Saturday, 15 May 2021 00:00

የከያኒ ኤሊያስ መልካን ታሪክ የያዘው “የከተማው መናኝ” መፅሐፍ ዛሬ ይመረቃል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

  በጋዜጠኛ ይነገር ጌታቸው የተሰናዳውና የታዋቂውን ሙዚቀኛ ኤሊያስ መልካን የህይወት ፈለግ ከተለያዩ ግላዊና ኪናዊ ንድፈ ሀሳቦች አንፃር በስፋት ለመመርመር የተሞከረበት “የከተማው መናኝ” መፅሐፍ ዛሬ ከቀኑ 7፡00 ጀምሮ በብሄራዊ ቴአትር በድምቀት እንደሚመረቅ የመፅሀፉ አዘጋጅ ጋዜጠኛ ይነገር ጌታቸው አስታወቀ። መፅሀፉ  ፍልስፍና፣ ነገረ መለኮት. ሳይንስ፣ ታሪክና ሙዚቃን በአንድ አጣምሮ የኤሊያስ መልካን ህይወት የሚዋጅ መሆኑን የገለፀው ጋዜጠኛው፣ በ14 ምዕራፎች ተከፋፍሎ በ409 ገፅ የተቀነበበ ሲሆን በ270 ብር ለገበያ መቅረቡም ታውቋል። በምርቃት ስነ-ስርዓቱ ላይ የተለያዩ ኪነ-ጥበባዊ ክንውኖች የሚያደረጉ ሲሆን የኤሊያስ መልካ ቤተሰቦች የስራ አጋሮቹ፣ አድናቂዎቹ፣ የቅርብ ወዳጆቹና ጓደኞቹ እንደሚታደሙና ስለ ታዋቂው ሙዚቀኛ ኤሊያስ መልካም ምስክርነት እንደሚሰጡ ታውቋል።
መፅሀፉም በዕለቱ ተመርቆ መሸጥ እንደሚጀምር ታውቋል። የመፅሐፉ አዘጋጅ ጋዜጠኛ ይነገር ጌታቸው፣ በኤፍ ኤም 97.1 እና በብስራት ሬዲዮ ከኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪኮች ጋር በተያያዙ መሰናዶዎቹ የሚታወቅ ሲሆን አዲስ አድማስን ጨምሮ በተለያዩ የህትመት ውጤቶች ላይም ሰፋ ያሉ ፖለቲካዊና  ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ በሚፅፋቸው ትንታኔዎች ይበልጥ ይታወቃል።

Read 960 times