Saturday, 15 May 2021 14:54

በመራጮች ምዝገባው ኦሮሚያ ክልል መሪነቱን ይዟል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(8 votes)

    • በ11 ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች ሲካሄድ የቆየው የምርጫ ምዝገባ ተጠናቋል
      • እስከ አሁን በተጠናቀረው ከ31.8 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ለምርጫው ተመዝግቧል
      • ምዝገባ ባልተጀመረባቸው አካባቢዎች የመራጮች ምዝገባው እስከ ግንቦት 13 ይካሄዳል
                
              በመላው አገሪቱ በአስራ አንዱም ክልሎችና  የከተማ መስተዳድሮች ሲከናወን የቆየው የመራጮች ምዝገባ ትናንት የተጠናቀቀ ሲሆን ኦሮሚያ ክልል ከ14.3 ሚሊዮን በላይ መራጮችን በመመዝገብ መሪነቱን ይዟል ተብሏል።
ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ያወጣው መረጃ እንደሚመለክተው ቦርዱ ከመጋቢት 16  ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ሲያካሂደው የቆየውንና ለሁለት ጊዜያት ያራዘመውን የመራጮች ምዝገባ አጠናቋል። በዚህም መሰረት በአዲስ አበባና ድሬደዋ ከተሞች፣ በአፋር፣ በአማራ ኦሮሚያ ፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ፣ በሃረሪ፣ በጋምቤላ፣ በደቡብ፣ በሲዳማና በሶማሌ ክልሎች ሲከናውን የቆየውን የመራጮች ምዝገባ ማጠናቀቁን ገልጿል።
ቦርዱ ለ6ኛው አገራዊ ምርጫ የሚያካሂደውን የመራጮች ምዝገባ በተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎች አለመካሄዱን አስታውሶ፤ በእነዚህ አካባቢዎች የመራጮች ምዝገባ ጊዜውን እስከ ግንቦት 13/2013 ዓ.ም ድረስ ለማድረግ መወሰኑን አመልክቷል። እነዚህም አካባቢዎች ምዕራብና ምስራቅ ወለጋ ዞኖች፣ ቄለም ወለጋ ዞን ፣ በሆሮጉድሩ ዞን በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከማሻ ዞን፣ እንዲሁም የመራጮች ምዝገባው በፀጥታ ችግር የተነሳ ሳይከናወን በቀረባቸው የአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔር ልዩ ዞን ምርጫ ምዝገባ እስከ ግንቦት 13 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ እንዲከናወን ተወስኗል።
ትናንት በተጠናቀቀው የመራጮች ምዝገባ እስከ አሁን ባለው ሪፖርት ኦሮሚያ ክልል ከ14.3 ሚሊዮን በላይ መራጮችን በመመዝገብ  ቀዳሚነቱን የያዘ ሲሆን አማራ ክልል 5.2 ሚሊዮን መራጮችን መመዝገቡን የምርጫ ቦርድ ጊዜያዊ የመራጮች ምዝገባ መረጃ ያመለክታል።  
በሀገሪቱ ሁሉም የምርጫ ክልሎች የተመዘገቡ መራጮችን ቁጥር ለማወቅ ከሁሉም ክልሎች የተሰበሰቡ መረጃዎችን ማጠናቀር እንደሚያስፈልግ የገለጸው ቦርዱ፤  እስከ አሁን ድረስ ከ31.8 ሚሊዮን በላይ መራጮች መመዝገባቸውን አመልክቷል።
ቦርዱ ባለው የእጩ ምዝገባ ጊዜ ሰሌዳ መሰረትም ማንኛውም ፓርቲ እጩውን መለወጥ ወይም መተካት የሚችለው  ከድምፅ መስጫው አንድ ወር በፊት ብቻ በመሆኑ ከሚያዚያ 28 ቀን 2013 ዓ.ም በኋላ የእጩ መተካት፣ መቀየር መለወጥና ማንኛውም አይነት ማሻሻያ ማድረግን የማይቀበል መሆኑንም ቦርዱ አስታውቋል።


Read 11704 times