Saturday, 17 April 2021 11:27

“የጋራ እሴቶቻችን ለሀገራዊ መግባባትና ህብረብሔራዊ አንድነት ያላቸው ፋይዳ ምንድን ነው?”

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

  የኢፌዲሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮና ከመዳ ወላቡ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር፣ ሚያዚያ 4 እና 5 ቀን 2013 ዓ.ም በባሌ ዞን መቀመጫ ሮቤ ከተማ አራተኛውን የጥናትና ምርምር ጉባኤ “የጋራ እሴቶቻችን ለሀገራዊ መግባባትና ህብረብሔራዊ አንድነታችን ያላቸው ፋይዳ” በሚል ርዕስ አዘጋጅቶ ነበር። በዚህ ጉባኤ ላይ ምሁራን፣ ፖለቲከኞች፣ ደራሲያን፣ አርቲስቶችና ሌሎችም እንግዶች ታድመው ነበር፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ ምሁራን ጥናታዊ ፅሁፎችን ያቀረቡ ሲሆን በተለይም የጋራ እሴቶቻችንን አጉልተንና አክብረን ብንጠቀምና ተግባር ላይ ብናውል ለሀገራዊ መግባባትና ህብረት ብሔራዊ አንድነት ምን ያህል ፋይዳ እንደሚኖራቸው የሚያሳዩ ጥናቶች ቀርበዋል።
 በጉባኤው ከቀረቡት የጥናትና ምርምር ውጤቶች መካከል “የጋራ እሴቶቻችን ለብሔራዊ ተግባቦት መልማት፣ በጌዴኦና በጉጂ ማሕበረሰብ ተምሳሌትነት” የተሰኘውና በዲላ ዩኒቨርስቲው አዲሱ ዘገየ (ዶ/ር)፣ “የአርኪኦሎጂ ቅርሶቻችንና ብሔራዊ ተግባቦት፣ የሜጋሊቲክ ህብረተሰብ መልዕክቶች” በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲው አለባቸው በላይ (ዶ/ር)፣ ብዝኃነት፣ የሴቶች እኩልነትና የሰለጠነ ማህበረሰብ ግንባታ እሳቤዎች በዘመን ተሻጋሪ የኢትዮጵያ ፍልስፍና ውስጥ”፣ በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲው የፍልስፍና መምህር አቶ ኢያሱ በሬንቶ አሰፋ፣ “የኢትየዮጵያውያን የጋራ ዕሴት እድር፣ ለህብረብሔራዊ አንድነት”፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነ-ጽሁፍ አካዳሚ የባህል ተመራማሪ በሆኑት ፍሬህይወት ባዩ (ዶ/ር) “የጎጃምና የወለጋ ህዝቦች ማህበረ ባህላዊ እሴቶች ለአንድነትና ለሀገር ግንባታ ተምሳሌትነት”፣ በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲው ደሳለኝ መኩሪያ (ረ/ፕ) እና ሌሎችም በመደወላቡ ዩኒቨርስቲና በወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ምሁራን የተዘጋጁ ጥናታዊ ፅሁፎች ይገኙባቸዋል።
ሁሉም ጥናታዊ ጽሑፎች ኢትዮጵያዊያ ያላቸውን የጋራ እሴት በመጠቀም ልምድ በመለዋወጥና የአንዱን ባህል ሌላው በማወቅ ሊያመጣ የሚችለው ህብረ ብሔራዊ አንድነት ፋይዳ ትልቅ መሆኑ ነው፤ የጥናታቸው መዳረሻ።
በውይይቶች ወቅትም ጉልህ ሀሳብ ሆኖ በአዳራሹ  ሲናኝ የነበረው ኢትዮጵያ የብዙ ባህል፣ ወግና ስርዓት፣ የተፈጥሮና ሰው የሰራሽ ሀብቶች ያሏት ሀገር ብትሆንም ከዘርፉ ተጠቃሚ ያልሆነው ለምንድን ነው? ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን የጋራ እሴቶቻችንን እንዴት እንጠቀምባቸው? የጋራ እሴቶቻችንን የሚሸረሽሩ ዘርፈ ብዙ ችግሮችንስ እንዴት እንቅረፍ? የሚሉት በውይይቱም በጥናታዊ ፅሑፎቹም አፅንኦት ያገኙ ጉዳዮች ናቸው።
በዚህ ጉባኤ ላይ ከታደሙት ውስጥ እውቁ ምሁርና ፖለቲከና በየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር) አንዱ ሲሆኑ ባደረጉት ንግግር፤ አሁን አገራችን ላይ እየታ ያለው ችግር የጋራ እሴቶቻችንን በአግባቡ ካለመጠቀምና ለተከታዮቻችንም ካለማስተማር የመጣ ነው ብለዋል። አክለውም፤ “አሁን ላይ የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚሰሩ ጥቂት ሰዎች የራሳቸውን አጀንዳ ለማራመድ ሲሉ እየተጠቀሙብን እንደሆነና እኛም በዚህ ዕኩይ ሀሳብ ላይ በመንቃት፣ የጋራ እሴቶቻችንን በመጠበቅ ህዝቡንና ሀገራችንን ከሴረኞች መጠበቅ አለብን” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በጥናታዊ ፅሁፎቹ ዙሪያ ውይይት ተደርጎ ከተጠናቀቀ በኋላ በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የዲንሾና የሳነቴ መዳረሻዎችን ታዳሚዎች ጎብኝተዋል።


Read 1457 times