Monday, 26 April 2021 00:00

ገንዘቤ በኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያ ትፈልጋለች

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

      ‹‹አትሌቶች የኮሮና ቫይረስ ክትባት ከወሰዱ አሎምፒኩ ምቹ ይሆናል››

          ኢትዮጵያዊቷ ምርጥ የመካከለኛ ርቀት ሯጭ ገንዘቤ ዲባባ በቶኪዮ 2020 ላይ አትሌቶች የኮረና ቫይረስ ክትባት ከወሰዱ ኦሎምፒኩ ምቹ እንደሚሆንና የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያን ለማግኘት እንደምትፈልግ አስታወቀች። በ32ኛው ኦሎምፒያድ ላይ ለሚሳተፉ አትሌቶች ቅድሚያ ትኩረት መሰጠት እንዳለበት ያመለከተችው ኦሎምፒያኗ፤ በኦሎምፒክ መወዳደርያ ስፍራዎች ከሌሎች አትሌቶች ጋር በነፃነት ለመቆየት እና ለመወዳደር ክትባት መውሰዱን ወሳኝና አስፈላጊ ያደርገዋል ነው ያለችው፡፡ ዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ተሳታፊዎች ለወረርሽኝ እንዳይጋለጡ ከፍተኛ የቁጥጥር ስራዎችና ጥበቃዎችን እንደሚያደርግ ሙሉ እምነት እንዳላትም ተናግራለች፡፡
ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ 32ኛውን ኦሎምፒያድ ለማካሄድ የተለያዩ መመርያዎችን አውጥቷል፡፡ ለሶስት የተለያዩ የኦሎፒክ ማህበረሰቦች የሚሆኑ ማኑዋሎችን አዘጋጅቶም አሰራጭቷቸዋል፡፡ ዓለም አቀፍ ተመልካቾች ወደ ጃፓን እንዳይገቡ መወሰኑ ከርምጃዎቹ አንዱ ሲሆን በኦሎምፒክ መንደር እና የስፖርት መድረኩ በሚያልፍባቸው የጃፓን ከተሞች ርቀትን መጠበቅ በልዩ መመርያ ተግባራዊ ይሆናል፡፡ በኦሎምፒክ መንደር እና በውድድር ስፍራዎች በተደጋጋሚ የኮሮና ምርመራ እና የሙቀት መለካት ስራዎች ይኖራሉ፡፡ እንዲሁም የኦሎምፒኩ ተሳታፊዎች በየአገራቸው ክትባታቸውን ወስደው  እንዲገቡ ይበረታታል፡፡
ኦሎምፒያኗ ገንዘቤ 32ኛው ኦሎምፒያድ ልክ 100 ቀናት ሲቀሩት ከስታት ፕርፎርም ኒውስ ጋር ባደረገችው አጭር ቃለምልልስ ላይ ስለ ኦሎምፒክ ተሳትፎዋም ተናግራለች፡፡  በኮሮና ወረርሽኝ የተነሳ የኦሎምፒክ ዝግጅትና የልምምድ መርሃግብሮችን ተዛብተውብኝ ነበር  ያለችው ገንዘቤ  በ1500 ሜትር ለመሳተፍ ተስፋ ማድረጓንና ዋንኛው ትኩረቷ የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያ ማግኘት እንደሆነ ነው የጠቆመችው፡፡
በ1500 ሜትር የዓለም ሪከርድን ከ6 ዓመት በፊት በዓለም አትሌቲክስ በቤጂንግ የዓለም አትሌቲስ ያሸነፈችው የወርቅ ሜዳልያ ግዙፍ ውጤቷ ነው፡፡ የብራዚሏ  ሪዮ ዲጄኔሮ ባስተናገደችው 31ኛው ኦሎምፒያድ ላይ በኦሎምፒክ የመጀመርያ ተሳትፎዋን አድርጋ በመካከለኛ ርቀት የመጀመርያውን የብር ሜዳልያ ለራሷና ለኢትዮጵያ አስመዝግባለች፡፡ከገንዘቤ በፊት በ2012 እኤአ በለንደን አሎምፒክ ላይ በ1500 አበባ አረጋዊ ለኢትዮጵያ በመሮጥ የብር ሜዳልያ ማስገኘቷ እና ከዚያ በኋላ ዜግነቷን ወደ ስዊድን እንደቀየረች ይታወሳል፡፡
አትሌት ገንዘቤ ስለቶኪዮ 2020 የሰጠችውን አስተያየት በርካታ የዓለም ሚዲያዎች የተቀባበሉት ሲሆን ስለ ሜዳልያ እድሏም ያነሳቸውን ሃሳቦች ፅፈውታል፡፡ ‹‹በመዘጋጀት ላይ ያለሁት ለኦሎምፒክ እንጅ ለዓለም ሪከርድ አይደለም፣ ከኦሎምፒክ በኋላ ግን የዓለም ሪከርድን ለማሻሻል አንድ ሙከራ አደርጋለሁ›› በማለትም አስተያየት ሰጥታለች፡፡ ‹በማንኛውም ውድድር ላይ   ጠንክሮ የሚሰራው ተወዳዳሪ ሪከርድ ሊያሻሽል ይችላል፡፡
ቶኪዮ ላይ ለሪኮርድ የሚሮጥ ካለ ውድድሩ ላይ እኔም አለሁበት›› ያለችው፡፡ በ1500 ሜትር የዓለም ሪከርድን በ2015 እኤአ ላይ ገንዘቤ ያስመዘገበችው 3:50.07  በሆነ ጊዜ ሲሆን የኦሎምፒክ ሪከርድን 3:32.07  በሆነ ሰዓት በ2000 እኤ ላይ ሲድኒ ላይ ያስመዘገበችው የኬንያዋ ኖህ ኔጀነኒ  ናት፡፡
አትሌት ገንዘቤ ዲባባ በቶኪዮ 2020 ላይ ከተጠበቁ የኢትዮጵያን ኦሎምፒያኖች አንዷ ብትሆንም በሴቶች 1500 ሜትር የኦሎምፒክ ውድድር ላይ ሌሎች ምርጥ አትሌቶች መኖራቸውንም መጥቀስ ያስፈልጋል፡፡ ኦሎምፒክፕሪዲክሽን በሰራው ትንበያ  ለገንዘቤ ዲባባ የሜዳልያ እድል አልተሰጣትም፡፡ የወርቅ ሜዳልያ እንደምታሸንፍ ግምት የወሰደቸወ ለሆላንድ የምትሮጠውን ሲፋን ሃሰን ስትሆን፤  የኦሎምፒክ ሻምፒዮንነቷን ለማስጠበቅ የምትገባው ኬንያዊቷ ፌይዝ ኪፕዮጌን የብር ሜዳልያ እንደምትወስድና ኢትዮጵያዊቷ ጉዳፍ ፀጋይ የነሐስ ሜዳልያውን እንደምትወስድ አመልክቷል፡፡
ሶስቱ አትሌቶች ከ2 ዓመት በፊት በ17 ኛው  የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዶሃ ላይ በሴቶች 1500 ሜትር የፍፃሜ ውድድር ላይ ከፍተኛ ፉክክር አድርገዋል፡፡ እንደቅደም ተከተላቸውም የዓለም ሻምፒዮና ሜዳልዎችን ተጎናፅፈዋል። ከላይ ከተጠቀሱት ኦሎምፒያኖች ባሻገር በ32ኛው ኦሎምፒያድ ላይ በተመሳሳይ ርቀት የሚጠቁ የቻይና እና የራሽያ እና የምስራቅ አውሮፓ አገራትን የሚወክሉ ኦሎምፒያኖች ናቸው፡፡
ኬንያዊቷ ፌይዝ ኪፕዮጌን በሪዮ ኦሎምፒክ በ1500 ሜትር የወርቅ ሜዳልያ ከወሰደች በኋላ በረጅም ርቀት የ5ሺ እና 10ሺ ሜትር ውድድሮች ስትሳተፍ ቆይታለች፡፡ በተለይ በ10ሺ ሜትር የዓለምን ሪከርድ በሁለት ውድድሮች ለጥቂት አምልጧታል፡፡
በቶኪዮ 2020 ላይ የኦሎምፒክ ክብሯን ለማስጠበቅ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት ስትናገር ዋና ተቃናቃኟ  ሲፋን ሃሰን  መሆኗን ነው የገለፀችው፡፡  ኢትዮጵያዊት ጉዳፍ ፀጋይም በመካከለኛ ርቀት ኦሎምፒኩን ከሚያደምቁት መካከል ስሟ የተጠቀሰው ባለፈው ዓመት የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሪከርድን በ1500 ሜትር በማስመዝገቧ ነው፡፡


Read 8033 times