Print this page
Sunday, 18 April 2021 18:02

6 ሚ. ዩሮ የወጣበት የሾላ ወተት ማስፋፊያ ስራ ጀመረ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 በቀን ከ80-90 ሺህ ሊትር ወተት የማምረት አቅም አለው
                               
              ከሚድሮክ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ኩባንያዎች አንዱ የሆነውና በ6 ሚ.ዩሮ ማስፋፊያ የተደረገበት ሾላ ወተት ፋብሪካ ተመርቆ ሥራ ጀመረ፡፡ ላምበረት መናኸሪያ አካባቢ የሚገኘው ሾላ ወተት ፋብሪካ ማስፋፊያው ከመሰራቱ በፊት የሚድሮክ  ኢንቨስትመንት ባለቤት ሼህ መሃመድ አሊ አላሙዲ በመካከለኛው ምስራቅ አገራት የሚገኙ ትልልቅ የወተት ፋብሪካዎችን ከጎበኙ በኋላ ሾላ ወተት  በነዚያ የአረቡ አገር የወተት ፋብሪካዎች አይነት እንዲደራጅ በመፈለጋቸው፣ በዘመናዊ የጣሊያን ማሽኖችና ቴክኖሎጂዎች ተደራጅቶ ስራ መጀመሩም በምረቃው ዕለት  ተገልጿል::
ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት በሰለጠኑ ባለሙያዎችና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እየታገዘ፣ በቀን ከ80-90 ሺህ ሊትር ጥራቱን የጠበቀ ወተት የማምረት አቅም እንዳለው የተገለፀ ሲሆን፣እስ ከዛሬ ይሰራበት የነበረው ወተትን በላስቲክ የማሸግ ሥራ ቀርቶ ከውጭ በገቡና ጥራታቸውን በጠበቁ ፕላስቲክ ኮዳዎች በ250 እና በ500 ሚ.ሊትር ለገበያ እንደሚቀርብ ተጠቁሟል፡፡
ፋብሪካው በአሁኑ ሰዓት ራቅ ራቅ ካሉ የኦሮሚያ አካባቢዎች ማለትም ከሰላሌ ከደብረ ብርሀንና  ከጎጃምም ጭምር የወተት ምርትን በመሰብሰብ የሚሰራ ሲሆን፣ራቅ ካሉ አካባቢዎች ወተት የመቀበያ ባንኮችን በማቋቋም፣ የወተት ምርትን ለማሳደግ እየሰራ እንደሆነ  ተገልጿል፡፡ የወተት መቀበያ ባንኮቹ መቋቋም ለወተት አስረካቢውም ሆነ ለተረካቢው ምቹ ሁኔታን ከመፍጠሩም በላይ እስከ ዛሬ “ወተት ገዢ አጣን” የሚለውን አርሶ አደርም ሆነ ጥራት ያለው ወተት አጣሁ ብሎ ሲያማርር የነበረውን የወተት ፋብሪካ  ጥያቄ የሚመልስ  ነው ተብሏል፡፡ 400 ለሚሆኑ ሰራተኞች የስራ ዕድል በፈጠረው በዚህ የፋብሪካ ማስፋፊያ ምርቃት ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ም/ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤና የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ፤ አብዲሳ ሪቫኑን ከቆረጡና ከጎበኙ በኋላ ወተቱን ቀምሰው አድናቆታቸውን ገልፀዋል፡፡ ሚድሮክ ኢትዮጵያ፤ ሾላ ወተትን በኢትዮጵያ ሚሊኒየም በ2000 ዓ.ም በ66 ሚሊዮን ብር በመግዛት የሚደሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ አካል ማድረጉ አይዘነጋም፡፡


Read 2233 times