Saturday, 15 May 2021 14:51

የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት በትግራይ ጦርነት ተሳታፊዎች ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ግፊት እያደረጉ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሃላፊ መንግስታቸው በትግራይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈፅሟል የሚል ጥርጣሬ እንዳለው የገለፁ ሲሆን የአሜሪካ የኮንግረስ አባላት የጆ ባይደን አስተዳደር በጦርነቱ ተሳታፊዎች ላይ ማዕቀብ እንዲጥል ግፊት እያደረጉ መሆኑ ታውቋል፡፡
በኮንግረሱ የዲሞክራቲክ ተወካዮች ሊቀ መንበሩ ጆርጅ ሚክ እና የቴክሳስ ግዛት ተወካዮችና የሪፐብሊካኑ አባል ማይክል ማክላውል የኮንግረስ አባላቱን ወክለው በጆ ባይደን አስተዳደር ላይ ግፊት እያደረጉ ሲሆን በትግራይ ክልል ሰብአዊ መብት ጥሰት እየፈፀሙ ባሉ ሁሉም አካላት ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ነው የጠየቁት፡፡
የኮንግረስ አባላቱ ባወጡት መግለጫ፤ “በተለይ የኤርትራ ወታደሮች ከክልሉ እስካሁን አለመውጣታቸው ሁኔታውን አሳሳቢ ያደርገዋል፤ በክልሉ መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሊቀጥሉ ይችላሉ የሚል ስጋት አለን” ብለዋል፡፡
የኮንግረስ አባላቱ በመግለጫቸው በጦርነቱ በርካታ ንፁሃን መገደላቸውን፣ ሴቶች መደፈራቸውንና ፆታዊ ጥቃት መፈፀሙ አውስተዋል፡፡ በጦርነቱ የተሳተፉ ሁሉም አካላት ማለትም ህወኃት፣የመከላከያ ሰራዊት፣ የኤርትራ ሰራዊትና ሌሎች ታጣቂዎች በከተሞች አካባቢ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ለደረሱት ጉዳቶች ሃላፊነት አለባቸው ብለዋል- የኮንግረስ አባላቱ፡፡
ጥያቄው የቀረበለት የባይደን አስተዳደር ሁሉንም አማራጮች እየተመለከተ መሆኑን እንገነዘባለን፤ በቀጣይ የሚያሳልፋቸውን ውሳኔዎችም  እንጠብቃለ፡፡ ያሉት የኮንግረስ አባላቱ ጥያቄያችን በዋናነት ማእቀብ እንዲጣል ነው   ብለዋል፡፡
ስድስት ወራት ባስቆጠረው የትግራይ ግጭት የተሳተፉ አካላት ላይ ከሃገር ወደ ሃገር  እንዳይንቀሳቀሱ የሚያደርግ ማዕቀብን ጨምሮ ሌሎች አማራጮች እንዲታሰቡ ጭምር ነው የኮንግረስ አባላቱ እየጠየቁና በባይደን አስተዳደር ላይ ግፊት እያደረጉ ያሉት ተብሏል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሃላፊ አንቶኒ ብሊንከን በበኩላቸው፤ በትግራይ  ግጭት የዘር ማጥፋት ወንጀል መፈፀሙን ጠቁመው፤ ግጭቱ እንዲበቃ መጠየቃቸውን ተዘግቧል።

Read 12011 times