Saturday, 08 May 2021 12:54

አዞው ወደ ውሃ ሲስብ፤ ጉማሬው ወደ ሣሩ ይስባል

Written by 
Rate this item
(4 votes)

    የምድር አውሬ ሁሉ መነገጃና መሰባሰቢያ አንድ ገበያ ነበር ይባላል፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን አውሬ
ሁሉ እገበያ ሲውል፤ አያ ጅቦ ቀርቶ ኖሯል፡፡ ማታ ሁሉም ከገበያ ሲመለስ ከጎሬው ብቅ ይልና መንገድ ዳር ይቀመጣል፡፡ ዝንጀሮ ስትመለስ ያገኛትና ገበያው እንዴት እንደዋለ ይጠይቃታል፡፡
“እቸኩላለሁ፤ ጦጢት ከኋላ አለችልህ እሷን ጠይቃት” ብላው ሄደች፡፡
 ጦጢት ስትመለስ ጠብቆ “ገበያው እንዴት ዋለ?” አላት፡፡
 “መሽቶብኛል፡፡ ገና ብዙ ሥራ አለብኝ” ብላው አለፈች፡፡ ቀጥላ ሚዳቋ መጣች፡፡
ያንኑ ጥያቄ ጠየቃት፡፡ “እንኮዬ አህይት እኋላ አለች - እሷን ጠይቅ!! እኔ እነዝንጀሮ ቀድመውኛል፤
ልድረስባቸው” ብላው ሄደች፡፡
አህያ ስትንቀረደድ መጣች፡፡ ገበያው እንዴት እንደዋለ ጠየቃት፡፡ “ቆይ አረፍ ብዬ ላውራልህ”
ብላ አጠገቡ ተቀመጠች፡፡ “ይሄ ተገዛ! ያ ተሸጠ!” ስትለው አመሸች፡፡
 አያ ጅቦ ቀጠለና “ለመሆኑ እኔ እምዘለውን መዝለል ትችያለሽ?” አላት፡፡
“አሳምሬ” አለችው፡፡
እሱ የሞት ሞቱን ዘለለ፡፡ እሷ ግን እዘላለሁ ብላ ገደሉ ውስጥ ወደቀች፡፡ አያ ጅቦ ወርዶ ሆዷን
ዘንጥሎ መብላት ጀመረ፡፡ እመት ውሻ በዛ ስታልፍ ስጋ ሸቷት መጣች፡፡
“ነይ ውረጂና እየመተርሽ አብይኝ” አላት፡፡ ወርዳ እየመተረች ስታበላው የአህያዋን ልብ አገኘችና
እሱ ሳያያት ዋጥ ስልቅጥ አደረገችው፡፡
ቆይቶ “አንቺ ልቧ የታል?” ሲል ጠየቃት፡፡
 ውሺትም፤ “ልብ ባይኖራት ነው እንጂ ልብ ቢኖራት መቼ ካንተ ዘንድ መጥታ ትቀመጥ ነበር?!” አለችው፡
“ታመጪ እንደሁ አምጪ፤ አለዛ አንቺንም እበላሻለሁ!” አለ፡፡
“አያ ጅቦ፤ ያለ ቂቤ? ያለ ድልህ? ደረቁን ልትበላኝ?”
“ቅቤና ድልሁ ከየት ይመጣል?” አለ ጅቦ በመጎምጀት፡፡
“ከእመቤቴና ከጌታዬ ቤት አመጣለሁ”
“ሄደሽ የጠፋሽ እንደሆን ማ ብዬ እጠራሻለሁ?”
“እንኮዬ -ልብ- አጥቼ” ብለህ ጥራኝ፡፡
“በይ እንግዲያው ሄደሽ አምጪ” ብሎ ላካት፡፡ ቅርት አለች፡፡ ሲቸግረው፤
“ኧረ እንኮዬ ልብ አጥቼ?” ሲል ጮሆ ተጣራ፡፡
ውሻም፤ “ከጌታዬና ከእመቤቴ ቤት ለምን ወጥቼ!” አለችው፡፡ ከዚያም የስድብ መዓት ታወርድበት ጀመር፡፡
ጅቦም፤ “አንቺም እጉድፍ እኔም እጉድፍ፡፡ አገኝሻለሁ ስንተላለፍ” አላት፡፡
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ውነትም ጉድፍ ስትለቃቅም አገኛት፡፡ ዐይኗ ፈጠጠ፡፡
“ዐይንሽ እንዴት እንዲህ አማረልሽ?” ሲል ጠየቃት፡፡
“በዐሥር የአጋም እሾክ ተነቅሼ!” አለችው፡፡
“እስቲ እኔንም ንቀሺኝ?”
ተስማምታ ከጌታዋ አጥር ዓሥር የአጋም እሾህ ሰብራ አምጥታ ዐይኖቹን ቸከቸከችው፡፡
“ኧረ አመመኝ” ሲል፤ “ዝም በል ሲያጌጡ ይመላለጡ ነው፣ ማማር እንዲያው ይገኝ መሰለህ?”
ትለዋለች፡፡
ሁለቱንም ዐይኖቹን አጥፍታ፤ “በል ና ሠንጋ ጥለው የሚሻሙ ጅቦች ጋ ልቀላቅልህ” ብላ፤ ውቂያ ላይ ያሉ ገበሬዎች ማህል ከተተችው፡፡  ጤፍ መውቂያ ሙጫቸውን እየመዘዙ ሊገድሉት
ያራውጡት ጀመር፡፡
ውሻ ሆዬ እነሱ ሲሯሯጡ ዳቧቸውን ይዛ ወደ ቤቷ መጭ አለች!!
* * *
ያሰቡትን ቸል ሳይሉ ከፍፃሜ ማድረስ አስተዋይነት ነው፡፡ ያለ እኩያ ጓደኛ መያዝ፤ ነገርን ሳያመዛዝኑ ፈጥኖ አምኖ መቀበል ከጥቃት የሚያደርስ ቂልነት ነው፡፡ አታላይ ለጊዜው የመብለጥለጥ ምኞቱን ቢያረካም፣ የፈፀመው ደባ እንደሚደርስበት የዥቡን አወዳደቅ ማስተዋል በቂ ነው! ብልህ በዘዴ ከአደጋ ያመልጣል፡፡ ኃይለኛ የሆነ ጠላት ቢገጥመው እንኳ በጥበብ ለመርታት ይችላል፡፡
ሀገራችን ያለችበት ሁኔታ አሳሳቢ ነው፡፡ አንዱ ሲሠራ ሌላው ሲያፈርስ፣ አንዱ ሲያስር ሌላው ሲተበተብ፤ የሁኔታዎች መወሳሰብ ይከሰታል፡፡
ከውስብስቡ ሁኔታ ለመውጣት እጅግ አስፈላጊው ነገር ትዕግሥትና ስክነት ነው፡፡ ባላንጣ፤ ሀገር ያልተረጋጋበትን ሰዓት መምረጡ የታወቀ ጉዳይ ነው፡፡ በብልህነት ማውጠንጠን፣ አርቆ - ማስተዋል፤ ነገሮች ተደራርበው ግራ እንዳያጋቡን ይጠቅመናል፡፡
የግብጽና ሱዳን ትንኮሳና ዓለማቀፍ ዘመቻ አንድ ረድፍ ነው፡፡ የዜጎች በታጣቂዎች መገደልና መፈናቀል ሌላ ከባድ ችግር ነው፡፡ የዓለማቀፉ ማህበረሰብ ዲፕሎማሲያዊ ጫናም ሌላ የጎን ውጋት ነው፡፡ የኑሮ ውድነቱም ገና ያልተወጣነው አቀበት ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ በጦርነት ድንፋታ ንፋስ ሲታጀቡ ደግ አይሆንም፡ስለ ጦርነት ከተነገሩት ድንቅ አነጋገሮች ሁሉ የሚከተለው ይገኝበታል፡ -
“ጦርነት ነፃነትህን ስለሚወስድብህ አስፈላጊ የሆነ ምርጫ ላይ ለመዋጋት ወይም ላለመዋጋት ልትወስን ትችላለህ፡፡ አንዴ ጦርነት ከገባህ ግን የምርጫ ኃይልህ አከተመ” (ጊልበርት ሙሬይ) ሁሉም ነገር ጥንቃቄንና ዝግጁነትን ይጠይቃል፡፡ የተረጋጋ ህዝብን ይጠይቃል፡፡
መንገዶች ሁሉ ወደ አንድ አቅጣጫ እንዳይሄዱ፤ እመነገጃውና እመገበያያው የሚገቡትን ባለይዞታዎች በጥሞና መያዝ ይገባል፡፡ የህዝብን አመኔታ የሚያጠናክር አዎንታዊ እርምጃ፣ ሀገራዊ ስሜትን ለማድመቅ እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ ቤትም አገርም አለኝ የሚል ህዝብ እንዲኖረን ያስፈልጋል!
“በሰው ልጅ ላይ የወረደ ታላቅ መርገምት ጦርነት ነው፡፡ በሰላም ጊዜ የሚፈፀሙት የጭካኔ ወንጀሎች፤ በሰላም ጊዜ የሚካሄዱት ሚስጥራዊ ሙስናዎች አሊያም የሀገሮች ሃሳብ - የለሽ የገንዘብ ዝርክርክነቶች ሁሉ፤ ጦርነት ከሚያደርስብን ሠይጣናዊ ጥፋት ጋር ሲወዳደሩ እንክልካይ ነገሮች ይሆናሉ” ይለናል፤ ሲድኒ ስሚዝ፡፡
የህዝብን የልብ ትርታ ማዳመጥ የወቅቱ ጥሪ ነው፡፡ የመንግሥት ጥንቃቄ የተሞላ እርምጃም የወቅቱ ጥሪ ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊና ዲፕሎማሲያዊ ሂደትን ሥራዬ ብሎ ማቀናጀት ብልህነት ነው!! ዕውነት ገና ጫማውን እያሰረ፣ ውሸት ዓለምን ዞሮ ይጨርሳል የሚለውን አባባል አንርሳ!!
በመላና በጥበብ የመምራት ክህሎትን የሚጠይቅ ወቅት ነው፡፡ “አዞው ወደ ውሃ ሲስብ፣ ጉማሬው ወደ ሣሩ ይስባል” የሚለው የወላይታ ተረት ጉዳያችንን ያሳስበናል፡፡



Read 13012 times