሚኒስቴር የኢንዶክትሪኔሽን ሃላፊው ሜ/ጀነራል መሃመድ ተሰማ በበኩላቸው፤ መከላከያ ሰራዊቱ የህወኃት ርዝራዦችን በመለቃቀም ላይ  መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የመጠናከር አዝማሚያ ያሳየው ተፈፀሙ የተባሉ ኢ ሰብአዊ ድርጊቶች በመገናኛ ብዙኃን በመውጣታቸውና ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ በመዋላቸው መሆኑን ክራይስስ ግሩፕ አመልክቷል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በተበታተነ መልኩ በሽምቅ ውጊያ ላይ  የተሰማራው የህወኃት ቡድን ቀደም ሲል ጦርነቱን ሲጀምር ታንኮች፣ ሮኬቶችንና ሌሎች ከባድ መሳሪያዎችን ታጥቆ የነበረ ቢሆንም፤ በአሁኑ ወቅት በቀላልና የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎች ብቻ የሽምቅ ውጊያ ለማድረግ መገደዱን ነው የተቋሙ ሪፖርት ያመለከተው፡፡
በሽምቅ ውጊያ ላይ ነው በተባለው የህወኃት ቡድን ውስጥ የቀድሞ የመከላከያ ሰራዊት ኢታማዦር ሹም ሌ/ጄነራል ፃድቃን ገ/ትንሳይና ሜ/ጀነራል ታደሰ ወረደ እንደሚገኙበት ክራይስስ ግሩፕ ጠቁሟል፡፡
“በአሁኑ ወቅት አማፂው ቡድን ከውጭ የሚገናኝበት ምንም ዓይነት መንገድ አለመኖሩ የበለጠ እንዳይጠናከር ያደርገዋል፤መከላከያ ሰራዊትም ጠንካራ እርምጃዎች እየወሰደ መሆኑ ፋታ ይነሳዋል፤ በዚህም ትርጉም ያለው ውጤት አያመጣም፤ ለመከላከያ ሰራዊትም ያን ያህል ስጋት አይሆንም” ብሏል ሪፖርቱ፡፡
ክራይስስ ግሩፕ በሪፖርቱ ማጠቃለያ በቅድሚያ ተኩስ እንዲቆምና ዜጎች እርዳታ እንዲያገኙ የጠየቀው ክራይስስ ግሩፕ፤ በመቀጠልም  አማፂው ቡድንና መንግስት ተደራድረው ለችግሩ መፍትሔ እንዲያበጁ ምክረ ሃሳብ አቅርቧል፡፡
በትግራይ ለተፈጠረው ቀውስ በዋናነት ህወኃትና መሪዎቹ ተጠያቂ መሆናቸውን ያመለከተው ተቋሙ፤ መንግስትም የራሱ ድርሻ እንዳለው ጠቁሟል፡፡


Read 11647 times Last modified on Saturday, 17 April 2021 11:10