Saturday, 24 April 2021 13:19

32ኛው ኦሎምፒያድን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ያራቅቁታል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

  • ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ በተለያዩ ፕሮጀክቶች ወጥቷል
        • ከ80ሺ ቶን የሞባይል ቀፎዎችና የኤሌክትሮኒክስ መሳርያዎች 5ሺ ሜዳልያ ተሰርቷል፡፡
        • በ400 ቶን የፕላስቲክ ጠርሙሶች የሽልማት መድረኮች ተሰርተዋል
        • ሾፌር አልባ መኪኖች እና ሮቦቶች በሺዎች ይሰማራሉ

             ጃፓን የምታስተናግደው 32ኛው ኦሎምፒያድ በዓመት መራዘሙ ከ2.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ቢያከስርም በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በመራቀቅ  መላው ዓለምን እንደሚያስደምም ተጠብቋል፡፡ ከሳምንት በፊት ከጃፓን የወጡ ዘገባዎች የኮሮና ወረርሽኝ ምናልባትም ኦሎምፒኩ በድጋሚ እንዲራዘምና ምናልባትም ሙሉ ለሙሉ እንዲሰረዝ ተፅእኖዎች እንዳሳደረ ያመለክታሉ፡፡ አንዳንድ የጃፓን ባለስልጣናትም በ2032 እኤአ ላይ ጃፓን የመስተንግዶ እድሉን  በድጋሚ እንድታገኝ ይጠየቅ ብለውም  ሃሳብ አቅርበዋል፡፡ ታዋቂ የጃፓን  የብሮድካስት ኩባንያ ኤንኤችኬ ከጃፓናውያን በሰበሰበው ድምፅ 77 በመቶው ኦሎምፒኩ እንዲሰረዝ ወይም በድጋሚ እንዲራዘም እንፈልጋለን ብለዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ቶኪዮ 2020 በኦሎምፒክ ታሪክ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸውን ኣዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ተግባር ላይ በማዋል የሚስተካከለው አለመኖሩ ተዘግቧል፡፡ ከኦሎምፒኩ በተገናኙ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ፕሮጀክቶች እስከ 10 ቢሊዮን ዶላር በላይ በጃፓን መንግስትና በትልልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች  ወጭ ተደርጓል፡፡ ይህም ሁኔታም የጃፓን ዝግጅትን በኦሎምፒክ የተራቀቀ እና ጊዜውን የቀደመ አድርጎታል። ጃፓን ከፍተኛ ደረጃ የደረሰችባቸውን የኦሎምፒክ ቴክኖሎጂዎች በማስተዋወቅ ከቱሪዝም ያጣችውን ገቢ የሚያካክስ ከፍተኛ የኢኮኖሚ መነቃቃት እንደምትፈጥርበትም ተጠብቋል። በአሎምፒክ ታሪክ በ1912 እኤአ ላይ በስቶክሆልም የኤሌክትሮኒክ ስቶፕ ዎች ሲተዋወቅ፤ በ1936 እኤአ በበርሊን ኦሎምፒክ ደግሞ ዓለም አቀፍ የቴሌቭዥ ስርጭት ተጀምሯል፡፡ በ1964 እኤአ ላይ የጃፓኗ ቶኪዮ ባስተናገደችው አሎምፒክ ሼንካሱኒ የተባለ የዓለማችን ፈጣን ባቡር የተዋወቀ ሲሆን በቶኪዮ 2020 ላይም 601 ኪሜትር በሰዓት የሚወነጨፍ ባቡር ይተዋወቃል፡፡
ለ32ኛው ኦሎምፒያድ በቅድሚ ከተዋወቁ ልዩ የቴክኖሎጂ ምርቶች የመጀመርያው የወርቅ፤ የብርና፤ የነሐስ ሜዳልያዎች የተሰሩበት መንገድ ነው፡፡  ለኦሎምፒያዱ የሚሸለሙ 5000 የወርቅ ፣ የብርና የነሐስ ሜዳልያዎች የተሰሩት በሁለት ዓመታት ከጃፓናውያን ላይ በተሰበሰቡ 80,000 ቶን የሚመዝኑ  6.21 ሚሊዮን ሞባይል ስልኮችና፤ ያገለገሉ አነስተኛ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ተሰርተዋል፡፡ ከሞባይሎቹ እና ከኤሌክትሮኒክስ መሳርያዎቹ ወደ 32 ኪሎ ግራም ወርቅ ፣ 3,500 ኪሎ ግራም ብር እና 2,200 ኪሎ ግራም ነሐስ ተገኝቷል፡፡ ፒ ኤንድ ጂ የተባለ ኩባንያ ደግሞ የሽልማት ስነስርዓት የሚካሄድባቸውን  መድረኮች ከፕላስቲክ ጠርሙሶችና ሌሎች ቁሶች አምርቷቸዋል። ከ400 ቶን በላይ የፕላስቲክ ጠርሙሶችና የፕላስቲክ ቆሻሻዎች  በመጠቀም የሽልማት መድረኮቹ ተሰርተዋል፡፡
 በጃፓን በተለያዩ ከተሞች በተገነቡ 40 የኦሎምፒክ መወዳደርያ ስፍራዎች ላይ በተካሄዱ ግንባታዎች 95 በመቶው የካርቦን ልቀት የሌላቸው፤ መልሰው ጥቅም ላይ የሚውሉና ለአዲስ ሁኔታ የሚቀየሩ መሆናቸው ሌላው አስደናቂ እድገት ነው፡፡ ሃይድሮጅን ጋዝን በመጠቀም በውሃ እና በኤሌክትሪክ የሃይል አገልግሎት የሚንቀሳቀሰው ኦሎምፒኩ ምንም አይነት ብክለት ላይፈጥር መቻሉም አድናቆት አትርፏል፡፡
የአሎምፒኩ የመክፈቻ ስነስርዓትን ከሚያደምቁ ትርኢቶች ዋንኛው እስከ 4 ሚሊዮን ዶላር ወጭ የሆነበት የክዋክብት ርችት ነው፡፡ የጠፈር መዝናኛዎች በመስራት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ እውቅና ያለው አስትሮ ላይቭ የተባለ ኩባንያ የክዋክብት ስባሪዎች በምድር ላይ የዘነቡ እስኪመስል በቀለማት ያሸበረቀ ሰው ሰራሽ የክዋክብት ርችት ይተኮሳል፡፡
ታላላቆቹ የመኪና አምራች ኩባንያዎች ኒሳንና ቶዮታ በሺዎች የሚቆጠሩ ሾፌር አልባ መኪናዎችንና ሮቦቶችን ለተለያዩ አገልግሎቶች ያቀርባሉ፡፡ ለተሳታፊ ኦሎምፒያኖች፤ ልዑካኖቻቸው  መረጃ በመስጠት፤ በውድድር ሜዳዎች መወዳደርያ የስፖርት ቁሶችን በማጓጓዝ፤ በኦሎምፒክ መንደር እና በውድድር ስፍራዎች የሚንቀሳቀሱትን ሁሉ በማመላስ የሚሰሩ ቴክኖሎጂዎችንም ኩባንያዎቹ ያስተዋውቃሉ፡፡ ኦሎምፒኩ ከመጀመሩ ከ1 ወራት ቀደም ብሎ በማሰማራት ልዩ ፍትሻ ያደርጋሉ፡፡ የሁለቱ ኩባንያዎች ሚኒ ባስ መሰል ተሽከርካሪዎች ኦሎምፒክ መወዳደርያ ስፍራዎች ላይ በመዘዋወር ለእግረኞች የሊፍት አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ ሾፌር አልባ መኪናዎቹ ከኦሎምፒክ በኋላ ተጨማሪ ስራዎች ተከናውነውባቸው እስከ 2025 እኤአ ለዓለም ገበያ እንደሚቀርቡም ታውቋል፡፡
በተለይ የቶዮታ ኩባንያ ተጨማሪ አገልግሎት የሚሰጡ ሮቦቶችን በማሰማራት ኦሎምፒኩን ከቴክኖሎጂዎች ጋር ያስተሳስራሉ። ቶዮታ የሚያሰማራቸው ተሽከርካሪ ሮቦቶች በሜዳ ላይ በሚካሄዱ የስፖርት ውድድሮች ንቁ ተሳትፎ ያደርጋሉ፡፡ ለምሳሌ የተወረሩ ጦሮች፤ ዲስከሶች እና አሎሎዎችን ያመላልሳሉ፡፡ ለአካል ጉዳተኞችና ለአቅመ ደካሞች ውሃ እና ሌሎች ነገሮችን በማቀበልና መረጃ በመስጠት ይሰራሉ።
የኦሎምፒክ አዘጋጆች እንደገለፁት  ደግሞ የኦሎምፒኩ እና የፓራሊምፒክስ ሁለት የማስኮትት ሮቦቶች ቢያንስ እስከ 1000 የኦሎምፒክ ተሳታፊዎችን ድጋፍ እንደሚሰጡ ነው፡፡  በኦሎምፒክ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በውድድሩ ላይ የሚሰማሩ የኦሎምፒክ ማስኮቶች በሮቦቲክ ቴክኖሎጂ የተዘጋጁ ሆነዋል፡፡ ስለ አሎምፒክ መረጃ የሚሰጡ እና የሚያሟሙቁ አስተናጋጆች ናቸው፡፡የኦሎምፒኩን መድረክ የሚያስተናግዱት  እኝህ ልዩ ሮቦቶች አትሌቶችን እና ተመልካቾችን በውድድር ቀናት ይቀበላሉ፣ በውድድር ስፍራዎች ተገኝተው ድጋፍ በመስጠት ይሰራሉ። የቶኪዮ 2020 ኦፊሴላዊ የኦሎምፒክ ማስኮት ሮቦቶች እንግዶችን በማውለብለብ፣ እጅ በማጨብጨብ እና ሰላምታ የሚያቀርቡ እና ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጡ ናቸው፡፡ በግንባራቸው ላይ የተለያዩ የፊት ገጽታ እና ካሜራዎች ስላሏቸው ሰዎች በአቅራቢያ ባሉበት ጊዜ እንዲገነዘቧቸው እና ምላሽ እንዲሰጡ ያስችላቸዋል ፡፡ በአሎምፒክ መንደር ውስጥ ተሳታፊዎችን ያስተናግዳሉ፤ ያጫውታሉ፤ ያዝናናሉ እንዲሁም ልዩ ልዩ ድጋፍ ይሰጣሉ፡፡
ኔክ ኮርፖሬሽን ለኦሎምፒኩ ያበረከተው ደግሞ ‹‹ኢፌስ›› የተባለ የኦሎምፒክ ተሳታፊዎችን መልክ እንደ መታወቂያ መምርሮ ለማረጋገጥ የሚጠቀም አዲስ ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ይህ የፊት ገፅን በካሜራ በመቅረፅ ልዩ የማንነት ማረጋገጫ ካሜራ በመታወቂያ ቁጥጥር ያለውን አሰልቺ ሂደት የሚያቃልል ነው፡፡ በየኦሎምፒክ መድረኮቹ ከ300ሺ በላይ ኦሎምፒያኖች የፊት ገፆችን እንደመታወቂያ መዝግቦ እንቅስቃሴያቸውን ያቀላጥፍላቸዋል፡፡
ከኦሎምፒክ ዓለም አቀፍ ስፖንሰሮች አንዱ የሆነው ኢንቴል በቨርችዋል ሪያሊቲ ታላቁን የስፖርት መድረክ ልዩ ገፅታ እንደሚያላብሰውም ተጠብቋል፡፡ ወቅቱን በጠበቀ የዲጅታል ቴክኖሎጂ መነፅር የኦሎምፒክ ሽፋኑን ያደምቀዋል ነው የተባለው፡፡ ኢንቴል ለኦሎምፒኩ ዓለም አቀፍ ስፖንሰር ሲሆን ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን የጠበቁ ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ ኦሎምፒያኖች፤ የስፖርት አፍቃሪዎች እና ተመልካቾች እንዲሁም አዘጋጆችን የሚያረካ ልዩ ልምድ እፈጥራለሁ የሚል መግለጫ አውጥቷል፡፡ በ5ጂ ቴክኖሎጂ አማካኝነት ውድድሮች፤ ልምምዶች እና ሌሎች የኦሎምፒክ ድባቦችን በደመቀ ሁኔታ ለማሰራጨት ነው፡፡
ከ206 አገራት የሚመጩ ልዑካንን በቋንቋዎቻቸው ለማስተናገድ ከጃፓንኛ ወደ እስከ 27 የዓለም ቋንቋዎችን የሚተረግሙ አፕሊኬሽኖችም ጥቅም ላይ የሚውሉ ሲሆን ፓናሶኒክ ኩባንያ በዚህ ቴክኖሎጂ ላይ የተሳተፈው የጃፓን ቋንቋን ወደ አስር ቋንቋ የሚተረጉም አንገት ላይ የሚንጠለጠል መሳርያ በማምረት ነው፡፡
የኦሎምፒክ ዓለም አቀፍ ስፖንሰር የቻይናው አሊባባ ግሩፕ በኦሎምፒኩ ድምቀት ላይ የበኩሉን ተሳትፎ ያደርጋል፡፡ ከጃፓን ትልልቅ ኩባኑያዎች ጋር በሚሰረታበት እቅድ ለኦሎምፒኩ ልዩ ሽፋን የሚሰጡ ትልልቅ ግዙፍ ስክሪኖችን ይሰቅላል፡፡ በሻርፕ ኤሌክትሮኒክስ በኦሎምፒኩ የሚተዋወቀው 85 ኢንች ቲቪ እስከ 130ሺ ዶላር ያወጣል፡፡

Read 3347 times