Saturday, 08 May 2021 12:52

በቶኪዮ 2020 የኦሎምፒክ ማራቶን

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

     የቀነኒሳ ስም መግባት ለዓለም አጓጊ ይሆናል በሜዳልያ ትንበያዎች የተሻለ ግምት ለምስራቅ አፍሪካ ተሰጥቷል ኪፕቾጌን የአበበ ቢቂላ ታሪክ ያጓገዋል

            ቶኪዮ ለምታስተናግደው 32ኛው ኦሎምፒያድ ሰባ ሰባት ቀናት ቀርተዋል፡፡ በኦሎምፒክ የማራቶን ውድድር ላይ የኢትዮጵያና ኬንያ ቡድኖች በዓለም ዙርያ ከፍተኛ ትኩረት እየሳቡ መጥተዋል፡፡ ኬንያ በሁለቱም ፆታዎች የቀረቡትን የኦሎምፒክ ሜዳልያዎች ጠቅልሎ ለመውሰድ ዝግጅት እያደረገች መሆኗን ስትገልፅ፤ በኢትዮጵያ በኩል በቡድን አመራረጡ ኦሎምፒያኖች፤ አትሌቲክስ ፌደሬሽንና የኦሎምፒክ ኮሚቴ ሲወዛገቡ ሰንብተዋል፡፡
በኦሎምፒክ መድረክ የማራቶን ውድድር ትልቅ ጉዳይ ነው፡፡ ጃፓን ውስጥ መካሄዱም ልዩ ትኩረት የሚስብ ይሆናል፡፡ በማራቶን ስፖርት የምትታወቀው ጃፓን በአሁኑ ወቅት በሁለቱም ፆታዎች በዓለም ፈጣን የማራቶን ሰዓት እስከ 20ኛ ደረጃ የሚገቡ አትሌቶች አሏት። ከታዋቂዎቹ ስድስት ዓመታዊ ማራቶን ዋና ዋናዎቹ አንዱ የሆነው የቶኪዮ ማራቶን እንዲሁም የፉኩካ ማራቶኖችም በአገሪቱ ይዘጋጃሉ፡፡ ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኪሚቴ ባወጣው መርሃ ግብር  በቶኪዮ 2020 ላይ የሴቶች ማራቶን ኦገስት 7 በፍፃሜው ዋዜማ ላይ የሚካሄድ ሲሆን  የወንዶች ማራቶን በፍፃሜው ቀን ኦገስት 8 ላይ ይካሄዳል። ሁለቱም የድል ሥነ ሥርዓቶች በመዝጊያ ሥነ ሥርዓቱ እንደሚከናወኑም ታውቋል። በኦሎምፒክ ማራቶን ላይ እያንዳንዱ አገር በሁለቱም ፆታዎች ማሰለፍ የሚችለው  ሶስት አትሌቶችን ብቻ ነው፡፡ ይህ የስፖርት አድማስ ዘገባ በኦሎምፒክ ማራቶን  ዙርያ በኢትዮጵያ እና በኬንያ ቡድኖች  ያሉትን ሁኔታዎች የሚዳሰስ ነው፡፡
አወዛጋቢው የኢትዮጵያ  የማራቶን
ቡድን  አመራረጥ
 በቶኪዮ 2020 የኦሎምፒክ ማራቶን  የኢትዮጵያ ቡድን አመራረጥ ላይ የተፈጠረው ውዝግብ የሚያስደስት አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ካሉት ምርጥ የማራቶን ኦሎምፒያኖች፤ አሰልጣኞች፤ ማናጀሮች እና አትሌቶች አንፃር የቡድኑ ምርጫ ከኬንያ ቀድሞ መታወቅ ሁሉ ነበረበት፡፡ በኮቪድ 19 ሳቢያ ኦሎምፒኩ በ1 ዓመት መሸጋሸጉ በተለይ ለማራቶን ቡድን የሚያዘጋጁ ውጤቶች እና ውድድሮችን አስተጓጉሏቸዋል፡፡ ይህም ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ በፌደሬሽንና በኦሎምፒክ ኮሚቴ መካከል የሚያወዛግብ አጀንዳን ፈጥሮ ቆይቷል፡፡
ከውዝግቡ መካረር የተነሳ በቶኪዮ 2020 ላይ የኢትዮጵያ ማራቶንን ቡድንን በይፋ መግለፅ አዳጋች ሆኗል፡፡ የማራቶን ቡድኖቹን እንደኬንያ እነማን ይምሯቸው የሚል ጥያቄ ቢነሳ ለመመለስ የሚያስቸግርበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። ባለፈው ሰሞን ለምሳሌ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ባሰራጯቸው ዘገባዎች ቀነኒሳ በአትሌቲክስ ፌደሬሽን የማጣርያ ውድድር ባለመሳተፉ  የቶኪዮ ኦሎምፒክ አምልጦታል የሚለው አጀንዳ ተራግቧል፡፡
በኦሎምፒክ ዝግጅቱ ላይ በተደጋጋሚ ውሳኔዎችን ሲቀያይር  የቆየው የአትሌቲክስ ፌደሬሽን በማራቶን ቡድን ምርጫ ማጣርያ ያዘጋጀበት አመራረጡ ብዙዎችን አላሳመነም። ባለው ሙሉ ስልጣን በድንገት በ35 ኪሜትር የኦሎምፒክ ማጣርያ ውድድሩን  ሰበታ ከተማ ላይ ሲያዘጋጅ በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን በማራቶን ወክለው የሚወዳደሩ አትሌቶች በሁለቱም ፆታዎች የተለዩበት ለመለየት እንደሆነ ገልጿል፡፡ በውድድሩ ላይ እንዲሳተፉም ለ12 ወንድና ለሰባት ሴት ማራቶን ሯጮች ማስታወቂያም አውጥቶ ነበር፡፡ ምርጥ የማራቶን ሯጮች   ኦሊምፒክ ከሦስት ወር ያነሰ ጊዜ እየቀረው የማጣሪያ ውድድሩ መካሄዱን አልተቀበሉትም፡፡ ውድድሩ በተካሄደበት ቀን የአየር ንብረቱ ቀዝቃዛ መሆኑ፤ የትራፊክ መጨናነቅ የሚበዛበት ጎዳና ላይ መደረጉንም  አንዳንዶች ተችተዋል፡፡
ባለፉት አሎምፒያዶች አትሌቶች በቀጥታ የሚመረጡት ውድድሮች ከመድረሳቸው አስቀድሞ በተመረጡ ታላላቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ባስመዘገቧቸው ሰዓቶች እንደነበር ይታወቃል። ብዙዎቹ አትሌቶች ሚኒማ በማሟላት ዝግጅት ላይ ስለቆዩ ኢትዮጵያን የሚወክሉትን ለመለየት ውድድር አስፈላጊ ነበር፡፡ በኮቪድ-19  ምክንያት አትሌቶች በዓለም አቀፍ ውድድሮች ተወዳድረው አቅማቸውን የሚለኩባቸው ውድድሮች አልነበሩም፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ቴክኒክ ኮሚቴ  ከመነሻው  በሃዋሳ ከተማ የማራቶን ማጣሪያ ሊያካሂድ ነበር ፡፡ በአትሌቶች ስምምነት ይሄው ውድድር መሰረዙ  ከተነገረ በኋላ ደግሞ ስዊዘርላንድ ዙሪክ ላይ ማጣርያው እንደሚካሄድ ተገለፀ፡፡ ከኮቪድ-19 ስጋት ጋር በተያያዘ  ይህም መርሃ ግብር ከተሰረዘ በኋላ በመጨረሻም የማጣሪያ ውድድሩ በሰበታ እንዲካሄድ የፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ኮሚቴ፣ አሰልጣኞችና አትሌቶች ተስማምተዋል፡፡
በሰበታ ላይ በተካሄደው የማራቶን ማጣርያ ላይ በወንዶች ምድብ ያሸነፈው ሹራ ቂጢሳ ሲሆን 1 ሰዓት ከ45 ደቂቃ እና ከ55 ሰከንዶች በሆነ ጊዜ ርቀቱን በመሸፈን ነው፡፡ በዓለም ሻምፒዮን በማራቶን የወርቅ ሜዳልያ የተጎናፀፈው ሌሊሳ ዴሲሳ ደግሞ  በ20 ሰከንዶች ተቀድሞ ሁለተኛ ደረጃ ሲወስድ፤ ሶስተኛ ደረጃ ያስመዘገበው ሲሳይ ለማ በ3ኛ ደረጃ ጨርሷል፡፡ በሴቶች የ35 ኪሜትር የማጣርያ ውድድሩን ያሸነፈችው ትእግስት ግርማ 1:59:23 በሆነ ሰዓት ነው።  ሁለተኛ ሆና ያጠናቀቀችው አትሌት ብርሃኔ ዲባባ ስትሆን 3ኛ ደረጃ ያገኘችው  ሮዛ ደረጄ ናት፡፡ ሶስቱ አትሌቶች በኦሎምፒክ መድረክ ሲሳተፉ የመጀመርያቸው ነው፡፡ ትእግስት 14ኛው ፈጣን ሰዓት፤ ብርሃኔ ዲባባ 6ኛው እንዲሁም ሮዛ ኛው ፈጣን ሰዓትን በኢትዮያ የማራቶን ታሪክ ያስመዘገቡ ናቸው፡፡
የቀነኒሳ ጉዳይ
ቀነኒሳ ሰበታ ላይ በተደረገው የማጣርያ ውድድር አልተሳተፈም ነበር፡፡ ማናጀሩ ጆስ ሄርማንስ  በ2356 ሜትር ከፍታ  ላይ በቀዝቃዛ አየር በሚካሄደው ውድድር ላይ ቢሳተፍ በቂ የማገገሚያ ግዜ እንዳማይሰጠው በማመኑ ውሳኔ ላይ መድረሱን ለአጃንስ ፍሬንስ ፕሬስ ተናግረዋል። በማናጀሩ አስተያየት የማራቶን ማጣርያ ከቶኪዮ ዝግጅቱ ጋር የሚገናኝ እንዳልሆነ፤ ለቶኪዮ 2020 ምርጡ የማራቶን ቡድን ቀነኒሳ በቀለ ያለበት እንደሆነ ሲናገሩ በማጣርያው በተመዘገበው ውጤት እና በሌሎች አትሌች ላይ ተቃውሞ እንደሌላቸውም ገልጸዋል፡፡  
ከማጣርያ ውድድሩ በፊት ታዋቂው ኦሎምፒያን ቀነኒሳ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽንና ለመገናኛ ብዙኃን በፃፈው ደብዳቤ «አገሬን ከመወከል መከልከሌን ሕዝብ ይወቅልኝ፤ በጥሩ አቋም እና በመልካም ጤንነት ላይ ሆኜ አገሬን መወከል ልከለከል አይገባኝም» ብሎ ነበር። በማጣርያው ውድድር ባለመሳተፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኑ ከምርጫው ውጭ እንዳያደርገው በመስጋቱ ነበር፡፡ ባለፈው ሪዮ ኦሊምፒክም ኢትዮጵያን ለመወከል አስፈላጊውን ሰዓት አሟልቶ በመጨረሻ ሰዓት ግልፅ ባልሆነ ምክንያት ሳይሳተፍ መቅረቱን በማስታወስም በደብዳቤው ላይ ቅሬታውን ገልጿል፡፡ ቀነኒሳ የቶኪዮ ኦሊምፒክ በኮቪድ-19 ምክንያት ከመራዘሙ በፊት ኢትዮጵያን በማራቶን ለመወከል በቀዳሚነት ሲመረጥ በ2019 በርሊን ማራቶን ላይ 2:01:41 ያስመዘገው ፈጣን ሰዓት ዋናው ምክንያት ነበር፡፡ ኪፕቾጌ ካስመዘገበው የዓለም ክብረወሰን በሁለት ሰከንድ የዘገየ እንደነበር ይታወሳል።እንደ ኤኤፍፒ ዘገባ በኢትዮጵያ የማራቶን ቡድን ውስጥ የቀነኒሳ ስም መግባት ዓለምን የሚያጓጓ  ይሆናል፡፡ከወቅቱ የኦሎምፒክ ሻምፒዮን እና የዓለም ማራቶን ሪከርድ ባለቤት ኪፕቾጌ የሚገናኙበትን እድል ስለሚያሰፋው ነው፡፡
ኮሴጊ፤ ጄፕቺሪት ቼፕኔትጊችና ቼሮይት
በኬንያ የማራቶን ቡድን ሴቶቹን የምትመራው ብርጊድ ኮሴጊ ከ15 ዓመታት በላይ በእንግሊዟ አትሌት ፓውላ ራድክሊፍ ተይዞ የነበረውን የዓለም ሪከርድ በቺካጎ ማራቶን 2:14:04  በሆነ ጊዜ የነጠቀች ናት፡፡ የዓለም ግማሽ ማራቶን ሪከርድንም በ2019 ግሬት ኖርዝ ራን  64:28  በሆነ ጊዜ አስመዝግባ ነበር፡፡ በ2020 የቫሌንሽያ ማራቶንን ያሸነፈችው ፔሬስ ጄፕቺሪር   በዓለም የግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና ላይም  ልዩ ሪከርድ አሲይዛለች፡፡  ሩት ቼፕኔጊትች  ደግሞ ኳታር ላይ በተካሄደው 19ኛው የዓለም አትሌክስ ሻምፒዮና ላይ በማራቶን ሻምፒዮን ሆናለች፡፡
በዓለም የማራቶን ፈጣን ሰዓት ደረጃ ላይ ኮሴጊ በ2:14:04  አንደኛ ደረጃን ጄፕቺሪሪር 2:17:16 አራተኛ ደረጃን እንዲሁም 2:17:08 ቼፕኔጊቲች 5ኛ ደረጃን አከታትለው ይዘዋል፡፡
ሌላኛዋ የቡድኑ አባል በኦሎምፒክና በዓለም አቀፍ የረጅም ርቀት ውድድሮች ከፍተኛ ልምድ ያላት ቪቪያን ቼሮይት ናት፡፡ በ31ኛው ኦሎምፒያድ ሪዮ ዴጄኔሮ ላይ በ5ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ እንዲሁም በ10ሺ የብር ሜዳልያ መውሰዷ ይታወቃል፡፡ በአራት ኦሎምፒኮች ተሳትፋም በድምሩ ሜዳልያዎችን የሰበሰበች ናት፡፡ ቪቪያን  ቼሮይት በቶኪዮ 2020 ላይ በማራቶን የምትሳተፍበትን እድል ከሁሉም እኩል እንደያዘች ነው፡፡ በ2018 እኤአ ላይ በለንደን ማራቶን ያስመዘገበችው 14ኛውን የዓለም ማራቶን ፈጣን ሰዓት ሲሆን በቡድኑ ስትካተት ያላት ልምድ ከግምት ውስጥ ሳይገባ አልቀረም፡፡
የአበበ ቢቂላ ታሪክ ያጓጓው ኪፕቾጌ
ኬንያ ለቶኪዮ 2020 ለኦሎምፒክ ባሰለፈችው የማራቶን ቡድን ወሬው ሁሉ ስለኤሊውድ ኪፕቾጌ ነው፡፡ በመላው ዓለም ከቶኪዮ 2020 በተያያዙ የሚዲያ ሽፋኖች ሰፊ ሽፋን እየተሰጠው ይገኛል፡፡ በ31ኛው ኦሎምፒያድ ሪዮ ዴጀኔሮ ላይ ጣፋጩን የኦሎምፒክ ማራቶን ድል በምርጥ ብቃት ያስመዘገበው ክብሩን ለማስጠበቅ ይሰለፋል፡፡ እንደ ኢትዮጵያዊው አበበ ቢቂላ በሁለት ተከታታይ ኦሎምፒኮች በማራቶን የወርቅ ሜዳልያዎችን በመውሰድ ክብረወሰኑን መጋራትም ይፈልጋል፡፡
 ‹‹ስፖርትን ስለምወድ እሮጣለሁ፡፡ ህይወቴ ነው፡፡  በትልልቅ ከተሞች ማራቶኖችን ስሮጥ ነው የምኖረው፡፡ በመላው ዓለም እየዞርኩም ትውልዱን የስፖርትን አስፈላጊነት አስረዳለሁ። መልካም አኗኗር መሆኑን እመክራቸዋለሁ›› በማለትም ከአትሌክስ ኢለስትሬትድ ጋር በኦሎምፒክ ተሳትፎው ዙርያ ባደረገው ቃለምልልስ ተናግሯል፡፡
በቶኪዮ 2020 የኦሎምፒክ ዝግጅቱ ላይ ከዋና አሰልጣኙ ጋር ልዩ ትኩረት አድርጎ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በናይኪ ማራቶንን ከሁለት ሰዓት በታች የመግባት ፕሮጀክት፤ በጆስ ሄርማንስ በሚመራው የኤንኤን የሯጮች ቡድን  ያገኛቸው ልምዶችም ቀላል አይደሉም፡፡ ከዋና አሰልጣኙ ፓትሪክ ሳንግ ጋር የተገናኘው በ17 ዓመቱ ከ2002 ጀምሮ ነው፡፡ በዓለም አትሌቲክስ ላይ ከፍተኛ ደረጃ እስኪደርሱ አሰልጣኙ እና አትሌቱ ለ19 ዓመታት በዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ወርቃማ ታሪኮችን መፃፍ ችለዋል፡፡ በአንድ አሰልጣኝ እና አትሌት መካከል መኖር ያለበት ቆይታ መሆኑን በርካታ ትንታኔዎች ገልፀውታል፡፡
 ከኢትዮጵያ አትሌቶች ጋር ረጅም ጊዜ በመስራት የሚታወቁት ማናጀሩ ጆስ ሀርማንስ ከኪፕቾጌም ጋር ይሰራሉ፡፡ ኪፕቾጌ በግሎባል ስፖርት ኮሚኒኬሽን  ስር ለቶኪዮ 2020 በነበረው ዝግጅት ካፕታጋት በተባለች ከተማ በሳምንት ለ6 ቀናት ትኩረቱን ለኦሎምፒክ ባደረገ መንፈስ  እየሰራ ቆይቷል፡፡ 36 ዓመቱ እንደመሆኑ በዓመት ሁለት ማራቶን ብቻ የሚሮጥበት እድሜ ላይ ነው፡፡ ወደ ቶኪዮ 2020 ኦሎምፒክ ያተኮረበት ሌላው ምክንያት በ2020 ለንደን ማራቶን ላይ ኪፕቾጌ ሊቀናው አለመቻሉ ሲሆን በ8ኛ ደረጃ ውድድሩን መጨረሱ የያዘውን የዓለም ክብረወሰን አደጋ ውስጥ ከቶበታል፡፡ በሰባት ዓመቱ በማራቶን ውድድር የመጀመርያው ሽንፈት ሲያጋጥመው ውድድሩን ኢትዮጵያው ሹራ ቂጢሳ ነበር ድል ያደረገው ፡፡ በዚያው የለንደን ማራቶን ላይ  ከ9 ዓመታት በኋላ ከቀነኒሳ ጋር የመገናኘታቸው ነገር አለመሳካቱም በማራቶን የያዘው ዝና አንቀራፎበታል፡፡ ስለዚህም በቶኪዮ 2020 የአሎምፒክ ማራቶን ላይ ከቀነኒሳ ጋር ይህ እድል በድጋሚ ቢፈጠር መላው ዓለም በጉጉት ይጠብቀዋል፡፡
ለኪፕቾጌ  ቶኪዮ 2020 አራተኛው የኦሎምፒክ ተሳትፎ ነው፡፡ የኦሎምፒክ ክብሩን ለማስጠበቅ በሚሰለፍበት መድረክ ዋና ተቀናቃኞች ተብለው በሌትስራን ትንታኔ የተገለፁት ከኢትዮጵያ በለንደን ማራቶን ጥሎት የገባው ሹራ ቂጢሳ እና በቶኪዮ ማራቶን ሁለቴ ያሸነፈው ብርሃኑ ለገሰ ሲሆኑ የቦስተንና ቺካጎ ማራቶኖች በማሸነፍ ስሙ የገነነው ሌላው ኬንያዊ ሎውረንስ ቼሮኖ  ተጠቅሷል፡፡
ኪፕቹምባ፤ ኪፕሮቶና ቼሮኖ
 በወንዶች ምድብ ከኤሊውድ ኪፕቾጌ ጋር ቶኪዮ 2020 ላይ ለኬንያ ሊሰለፉ የሚችሉት ሌሎቹ ሶስት ማራቶኒስቶችም ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው ናቸው፡፡ ቪንሰን ኪፕቹምባ በ2019 የአምስተርዳም እና የቪዬና ማራቶኖችን ያሸነፈና ምርጥ ሰዓቱንም በ2:0 6:56 ያስመዘገበ ነው፡፡
ከ2 ዓመት በፊት በኢትዮጵያዊው ሌሊሳ ተቀድሞ በዓለም ሻምፒዮና የብር ሜዳልያ የደረሰው አሞስ ኪፕሮቶ ደግሞ በ2020 ላይ የቫሌንሽያ ማራቶንን ሲያሸንፍ ያስመዘገበው 2:03:30  በፈጣን ሰዓቶች ደረጃ እስከ አስረኛ ደረጃ ውስጥ አስገብቶታል፡፡ በ2019 የቦስተን ማራቶንን ያሸነፈው ሎውረን ቼሮኖም ከፍተኛ ልምድ ያለው ነው፡፡

Read 1234 times