Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 18 August 2012 14:12

ከድሬዳዋ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ የተሰጠ ማስተባበያ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

“በድሬደዋ የናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ብናኝ ለጤና ጠንቅ ሆኗል” በሚል ርዕስ ቅዳሜ   ነሐሴ 5 ቀን 2004 ዓ.ም በአዲስ አድማስ ጋዜጣ የወጣውን ጽሑፍ በተመለከተ ፋብሪካው የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቷል፡፡

ድርጅታችን መንግስት ከሚከተለው የተቀናጀ የአረንጓዴ ልማት እድገት አቅጣጫ (Climate Resilient Green Economy Growth) በመነሳት የአካባቢ ብክለት በአየር ንብረት ብሎም በዜጐች ደህንነት ላይ ሊፈጠር የሚችለውን ተጽእኖ ለመቆጣጠር የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

ከነዚህ ጥረቶች መካከል የሚከተሉት ተጠቃሾች ናቸው፡፡

የአካባቢ ብክለት ቁጥጥር አዋጅ 300/1995 በሚደነግገው መሠረት የአካባቢ ብክለት ኦዲት (Environmental Audit) ጥናት ማካሄዱ፣

ከጥናቱ ግኝቶች በመነሣት የማሻሻያ ድርጊት መርሃ ግብር (Corrective Action Plan) መንደፉ፣

ይህን የዳሰሳ ጥናት እና የድርጊት መርሃ ግብር ለድሬዳዋ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ለግምገማ ማቅረቡ፣

በድርጊት መርሃ ግብሩ መሠረት ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩ፣

አዲስ በመገንባት ላይ ላለው ግዙፍ የሲሚንቶ ፋብሪካ በገለልተኛ ባለሙያዎች የአካባቢ ተጽእኖ ዳሰሳ ጥናት ተካሂዶ፣ በድሬዳዋ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን አጽድቆ የግንባታ ሥራም ጀመሩ፣

ድርጅታችን ከመስተዳድሩና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በአካባቢ ጥበቃና በሌሎች የጋራ ጉዳዮች ላይ በቅንጅት የሚሰራ መሆኑ፣

የአካባቢው ነዋሪዎች ነፃ የመጠጥ ውሃ አገልግሎት እንዲያገኙና በተጨማሪም የአካባቢው ህብረተሰብ የሚገለገልባቸው የትምህርትና የጤና ተቋማት ለማስገንባት በዕቅድ መያዙ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ድርጅታችን የአካባቢ ብክለትን ለመቆጣጠር ከሚያደርገው ጥረት ጐን ለጐን ከላይ በተጠቀሰው አዋጅ እንዲሁም ተዛማጅ መመሪያዎችና ደንቦች በአገር አቀፍ ደረጃ የተቀመጠውን የብናኝ ልቀት መጠን አክብሮ ስራውን በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

ሁኔታውን በማስረጃ ለማስደገፍ ያህል፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቀመጠው የብናኝ ልቀት መጠን 150 microgram/m3 ሲሆን፣ በአንፃሩ ፋብሪካው መደበኛ የምርት ሂደቱን በሚያከናውንበት ወቅት የሚያወጣው የብናኝ መጠን በፋብሪካው ቅጥር ግቢ ውስጥ 132 microgram/m3 መሆኑ ከላይ በተጠቀሰው ጥናት ተረጋግጧል፡፡

የሀገር አቀፍ የልቀት መጠን ደረጃ ከተቀመጠበት መሠረታዊ አላማዎች ማለትም የአየር ንብረት ብክለትን መከላከልና የማህበረሰቡን ደህንነት ከማስጠበቅ ግቦች አኳያ ሲታይ፣ የፋብሪካችን የልቀት መጠን በሚገኝበት ደረጃ በጋዜጣው እንደቀረበው በአካባቢው ማህበረሰብ ጤንነት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሣድሯል የሚል ድምዳሜ ላይ ለመድረስ የሚያስችል አይደለም፡፡

ኩባንያችን የልቀቱን መጠን ከዚህ በበለጠ በመቀነስ በአካባቢው ነዋሪዎች ደህንነት ላይ ምንም አይነት አሉታዊ ተጽእኖ የማይፈጥርበት ደረጃ ላይ ለማድረስ ያልተቆጠበ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

ኩባንያችን ከብር 1.8 ቢሊዮን በላይ መዋዕለ ንዋይ በመመደብ በድሬዳዋ ከተማ በቀን 3000 ቶን ክሊንከር የማምረት አቅም ያለው ፋብሪካ በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡

ይህ 3000 ቶን ክሊንከር የማምረት አቅም ያለው ግዙፍ ፋብሪካ ግንባታው ተጠናቆ የምርት ሙከራ በመጀመር (Commissioning) ሂደት ላይ የሚገኝ ሲሆን በቅርብ ወራት ውስጥ ወደ ማምረት ደረጃ ይሸጋገራል፡፡

አዲሱ የሲሚንቶ ፋብሪካ የማምረት ስራ ሲጀምር በአገሪቷ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣውን የሲሚንቶ ፍላጐት ለማሟላት ጉልህ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡

አዲሱ ፋብሪካ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሚታገዝ በመሆኑ የአካባቢ ብክለትን በተመለከተ የአገር አቀፍ ደረጃ እና ብሎም የአለም አቀፍ ደረጃዎችን እንደሚያሟላ ይታመናል፡፡

አዲሱ ፋብሪካ ስራ ሲጀምር አሁን በስራ ላይ የሚገኘው ፋብሪካ የተወሰነ የማሻሻያ ለውጥ ተደርጐለት፣ ሌሎች የሲሚንቶ ተጓዳኝ ምርቶችን እንዲያመርት ይደረጋል፡፡

በመጨረሻም ኩባንያችን የአካባቢ ብክለትን ለመቆጣጠር ለደነፈው መርሃ ግብር ተግባራዊነት ከድሬዳዋ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን እንዲሁም ከማህበረሰቡ ጋር የሚያደርገውን የተቀናጀ ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

 

 

 

Read 3874 times Last modified on Saturday, 18 August 2012 14:14