Sunday, 11 April 2021 20:43

“የቴአትር ጥበብ ከመንግስት ጥገኝነት መላቀቅ አለበት” (ረዳት ፕ/ር ወርቁ ሙሉነህ)

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

  በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ትምህርት ክፍል ሀላፊና መምህር ነኝ። የሥርዓተ ትምህርቱን ክለሳ አውደ ጥናት እንድታደርጉ እንዴት ተመረጣችሁ ላልሺኝ፣ በሁለት ምክንያት ነው የተመረጥነው። አንደኛው ፍላጎቱ ከእኛ ስለመጣ ሲሆን ሁለተኛውና ዋናው ጉዳይ ግን ዩኒቨርስቲያችን እንደ ዩኒቨርስቲም እንደ ሃገርም ቴአትር ላይ በትልቁ ከፍተኛ ሥራዎችን እየሰራንና አስተዋእፆ እያደረግን ስለሆነ ነው፡፡ የዓለም የቴአትር ቀንን ከአንዴም ሁለት ጊዜ በዩኒቨርስቲያችን ትልልቅ የዘርፉ ባለሙያዎች በተገኙበት አክብረናል፡፡ ይህንን አዲስ አድማስም እንደ ሚዲያ ትልልቅ ሽፋኖችን በመስጠት ለታሪክ አስቀምጦታል። ኢትዮጵያ የዓለም የቴአትር ማህበር አባል የሆነችውም በወልቂጤ ዩኒቨርስቲ አማካኝነት አንጋፋው የጥበብ ሰው ጋሽ ደበበ እሸቱ ምስራቅ አፍሪካን ወክሎ በዓለም የቴአትር ማህበር ውስጥ ይሰራ በነበረበት ጊዜ በፈጠረልን ግንኙነት ነው። በነዚህና መሰል ስራዎች ለቴአትር እድገት እያደረግን ባለነው አበርክቶ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴሩ የክለሳ አውደ ጥናቱን እንድናዘጋጅ መረጠን፡፡ ዩኒቨርስቲያችንም ይህን ጉዳይ ስናቀርብለት ፈቃደኛ ሆኖ 15 ቀን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነው እንድናዘጋጅ ሁኔታዎችን ያመቻቸልን። በዚህ አጋጣሚ  የዩኒቨርስቲያችን ፕሬዝዳንትና የስራ ባልደረቦቻቸውንን በእጅጉ እናመሰግናለን፡፡
እንግዲህ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ይህን ክለሳ ሰርቶ እንዲያቀርብና ሌሎችም ዩኒቨርስቲዎች በዚህ በተከለሰው ስርዓተ ትምህርት እንዲያስተምሩ ሀላፊነት የሰጠው ለቀዳሚውና የሁሉም ዩኒቨርስቶዎች እናት ለሆነው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ነበር፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ይሆናል ይመጥናል ያለውን ሥርዓተ ትምህርት ቀርፆ አቀረበ። ነገር ግን ሌሎች ዩኒቨርስቲዎች ያልተወያዩበት በመሆኑና በተለይ ክፍለ ሀገር ያሉ ዩኒቨርስቲዎችን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ በመሆኑ እንዲሁም አንዳንዶቹ ኮርሶች የክፍለ ሀገር ዩኒቨርስቲዎች ለመስጠት የሚቸገሩባቸው ሆነው በመገኘታቸው አልተስማሙም፡፡
ስለሆነም ይሄ ጥያቄ ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ቀርቦ ክለሳ እንዲደረግበት፣ ይህንንም የክለሳ አውደ ጥናት እኛ እንድናዘጋጅ እውቅና ሰጠን፡፡ ስለዚህ መጋቢት 13 እና 14 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን ጨምሮ መቀሌ፣ አክሱም፣ ጎንደር፣ ደብረ ታቦር፣ ወሎ፣ ጂማና ሌሎችም ዩኒቨርስቲዎች እንዲሁም አንጋፋዎቹ ብሔራዊና ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤቶች ተሳትፈውበት ጥሩና የሁሉንም ዩኒቨርስቲዎች ነባራዊና ተጨባጭ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ውይይትና ክርክር ተደርጎ ስምምነት ላይ ደርሰናል። ይሔንን ስምምነት ላይ የደረስንበትን የተከለሰ ሥርዓተ ትምህርት ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እንልካለን። የመጨረሻ አስተያየት ተሰጥቶበት ከፀደቀ በኋላ ሁሉም ዩኒቨርስቲዎች ወጥና አንድ አይነት በሆነ የቴአትር ስርዓተ ትምህርት ማስተማር ይጀምራሉ ማለት ነው፡፡
ቴአትር እንደ ሀገር መፋዘዝ ውስጥ ነው ያለው የሚባለው ቴአትር እንዲነቃቃ ብዙ ስራ ይጠይቃል። የመጀመሪያው ነገር የቴአትር ጥበብ ከመንግስት ጥገኝነት መላቀቅና ነፃ መውጣት አለበት። ኪነ-ጥበቡ በኢኮኖሚ ነፃ እስካልሆነ ድረስ በምንፈልገው መንገድ ሳይሆን መንግስት በቀደደልን መንገድ ብቻ ይሆናል የምንሄደው። ይሄ ለአንድ ሀገር ኪነ-ጥበብ መውደቅ ትልቁ ምክንያት ነው፡፡ ጥበብ በባህሪው ነፃነት ይፈልጋል፡፡ አሁን ግን ጥበቡ በመንግስት ጥገኝነት ስር ስለሆነ፣ እኛም ምርጫ ስለሌለን በገበያው ላይ ትልቅ እንከን እየፈጠረ ነው፡፡
የኢትዮጵያ የቴአትር ታሪክ ብለን ማውራት አንችልም። በእኔ እምነት ቴአትር አዲስ አበባ ላይ ነው ታጥሮ ያለው። አዲስ አበባም ከአራት ቴአትር ቤቶች በደንብ እየሰሩ ያሉት ምናልባትም ሁለቱ ቢሆኑ ነው። እነሱም ቢሆን ነፃ ስላልሆኑ በፈለጉት መንገድ መንቀሳቀስ አይችሉም፡፡ ቢያንስ መንግሰት ኪነ-ጥበቡን ነፃ ቢያደርገውና ራሱን የሚችልበት መንገድ ቢፈጠር በፍጥነት ከመፋዘዝ ይወጣል፡፡ በሃሳብ በክንዋኔና በአጠቃላይ ሁኔታ ከፍ ያሉ፣ የተመልካችን ፊት ወደ ጥበብ የሚመልሱ ሥራዎች መስራት ይችላል፡፡ ነፃ እስካልሆነ ድረስ ግን ችግሩ እየተባባሰ ነው የሚሄደው የሚል እምነት ነው ያለኝ።




Read 1025 times