Saturday, 10 April 2021 13:39

ደመና ማዝነብና የጎንዮሽ ውጤቶቹ

Written by  ደስታ መብራቱ
Rate this item
(1 Vote)

ከሁሉ በማስቀደም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድና መንግስታቸው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለማበልጸግ፣ ወደ ሃገር ውስጥ ለማስገባትና አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ለማድረግ የሚሰጡትን ትኩረት ለማድነቅ እወዳለሁ። ዓለማችን እየገባችበት ካለው የአራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ዘመን አኳያ ራሳችንን ዘመኑ ባፈራቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች ማስታጠቅ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱን መጻኢ የኢኮኖሚ እድሎችንም የሚወስን ነው። ባለፉት ወራት  ውስጥ እንዲህ ዓይነት ትኩረት ከተሰጣቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች መካከል የኒዩክሊየር፣ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስና የደመና ማዝነብ ቴክኖሎጂዎች ይገኙበታል። በዚህ ጸሃፊ ዕምነት፣ ከማንኛውም የቴክኖሎጂ ሽግግር ልናገኝ የሚገባንን ሃገራዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የምንችለው፣ የቴክኖሎጂ ሽግግሩ በዕውቀት ላይ በተመረኮዘና ሁለንተናዊ ጠቀሜታውን ባረጋገጠ መልኩ ሲከናወን ብቻ ነው። በተለይም ትውልድ ተሻጋሪና ዘርፈ ብዙ ጉዳቶች ሊያስከትሉ የሚችሉ የኒዩክሊየር ኃይል ማመንጫና የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ ሽግግርን በሚመለከት ልዩ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።  በዚህ ረገድ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና ልማቱን በግንባር ቀደምትነት እንዲመራ ሃላፊነት የተሰጠው የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ባለሙያዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንና የሙያ ማህበራት ከፍተኛ ድርሻ ይኖራቸዋል። በዚህ ጽሁፍ፣ ሰሞኑን የመወያያ ርዕስ በሆነው የደመና ማዝነብ ላይ በማተኮር በጥንቃቄ ሊታዩ የሚገቡ አበይት ጉዳዮችን በአጭሩ ለማመላከት እሞክራለሁ።  
በቅድሚያ የቴክኖሎጂውን ምንነት በቀላሉ ለማስረዳት፣ ደመና ማዝነብ (cloud seeding) ማለት መሰረታዊ ባህርያትን ያሟላ የደመና ቁልል ላይ ባእድ የሆኑ ቁሶችን በመርጨት ወደ ዝናብነት ወይም በረዶነት ተቀይሮ በተመረጠ አካባቢ እንዲወርድ ማድረግ ነው። ይህንን ለማሳካትም ዋነኛው መንገድ የተለያዩ የማዕድን አዮዳይድስ (mineral iodides) ወይንም ጨው ደመናው ውስጥ በመርጨት በደመናው ውስጥ ያሉትን ጋሶች ትስስር ማበልጸግ ነው። በበርካታ ጥናቶች እንደተረጋገጠው፣ የዚህ ደመናን ወደ ዝናብ የመቀየር ቴክኖሎጂ ውጤማነት ባብዛኛው ከ 3 እስከ 5% ባለው መጠን የተወሰነ ሆኖ ተገኝቷል። በተለያዩ ሚዲያ ተደጋግሞ እንደተገለጸው፤ ደመና ማዝነብ ለበርካታ አስርተ ዓመታት የሚታወቅና በብዙ ሃገሮች ለተወሰኑ ዓላማዎች በተግባር ላይ የዋለ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ ዝናብ አጠር (arid) በሆነ የአየር ጠባያቸው የሚታወቁ አንዳንድ የመካከለኛው ምሥራቅ ሃገሮች ቀደም ሲል ከነበረው የተናጠል (isolated) አጠቃቀም በሰፋ መልኩ የመጠቀም እንቅስቃሴ ጀምረዋል። ከዚህ አኳያ፣ ኢትዮጵያም እንደ ማንኛቸውም ሌሎቹ ሃገሮች እጅግ በጣም አስፈላጊና ውሱን ለሆኑ ዓላማዎች ቴክኖሎጂውን ለመጠቀም የሚያስችል አቅም መገንባቷ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። በተለይም እንዲህ ዓይነት አቅም ግንባታ በወዳጅ መንግሥታት ድጋፍ የሚከወን ሲሆን ብዙም የሚያወዛግብ ሊሆን አይገባውም። ከዚህ አልፎ ግን፣ ይህንን ቴክኖሎጂ እንደ ዋነኛ የልማት አቅጣጫ አድርጎ መውሰድ በጥንቃቄ ሊታይ የሚገባው ነው። ለዚህም፣ በኢኮኖሚያዊ ውጤታማነቱ ላይ ሊነሱ ከሚችሉ ጥያቄዎች ባሻገር የሚከተሉትን አበይት ጉዳዮች መመልከት ያስፈልጋል።
የመጀመሪያው፣ ደመናውን ለማዝነብ ከሚረጨው ባእድ ቁሶች ጋር በተያያዘ ሊፈጠር የሚችለው ምህዳራዊ ክምችት (systemic deposition) በመካከለኛና በረዥም ጊዜ ሊያስከትል የሚችለው ማህበራዊና ከባቢያዊ ቀውስ ነው። ምህዳራዊ ክምችት፣ አንድ ከባቢያዊ ምህዳር በመደበኛው ዑደቱ (natural cycles) ሊያዋህደውና ሊያስተናግደው ከሚችለው በላይ ለሆነ ሰው ሰራሽ ግብዓት ሲጋለጥ የሚፈጠር የተዛባ ሁኔታ ነው። ላለፉት በርካታ አስርተ ዓመታት ያለ ሃሳብ ስናነደው የኖርነው የከርሰ ምድር ነዳጅ በከባቢ አየራችን ሊኖር የሚገባውን የካርቦን መጠን ከሚገባው በላይ በማሳደጉ የተነሳ ዛሬ ዓለማችንን ፈተና ውስጥ ለከተተው የአየር ሚዛን መዛባት መጋለጣችን ለዚህ አንድ ምሳሌ ነው። በተመሳሳዩ፣ ደመናን ለማዝነብ የምንጠቀማቸው ቁሳዊ ግብዓቶች ከዝናቡ ጋር አብረው ወደ ምድር የሚወርዱ በመሆናቸው በአካባቢያዊ ምህዳሩ ላይ ሊያስከትሉ የሚችሉትን ጎጂ ውጤቶች መመልከት አስፈላጊ ይሆናል። እስካሁን ድረስ ይህ ቴክኖሎጂ በጣም በተወሰነ ሁኔታ ጥቅም ላይ የዋለ በመሆኑ በአካባቢና ጤና ላይ ያስከተለው ተጽእኖ በዚያው መጠን ውሱን ነው።  ነገር ግን፣ ይህን ቴክኖሎጂ በስፋት የመጠቀም ሃሳቡ ካለ፣ ይህ ጉዳይ ተገቢው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ለምሳሌም፣ ከተወሰነ መጠን በላይ ጨውን የምንጠቀም ከሆነ፣ ይህ ከዝናቡ ጋር አብሮ በመውረድ የአፈሩን ጨዋማነት (salinity) ሊያሳድገው ይችላል። በሌላ በኩል፣ የምንጠቀመው የብር አዮዳይድ (silver iodide) ከሚገባው በላይ ከተከማቸ በሰዎች ጤንነት ላይም ሆነ ባካባቢ ብዝሃ ህይወት ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ቀላል አይደለም።
በማናቸውም የቴክኖሎጂ ሽግግር ግምገማ ወቅት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ሌላው ዓቢይ ጉዳይ ቴክኖሎጂው ከከባቢያዊ ምህዳር ጋር ሊኖረው የሚችለው መጣጣምና ሊያደርስ የሚችላቸው ጎጂ ውጤቶች ናቸው። ይህም ባብዛኛው ከአካባቢው ምህዳር ልዩ ባህርያትና ተጋላጭነት (ecological sensitivity) ጋር ይያያዛል። ለምሳሌም ያህል፣ የተባበሩት የአረብ ኤሚሬቶች ያላት የተፈጥሮ አካባቢ ምህዳር ከኢትዮጵያው የተፈጥሮ አካባቢ ምህዳር ከፍተኛ የባህርይ ልዩነት ያለው ነው። በመሆኑም፣ የተባበሩት የአረብ ኤሚሬቶች ካላት ውሱን የዝናብ እድል አኳያ ያሏትን ቀዳዳ ተጠቅማ ደመናን ማዝነብ ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ብታፈስ ተቀባይነት ይኖረዋል። ይህ ማለት ግን፣ በአፍሪካ ውስጥ ከኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ ቀጥሎ በውሃ ማማነት (water tower) የምትታወቀው ኢትዮጵያ ደመና ማዝነብን እንደ ዋነኛ  የልማት አቅጣጫ መውሰድ አለባት ለማለት አያስችልም። ከዚህ ይልቅ፣ በአረንጓዴው አሻራ እንደተጀመረው የሃገሪቱን የደን ሽፋን በማሳደግ ተፈጥሮአዊውን ደመና የማበልጸግ አቅሟን ማጠናከሩ የበለጠ ውጤታማ ያደርጋታል። ከዚህም ባላይ፣ ሊጨምር በሚችለው ጨዋማነትም ሆነ የከባቢ መበከል ምክንያት በሁለቱ ሃገሮች ከባቢያዊ ምህዳር ላይ ሊደርስ የሚችለው ጉዳትም በእጅጉ የተለያየ ይሆናል። ስለዚህም፣ ይህንንና ሌሎችም በመግቢያው ላይ የተጠቀሱ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት ለመጠቀም ከመወሰኑ በፊት ጠለቅ ያለ የከባቢያዊ ቴክኖሎጂ ሽግግር ግምገማ (Environmental Technology Assessment) ማድረግ ሃገሪቱን ለትውልድ ከሚተላለፉ ጉዳቶች ያድናል።   
ቀደም ሲል እንደተገለጸው፣ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በማደግ ላይ የሚገኙ ሃገሮች ባለፉት ሦስት የኢንዱስትሪ አብዮቶች እንደነበረው፣ የአራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ዘመንም የበዪ ተመልካች ከመሆን መዳን ከፈለጉ ዘመኑ ያፈራቸውን ቴክኖሎጂዎች መረዳትና አስማምቶ ጥቅም ላይ ማዋል ይኖርባቸዋል። ይህንን በሚያደርጉበት ወቅት ግን፣ የተዛቡ የቴክኖሎጂ መረጣና ሽግግር ውሳኔዎች በማድረግ ከፍተኛ ዋጋ ሊያስከፍሉ ለሚችሉና በኪሳራ ለታጠሩ ንብረቶች (stranded assets) እንዳይጋለጡ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።  እነኚህን መሰል አደጋዎች ለመቀነስና ለማስወገድ፣ ወደ እኛ የሚጎርፉ ማንኛውንም የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በዘፈቀደ የአጋጣሚ እመርታ (incidental leapfrogging) ተቀብሎ ከማስተናገድ መቆጠብ ያስፈልጋል። ከዚህ ይልቅ በዕውቀት ላይ በተመረኮዘ የዓይነታዊ እመርታ (transformational leapfrogging) መርሆዎች መሰረት የትኛውንም ቴክኖሎጂ ለሃገሪቱ ልዩ ሁኔታና ዘላቂ ልማት ግቦች በሚስማማ መልኩ በትኖ (unpack) መፈተሽና አስማምቶ ስራ ላይ ማዋል ያስፈልጋል። ለዚህም፣ ከሃገሪቱ የቴክኖሎጂ ተቋማትና ባለሙያዎች ከፍተኛ የምክርና የዕውቀት ድጋፍ ያስፈልጋል።
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊው  ደቡብ አፍሪካ በሚገኘው ስታለንቦሽ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፈሰር ሲሆኑ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትም ያስተምራሉ።

Read 3824 times Last modified on Saturday, 10 April 2021 13:48