Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 01 September 2012 09:59

ህዝብ አዋሽ ነው፣ የአዋሽ ማዕበል!! ነ.መ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

“ሞት ሳይሞቱት ነው እሚለመድ”፣ ሲባል ዋዛ መስሎኝ እኔ

ለካ የምሩን ሲመጣ፣ አንጀት - ይቆርጣል ሰው - መጥኔ!

ልብ - ያደማል የሰው ጠኔ!

ልብ - ይሰብራል ሐዘን ወይኔ!!

ሌት ተቀን እንደነደደ፣ ብቻውን የጨሰ ሶታ

ሞትን አላቀደ ኖሮ፣ የማታ ማታ ሲረታ

ያገር ጽዋ ከሰው ጽዋ፣ ሲቆራኝ ቀን ያስረግማል

ወጣት አዛውንት አላቅሶ፣ አገሩን ደረት ያስጥላል!

 

በዚህ ክፉ እኩይ ሰዓት

መሪ ብቻ አደል ያጣሁት

የእሳት - ዕድሜ አቻዬን እንጂ፣ ያንድ ትውልዴን ቁራኛ

የአንድ አጥር ግቢ አብሮ - አማጭ፣ ያንድ ቀን ክፍል ጓደኛ

ያንድ እናት ትግል ያቀፈን፣ ያንድ ዘመን ዘመነኛ!

ሆነን በተማሪ ንቃት፣ የህዝብን ዜማ ስናዜም

የህዝብ ህመም ስንታመም

እንዲህ በግማሽ - ምዕት ጣር፣ የህዝብን ለቅሶ ልናይ

ስንቱ ተወጥቶ ተወርዶ፣ አድሮ ውሎ ላገር አዋይ!!

ያኔ አልበለው ዘመኑን፣ ጊዜ ባዳ ያስመስላል

እንዲህ ሞትጋ ልንጠጋ፣ ስንት የቀን - ጐዶሎ አልፈናል

እንዲህ ማረፍህ ላይቀር፣ ስንቶች እረፍት ያዙልሃል

የታማህበት ባንዲራ፣ ዝቅ ብሎ ያነባልሃል!

ምነው ቀና ብለህ ባየህ፣ ይህን የአዋሽ ህዝብ ስሜት

ለመሪው ያለውን ክብር፤ ለሰው ልጅ ያለውን ስስት

ምድር ሰማይ አጥለቅልቆ፣ ሲንሰቀሰቅ በሣግ እሣት

ከአደባባይ አደባባይ አስከሬን፣ እንደ አራስ ሊያቅፍ

ካፋፍ ከየፎቁ ጫፍ፣ ከግርጌ ከየቤት ደጃፍ

ሰው እንደጨፈቃ ሆኖ፣ በየአስፋልቶቹ ምዕራፍ፣

ከኤርፖርት እስከ ዑራኤል፣ መስቀል አደባባይ በራፍ

ማዕበል እንደአዋሽ ሲጐርፍ…

እባክህ ቀና በል ዛሬ፤ የናፈቀውን ህዝብ አስብ

እጅ - ንሣ ላክብሮቱ፤ እቺ አገር ዳግመኛ ታብብ

ህዝብ አዋሽ ነው፣ ጐርፍ ነው ህዝብ!

እጅ ለእጅ ለመያያዝ፣ አይረፍድበትም ሰዓቱ

የቁርጡ ቀን ቁርጠኛ ነው፤ ኃያል ነው አዋሽ ፍላቱ

ከአንቀልባ እስከመቃብር፣ አለው ያከማቸው ትግሥት

ቁጣው እንደማይበገር፣ ደሞ አለው ሩህሩህ አንጀት!!

ይሄው ነው አስቀድሞ ቃል፤ ባህል ያለው ህዝብ ማለት!!

ሰው ማጣት ሰውን ያጐድላል

አገር እንዲህ ያስለቅሳል!!

ማን ነበረ ያ ደራሲ?

ተፎካካሪው ሞቶበት በሰቀቀን ያለቀሰ

“ከእንግዲህ ማን ሊሰድበኝ ነው?!” ያለው በዕንባ እየራሰ

ትግል የግል፣ ነው ፋና

ሰው ማጣት መሪር ነው ግና

ሐዘንን መስረፁ አይቀርም

ተፈጥሮም ውሏን አትስትም

ይብላኝ ቀን ለሌለው እንጂ፣ የሰው ልጅ በቀኑ ያልፋል

የተሞላለትን ፅዋ፣ ዕለቱን ቆጥሮ ይጠጣል

በመጨረሻዋ ሰዓት

ዘላለምን ቢታደሉም

ቅጽበትን አይታገሉም

የዕለቱ ለት የሚቀምሳት

የሰው ልጅ ፅዋው አንድ ናት

የማይካድ አይካድም

የተፃፈም አይፋቅም፡፡

ዜጋ ብቻውን፤ የሰው ልጅ፡፡

ህዝብ ግን የአዋሽ ጐርፍ አዋጅ!

የዚህን ጐርፍ ልብ የነካ

በመልካም ሥራው ይመካ!!

ህዝብ አዋሽ ነው፣ የአዋሽ ማዕበል

ባክህ አንዴ ተመልከተው፣ የዛሬን እንኳ ቀና በል!!

(ለመለስ ዜናዊና በሀዘን ለሰነበተው ጐርፍ ህዝብ)

ነሐሴ 18 2008 ዓ.ም

 

 

Read 31684 times Last modified on Saturday, 01 September 2012 10:07