Saturday, 01 May 2021 13:59

የፍቅር ምትሃት

Written by  መሳይ ደጉአለም
Rate this item
(7 votes)

     ያው እድለኛም አይደለሁ...
ታዋራኛለች!
ደፍሬ ስልኳን የጠየኩበት ቀን ትዝ ይለኛል።
ልዩ መሆኗ ግልፅ ነው... ድፍረቴ ቀርቶ!
“ይሄን ነገሬን ባትወደውስ?” ብዬ መስጋቴ ሌላ ታሪክ ነው!
ሰው እንዴት “ድምፄን ባትወደውስ?” ብሎ ይሳቀቃል?
እንደው ስንት አይነት ድምፅ ቢኖር ነው?
ብቻ እንዳልኩት እድለኛ ነገር ነኝ!
የመጀመርያ ቀን ደውዬላት፣ ቆንጆ ድምፅ እየሰማሁ ስቁነጠነጥ...
“ወይኔ መስዬ... ድምፅህ እንደዚህ የምስኪን ነው? እዛ ‘ፌስቡክ’ ላይ ስትፅፍ እኮ የሆነ አስፈሪ ኮስታራ ድምፅ ያለህ ነው የምትመስለው! “ አለቺኝ...
ኮስታራ ድምፅ እንዴት ያለው ነው?
Is ምስኪን ድምፅ a compliment?
ብቻ ከእነ ውዝግቤ የተጨመረልኝም የድምጿን በረከት እየባረክሁ ጥቂት ጊዜ አለፈ...
“አግኚኝ” ለማለት እስክደፍር...
በዚህ ጥቂት ጊዜ በስሟ እልፍ ግጥም ፃፍኩ...
ከእልፍ ቆነጃጂት ተኳረፍኩ...
እልፍ የፍቅር ዘፈን ተረጎምኩ...
ፍቅር፤ ፀሀፊ የሚያደርገው ነገር ሳይኖር አይቀርም!
‘ከፖስቶቼ’ ስር አስቀምጣ በምታልፈው ቀይ የልብ ቅርፅ፣ የልብ ልብ ተሰምቶኝ፣ እንድታገኘኝ መወትወት የጀመርኩበት ደፋር ሰሞን...
“የምትወደኝ መስሎኝ እኮ ነው...” ብላ አስደነገጠችኝ!
ለምን አልወዳትም?
አጭር እንደሆነች የማላውቅ መስሏት ይሆን?
ስንት ሰው ጠይቄ ስታወራ nervous እንደሆነችና እጆቿ እንደማያርፉ ያልሰማሁ መስሏት ይሆን?
“እንዴ... እወድሻለሁ እንጂ! ለምንድነው እማልወድሽ?” አልኳት ኮስተር ብዬ...
“ባክህ የመሰልኩህን ሴት ነው የምትወዳት፤ እኔን አይደለም! አታውቀኝም! ብታውቀኝ Lewis Capaldiን... Joel Corryን... አትጋብዘኝም... እየተረጎምክ በስሜ አትለጥፍልኝም ነበር! አብነት አጎናፍር ምን አለህ...?” አለቺኝ እንደማምረር እያደረጋት...
ጀንጃኝ ጎኔ አፍሮ ሲሽኮረመም egoዬ ምላሴን ተረክቦ... “እንዴ... እንዴ... ይኸው ልደታን! እሁድ እንደውም... Palmy የሚባል ቤት አብነትን ካላየን... ብዬ ልነዘንዝሽ ስል...” አላት!
“ውይ ደስ ይለኛል ጌታን!” አለቺኝ፤ ደስ በሚል ድምፅ!
ያው አርብና ቅዳሜ ሾፌሬን ይዤ፣ እሁድ የምለብሰውን ልብስ ፍለጋ ባከንኩ...
እድለኛም አይደለሁ... እሁድ ደረሰና አጭሯን ሱሴን አትላስ አገኘኋት...
እና ምን ለማለት ነው...
አብነት አጎናፍር ጥሩ ሰው አይደለም!
መጀመርያ ወደ መድረኩ ሲወጣ he is not intimidating at all... ጅንስ ሱሪው ውስጥ ሸሚዙን የሰገሰገ... የሚያብለጨልጭ ጫማ የለበሰ ጎልማሳ ምኑ intimidate ያደርጋል?
ደግሞ ከፈረንሳይኛ እስከ እንግሊዝኛ የፍቅር ዘፈኖች ተርጉሞና አስተርጉሞ ለጀነጀነ ሰው...
አብነትዬ መዝፈን ጀመረ...
“አንቺን ብሎ... ልቤ አልረጋ አለ...
ባሳብ ካንቺ ጋር... ሄዶ እየዋለ...
አስቻለሽ ወይ... ካለኔ ኑሮ...
ከበደኝ እኔን... እንጃ ዘንድሮ...
ለኔ ካለሽ... መቼም አይቀርም...
ውደጂኝ ብዬ... ሙጢኝ አልልም...
ለኔ ካለሽ... መቼም አይቀርም...
ውደጂኝ ብዬ... ሙጢኝ አልልም!”
እሷ በሳቀ ፊት ጮክ ብላ አብራው ትዘፍናለች...
ቁመቷን ናቅ አድርገው እንዳሻቸው ደረቷ ላይ የነገሱ ጡቶቿን 6-8 ምናምን እየጠበቀች nude ጥፍር ቀለም በቀባቻቸው ቆንጆ ትንንሽ ጣቶቿ ነካ ታደርጋቸዋለች...
አብነት ግን ምን ኾኖ ነው?
“ዞራ ዞራ የኔው ናት ዞራ ዞራ...” ምናምን በሚዘፈንበት ሀገር፣ እንዲህ መፈላሰፍ ምን የሚሉት ነገር ነው?
“... አለሁ... ይግባኝ አልጠየኩም...
ክፉም ነሽ አላልኩም...
ደግም ነሽ ሳልልም...
ብቻ ግን አለሁ...
እራሴን ባልጥልም...
አለሁ እንዳለሁ...”
ቱ...
እኔን ብሎ ገጣሚ!
እኔን ብሎ ተርጓሚ...
በጌታ ስም...
እሸማቀቃለሁ...
“... ዘንድሮስ ቸገረኝ... እምባዬ አልደርቅ አለኝ...
ሆዴም አልቆርጥ አለኝ... ድካሜ አሳዘነኝ...
ፍቅር አልቆይም አለኝ...
እየወሰወሰኝ... ከማጥ ወስጥ ዘፈቀኝ...”
እሷ እርክት እያለች ከአፍ ከአፉ ትቀበላለች...
እኔ እስከዛሬ “እንደዚህ ነው የምወድሽ...” ባልኩት እየተሳቀቅሁ አፈጣለሁ...
አብነት ሆዬ ይቀጥላል...
“...በርግጥ አታምኚም... አንቺን ማሰቤን...
ርቀሺኝ ስትሄጅ... ገፍተሺኝ እኔን...
አልጠላሽም... ስላልወደድሺኝ...
ካሳብ እንድድን... ብቻ ጠይቂኝ...”
እንዳልኩትም እድለኛ ነኝ...
ቆንጆ ብቻ ሳትሆን ልክም የሆነች ምትሀት ነው የወደድኩት!
ልክማ ነች...
የምወዳትን ያክል አልወደድኳትም...
አብነት ይሙት!

Read 2221 times