Monday, 12 April 2021 00:00

አትርሱ። ነገሩ፣ ምርጫ እንጂ፣ የሞት ሽረት ፍልሚያ አይደለም።

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

    • “አስታውስ፣ ሰው እንጂ አምላክ አይደለህም” ካሉ በኋላ፣ “ግን፣ ሰው ክቡር ነው” ብለው ቢጨምሩበት መልካም ነበር።
        • “አትርሳ፣ አመፅ ከችግር ይወለድ እንደሆነ እንጂ፤ መፍትሔን አይወልድም”። (ተከታይ ቢበዛልህም እንኳ)!
        • መፍትሔ ያለው፣ ከሰው ዘንድ ነው። አእምሮን በቅንነት ሲጠቀምና ለሥራ ሲተጋ፤ ነገርን ሁሉ ማሻሻል ይችላል።
             
             በጥንታዊቷ የሮም ከተማ የተፈጠረ ታሪክ ነው - ተያይዞ የመጥፋት አሳዛኝ ታሪክ - የጁሌስ ቄሳርና የተቀናቃኞቹ፣ የእልህና የአመፅ ታሪክ።  በጎራ ተቧድነው የጥላቻ አዙሪት ውስጥ ከገቡ በኋላ፣ ወደ ህሊና መመለስ ከባድ ነው። የሚያጋግል እንጂ የሚበርድ መካሪ ይጠፋልና።
እናም፣ እርስበርስ በጥርጣሬ እንደተጠማመዱ፣ ተከታትለው ጠፉ። እሱ አጣጣላቸው፣ እነሱ አጥላሉት። ተሳለቀባቸው፣ አሴሩበት። ምክርቤት አዳራሽ ውስጥ፣ በአመፅ ተረባርበው ወግተው ገደሉት። አመፅ ግን መፍትሔ አልሆነላቸውም። ጦር ዘመተባቸው። ገሚሶቹ አመፀኞች ራሳቸውን ገደሉ። ከአገር የተሰደዱትም አልተረፉም። በቄሳር አድናቂዎች የተመራ ጦር፣ የየገቡበት ገብቶ ጨረሳቸው።
ከመጠማመድ በፊትና በኋላ!
የሮም ታላቅነት፣ እንደ ድልድይ ነው ይባላል። ያለ ድልድይ፣ ሽግግር የለም። ሽግግሩ፣ ለበጎም ለክፉም ይሆናል። ወደ ምድረ ገነት ሊሆን ይችላል። ከማጡ ወደ ረመጡ፣ ከዘወትሩ ዓለም ወደ ጥልቁ ገሃምም ሊሆን ይችላል - ለውጡ።
የሆነሆኖ፣ ከየትም የሚመጣ፣ ወደየትም የሚሻገር ቢሆን፤ ለውጥ ከተባለ፣ ሁልጊዜ መሸጋገሪያ ድልድይ ይኖረዋል። ሁልጊዜ ደግሞ፣ ድልድዩ አደገኛ ነው። የሮም ስልጣኔም ከዚህ ውስጥ የሚመደብ ነው - አደገኛ ድልድይ።
ከግሪክ ስልጣኔ ማግስት የመጣ ነውና፣ የሮም ስልጣኔ፣ ደማቅ ወገግታ አልተለየውም። የጨለማው ዘመን ዋዜማ ነውና ጥቁር ደመና አጥልቶበታል።
በእርግጥ፤ የዛሬ 2000 ዓመታት ገደማ፣ የሮም ስልጣኔ፣ “መቼ ግዛቱ ተስፋፋና!” በሚል ስሜት፣ “ገና እያሟሟቀ ነበር” ሊባልለት ይችላል። ግን፣ ብልሽቱ እየጀማመረው ነበር። እንዲያም ሆኖ፣ ብርሃናማው የሥልጣኔ ውርስ፣ ያኔውኑ በቀላሉ የሚከስም አይደለም። ገና አልጨለመም። ሃያልነቱ አልተነካም። ሃብቱ ገና አልተሟጠጠም።
ከተሞች እየተስፋፉና እያደጉ እንጂ፣ እየፈረሱ አልነበረም፡፡ ከጥቂት ዓመታት በኋላ እንደሚፍረከረኩ ማን ገመተ? ወደ ኋላቀርነት ወደ ጨለማ ይመለሳሉ ብሎስ ማን አሰበ?
ለጊዜው ግን፣ የሮም ረዣዥም የንግድ መስመሮች፣ ገና በሽፍቶች አልተቋረጡም። መንገደኞችና ነጋዴዎች፣ ከሩቅ ከቅርብ ይመለሱባቸዋል። መንገዶች እየተሰሩ እንጂ ገና እየተበጣጠሱ አልነበረም። ናዳ እየወደረባቸው ተቀብረው አልተረሱም።
የሮም ከተማም፣ ገና  በጦርነት፣ በእሳትና በዝርፊያ ውበቷ አልረገፈም። እንዲያውም፣ ነዋሪዎችን የሚያረካ፤ እንግዳን የሚያስደምም ዕፁብ ድንቅ ከተማነቷ፣ የዘመኑ ወደር የለሽ ውበት እንደሆነ ማንም አይክደውም።
የዘመቻ ድልና ፌሽታ፣ አወዳሽና አጉዳፊ፣ ስጋትና አመፅ!
እንደወትሮው፤ አመፅን ለመቅጣት፣ ተቀናቃኝን ልክ ለማስገባት፣ ሰፊውን ግዛት ለማፅናት፣ ታላቋ ሮም፣ መሪዎችን በየጊዜው ትመድባለች። ጦር ታዘምታለች። የተላኩ መሪዎች በድል ሲመለሱ፣ ግርማዊቷ የሮም ከተማ፣ ከወትሮውም በላይ ትዋባለች። በነዋሪዎቿም ፍንደቃ፤ ይበልጥ ትንቆጠቆጣለች። በአበቦች አምራ ትደምቃለች።
ከግዙፍና ከግሩም ሕንጻዎቿ ጋር፤ ረዣዥም መንገዶቿ፣ በ”ውሮወሸባዬ”፣... በድል ዜማ፣ ይፍለቀለቃሉ። በድል አድራጊ ጦር ሰልፍና በአጀብ፣ በከበሮና በእምቢልታ፣ በጭፈራና በእልልታ፣ የሮም ከተማ ትሞቃለች። የዓለም መዲናነቷን ታውጃለች። በአዝናኝ የጦር ትርኢት ሕዝቡ ይደመማል። በነፃ ትግል የሞት ሽረት ፍልሚያ፣ ስታዲዬሙ ይቀወጣል። በትያትርና በሰርከስም፣ በምግብና በመጠጥ፣ ከተማዋ በፌሽታ  ትቀልጣለች። አንዳንዴም ትሰክራለች። “መሪያችን፤ ንጉሳችን” የሚል ድምፅ፣ ከሆይ ሆይታው መሀል ይስተጋባል።
የምን ንጉስ? ንጉስ አልነበራትም ሮም። ከንጉስ የሚያላቅቅ የሪፐብሊክ ስርዓትን መስርታለች፡፡ አነሰም በዛም፣ በቀጥታ እንዲሁም በተዘዋዋሪ የተመረጡ፣ በአዋቂነታቸው የተከበሩ፣ በስራቸው የታወቁ ሰዎችን ያካተተ ም/ቤት( ሰኔት) ነው፤ የሮም መንግስት አስኳል። መራሄ መንግስት፣ የክፍለ ግዛት አስተዳዳሪዎች የጦርነት መሪዎች የሚመደቡበትም በምክር ቤቱ ነው። ብዙ ጊዜ፣የምክር ቤት አባላት፣ በመሪነት ዘምተው በድል አድራጊነት ይመለሳሉ። ከዚህ ውጭ፣ ንጉስ የሚባል ነገር አልነበራቸውም። ክልክል ነው። ቢሆንም ግን…
በድል አድራጊነት ስሜት፣በእልልታና ጭፈራ በቀለጠው ጎዳና፤ ከስካር ሆይ ሆይታ መሃል፣ “ድል አድራጊ መሪያችን” “ንጉሳችን” የሚል ጩኸት ይበረታል። ጩኸቱ መሬት ሳይነካ በፊት፣ ከነካም ስር ሳይሰድ፣እዚያው አየር ላይ ጩኸት ብቻ ይቀራል። በአሸዋ ተቀብሮ መክናል። ንግስና በህግ ተከልሏል። ንጉሥነት አይፈቀድማ። አንዳንዴ ግን፣ ጩኸት በዝቶ፣ ህግን ያስንቃል።
በድል የተመለሰው የምክር ቤት አባል፤ (ሴናተር)፣ ያማረ ፈረስ ያጌጠ ሰረገላ ላይ ተቀምጦ፣ ወደ ሮም ሲገባ በደማቁ የአቀባበል እልልታ፣ ልቡ ይደነግጣል። የሰረገላው ነጂ፤ ተጨማሪ ስራ የተሰጠውም አለምክንያት አይደለም፡፡ “ሰው መሆንህን አስታውስ” እያለ ይናገራል - ለድል አድራጊው መሪ፡፡
ቢሆንም፣ የህዝብ ጩኸት ሃያል ነው። ድል አድራጊው መሪ፣ መላው አለም የዘመረለት ቢመስለው፣ “ንጉሳችን፤ ንጉሳችን” የሚለው ዜማ አናቱ ላይ ቢወጣበት አይፈረድበትም።
የህዝብ ጩኸት፣ ሲያወድስም ሲያጥላላም፣ ያሰክራል። ድል አድራጊው መሪ፣ ንጉስ የሆነ ሊመስለው ይችላል። ነገር ግን ባልደረቦቹ ከጎኑ አሉ። “አትርሳ፤ እንደኛው ሴናተር ነህ። ንጉስ አይደለም። ሮምን ንጉስ አይገዛትም” ይሉታል። በዚህም፣ ስካርን ወዲያው ፈጥነው ያበርዳሉ። ነገር ግን፣ ሁልጊዜ አይሳካላቸው። የሕዝብ ጩኸት ይበረታል። ስካር ይጦዛል።
“ንጉሳችን፣ ንጉሳችን” የሚለው ዜማ ከመክሰም ይልቅ፣ እየሰፋ እየገነነ ይመጣል። ምን ይሻላል? የሮም የሪፐብሊክ ስሪት ይፍረስ? ምክር ቤትና ምርጫ ተሽሮ፤ ንጉስ ይግዛት? ከዚያ ይልቅ፣ ራሱ ምክር ቤቱ፣ በራሱ ፈቃድ፣ የአባላቱ ድምጽ ተቆጥሮ፣ በምርጫ ቢወስንስ? ምክር ቤቱ ራሱ፣ ንጉስ ለመሰየም ቢስማማና ሕግ አውጥቶ ቢያውጅ አይሻልም? ለንጉስ ተገዢ መሆን ከባድ ሽንፈት ቢሆንም፤ ቢያንስ ቢያንስ፣ ንጉስ መረን እንዳይወጣ የሚያግዝ ምክር ቤትም ይኖራል። ሰኔቱ አይፈርስም። ለጊዜው ጥሩ መፍትሔ ነው ማለት ይቻላል። ግን፣ምን ዋጋ አለው?
ነገር ይባስኑ የሚበላሸው ገና በንግስናው እለት፣ በበዓለ ሲመቱ ነው። በበዓለ ሲመት ድግስ ከተማው በፌሽታ ስሜት እንደገና ይሰክራል። በሆይ ሆታ ክንፍ አብቅሎ መሬትን ለቅቆ በጭፈራ ይንሳፈፋል። ንጉሥ ሆይ፣ ሺ ዓመት ንገሥ እያሉ ይዘምራሉ። በዚሁ ማሳረግና መቋጨት ቢችሉ ይሻል ነበር። ግን፣  ሌላ አዲስ ጩኸት ገንኖ ይወጣል። “የዘላለሙ አዳኛችን። ጌታችን አምላካችን” የሚል ሆታ ከየጎዳናው ይስተጋባል።
“ፀሐዩ ንጉሳችን” የሚለው ዜማ፤ “ፀሐዩ አምላካችን" የሚል ውዳሴ ይመረቅለታል። ምን ይሻላል? የምክር ቤት አባላትና አማካሪዎች፣ ከንጉሱ አጠግብ ሆነው ሹክ ይሉታል። “ንጉስ ሆይ፣ ሰው ነህ፤ ንጉስ ሆይ ሰው መሆንህን አትርሳ” እያሉ ይወተውቱታል- በህዝብ ጩኸት እንዳይሰክር።
ታዲያ የአዋቂ ምክር የሚሰጡት፣ ጤናማ ተቀናቃኞች ብቻ አይደሉም። ብልህ ደጋፊዎቹም፣ መሪያቸውን ይመክራሉ። መንገዱን እንዳይስት፣ ከህሊናው እንዳይርቅ፣ በህዝብ ሆይ ሆይታ እንዳይሰክር ያሳስቡታል፤ ያባንኑታል።
ቀሽም መሪ ካልሆነ በቀር፣ የአማካሪዎቹን ማሳሰቢያና ተግሳፅ ቸል አይልም። አይጠላም። እንዲያውም፣ ይፈልገዋል። እውነታውን በግልጽ እንዲነግሩትና ሲሳሳት ፈጥነው እንዲያስታውሱት ትዕዛዝ ይሰጣቸዋል። “ተሿሚ እንጂ ንጉስ አይደለህም”፣ … “ሰው እንጂ አምላክ አይደለህም”…. እያሉ እንዲያስታውሱት ያዛቸዋል-። ለምን?
“ንጉሳችን! አምላካችን!” የሚል የህዝብ ጩኸት ሲደጋገምና ሲጋጋል፣ ህሊናን አሳጥቶ ሊያሰክር እንደሚችል አይጠፋውም- ብልህ መሪ። በሕዝብ ዘንድ የተጠላ ብቻ ሳይሆን የተወደደም፣ እንዲህ ይፈተናል። የህዝብ ደጋፍም፣ሆነ ተቃውሞ መቼም ቢሆን፣ ወደ ቅጥ የለሽ ጭፍን ስሜት ለመንሸራተት ያዘነብላል። ይህን መቋቋም የእያንዳንዱ መሪ ሃላፊነት ነው። ቀላል ፈተና አይደለም። ንጉስነቱን ሊያውጁለት፣ ዘውድ ሊጭኑለት የጎተጎቱት ባለስልጣናት ሞተዋል። አንዳንዶቹ በተቆርቋሪነት፣ ሌሎች በልወዳዳድ ባይነት። ሊያነግሱትም ዘውድ ሊጭኑለትም ሞክረዋል።
የጁሊየስ ቄሳር ምላሽ፤ “እኔ ቄሳር፣ እንጂ ንጉስ አይደለሁም” የሚል ነበር።
በአጭሩ፣ ጁሌስ ቄሳር፣ የከንቱ አወዳሾችን ፈተና ለማሸነፍ፣ በከፊልም ቢሆን ሞክሯል። ከራሱ ጥረትና ፅናት ጋር፣ የአዋቂ ደጋፊዎችና የጤናማ ተቀናቃኞች ምክር አግዞታል። ነገር ግን፣ ከንቱ አወዳሾችና አሳሳች ጭፍን ደጋፊዎች፣ በአንድ ወገን፣ በጥላቻ (በቅናት ወይም በፍርሀት) ወደ እልህ የሚያስገቡ ጭፍን ተቀናቃኞች ደግሞ በሌላ ወገን ነበሩ የሚበዙት። እንዲህ አይነት ሁኔታ፣ የውድቀት ዋዜማ ነው - ተያይዘው የሚጠፉበት ውድቀት።


Read 8851 times