Saturday, 10 April 2021 12:46

እስከ ምርጫው መጠናቀቂያ የፀጥታ ተግባር በኮማንድ እዝ እንዲመራ ተጠየቀ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(5 votes)

   
            በጥቃቱ እጃቸው አለበት የተባሉ ተሳተፎ የነበራቸው የመንግስት ሃላፊዎች በህግ ሊጠየቁ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡
ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ተከናውኖ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እስከሚደረግ ድረስ የአገሪቱ የፀጥታ ተግባር በጊዜያዊነት በተማከለ ኮማንድ እዝ ሊመራ እንደሚገባው የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አሳሰበ።
ተቋሙ በትላልቅ ከተሞችና የተለያየ የህብረተሰብ ክፍል በስብጥር የሚኖሩባቸው አካባቢዎች እንዲሁም የአስተዳደራዊ ወሰን ውዝግብ ያለባቸው ስፍራዎች፣ በፌደራል ፖሊስ ጥላ ስር ሆነው፣ ከሁሉም ክልሎች በተውጣጡ የልዩ ሀይል ፖሊሶች እንዲጠበቁ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁሟል፡፡
ከተቋሙ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው በቅርቡ፤ በሰሜን ሸዋ ዞንና ኦሮሚያ ልዩ ዞን ውስጥ በተፈጠሩ ግጭቶች 303 ንጹሀን ዜጎች ሲገደሉ፣ 369 ያህሉ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን 91 ሺ 756 ዜጎች ደግሞ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል፡፡
ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ 81 ተጠርጣሪ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው እንደነበር ያመለከተው ይኸው መረጃ፤ ከበላይ በተሠጠ ትእዛዝና ምክንያቱ ባልታወቀ መንገድ እንዲለቀቁ ተደርገዋል ብሏል፡፡
በሰሜን ሸዋ ዞን የተፈፀመው ጥቃት፣ በዘመናዊ መሳሪያ የተደገፈ እንደነበር አረጋግጫለሁ ያለው ተቋሙ፤ በወቅቱ በአካባቢው የነበረው የፀጥታ ኃይል እንዲነሳ መደረጉ ችግሩን የከፋ አድርጎታል ብሏል፡፡ በአካባቢው የደረሱት ጥፋቶች የመንግስት ቸልተኝነት ወይም ትኩረት ማነስ ውጤት ነው ብሎ እንደሚያምን አመልክቷል፡፡
መንግስት የህግ የበላይነት ከማስከበርና ከማረጋገጥ በላይ ቀዳሚ አጀንዳ ሊኖረው አይገባም ያለው  ተቋሙ፤ ቢያንስ በጉያው ስር  ያሉትንና ለችግሮች መፈጠርና መባባስ ምክንያት የሆኑትን አመራሮች ሊያጣራና አስቸኳይ እርምጃ ሊወስድ ይገባል ብሏል፡፡
የክልል ከፍተኛ አመራሮች ከብሔር አስተሳሰብ በመውጣት በመርህ አገሪቱን ብሎም ክልላቸውን ሊመሩ ይገባል የሚል እምነት እንዳለው የገለፀው የህዝብን እንባ ጠባቂ ተቋም
የመንግስት አስፈፃሚ አካላት ለህግ የበላይነት መርህ ሊገዙ ይገባል ብሏል፡፡
በግጭቱ ተሳትፎ የነበራቸው የመንግስት አስፈፃሚ አካላት በህግ ሊጠየቁ እንደሚገባም የእንባ ጠባቂ ተቋም አሳስቧል፡፡ የሰላም ሚኒስቴር አደረጃጀት በአግባቡ እንዲታይና እንደገና እንዲከለስ ያሳሰበው ተቋሙ፤ መንግስት ቆፍጠን ያለ አመራር ሊሰጥ እንደሚገባም አመልክቷል፡፡
የሰላም ሚኒስቴር ሁለት ተቃራኒ ተግባራትን ማለትም የሰላም ግንባታና የፀጥታ ማስከበር ኃላፊነቶች የተሰጡት ሲሆን የሰላም ግንባታው በሂደትና በተራዘመ ትምህርትና የግንዛቤ ስራ የሚከናወን ሲሆን የፀጥታ መዋቅር ግን በቅ    ፅበት በሚወሰኑ ውሳኔዎችና እርምጃዎች የሚከናወን እንደሆነ ያመለከተው የተቋሙ  መረጃ፤ የፀጥታ መዋቅሩና የማህበራዊ መረጃ ደህንነት ስራው ራሱን በቻለ ተቋም ሊመራ እንደሚገባው ጠቁሟል፡፡ ይህ ካልሆነም ተጠሪነቱ በቀጥታ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መሆን አለበት ይላል-ተቋሙ፡፡



Read 11397 times Last modified on Saturday, 17 April 2021 11:06