Saturday, 01 September 2012 10:31

ሰው ካልሞተ አይመሰገንም! (የአበሻ ተረት) “እረፍት ምን እንደሆነ አላውቅም፤ ናፍቆኛል” (ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ) ይሄ ጨዋ ህዝብ ዳቦም ዲሞክራሲም ሊጠግብ ይገባል!

Written by  ኤሊያስ
Rate this item
(3 votes)

የክቡር ጠ/ሚኒስትሩን ህልፈተ - ህይወት የሰማሁት ማክሰኞ ጠዋት በኢቴቪ ነበር - ሦስት ዓመት ተኩል ከሆነውህ ልጄ ጋር፡፡ ለወትሮው ኢቴቪ ሲከፈት “ዜና አልፈልግም” እያለ (ዜና ለልጅ አይሆንማ!) ወደ ዲሽ እንዲለወጥለትና በአረብኛ የሚቀርበው የህፃናት ፕሮግራም እንዲከፈትለት የሚወተውተኝ ልጄ፤ በዚህ ዕለት እንደኔው ህልፈተ-ዜናውን በጥሞና መከታተሉ በግርምት ሞልቶኝ ነበር፡፡ ይባስ ብሎ ግን ከፊቴ ገጽታ ላይ የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን ተረዳ መሰለኝ “መለስ ሞተ?” በማለት አንዴ ወደ ቲቪው መስኮት፣ ሌላ ጊዜ ወደ እኔ አፍጥጦ እየተመለከተ አፋጠጠኝ፡፡ ቢቸግረኝ “አዎ” አልኩት የምለው ጠፍቶኝ፤ ግራ በተጋባ ስሜት፡፡ ይሄኔ ነው ሌላ መገረም ውስጥ የዶለኝ፡፡ ልክ እንደ አዋቂ በሁለት እጆቹ ጭንቅላቱን ይዞ አቀረቀረ (በደመነፍስ ሳይገባው የቀረ አይመስለኝም) ወዲያው ግን በኢቴቪ ይታይ የነበረው በአሳዛኝ የዋሽንት ድምጽ የታጀበው የጠ/ሚኒስትሩ ምስል ጠፋና ንግግራቸው መታየትና መስማት ጀመረ፡፡ ልጄ ከመቅጽበት ካቀረቀረበት ቀና ብሎ ወደ ቲቪው መስኮት መልከት አደረገና “ባቢ…መለስን አስነሳሁት!” አለኝ - በፈገግታ በታጀበ ንፁህ ፈገግታ፡፡ ስሜቱ ግን ከዛም በላይ ነበር፡፡

“በቃ አትዘን አስነስቼልሃለሁ!” የሚል ዓይነት ይመስላል፡፡ (ምነው እንደ አፉ በአደረገልን!) ወዳጆቼ…የዛሬ ህፃናት እኮ ጥይቶች ናቸው፤ ጭንቅላታቸው ብሩህ ነው፡፡ ንግግራቸው፤ የማመዛዘን አቅማቸው ከዕድሜያቸው በላይ ነው፡፡ (ፈጣሪ ይባርካቸው!) ይሄን ተፈጥሮአዊ ጭንቅላታቸውን ለበጐ ያውሉት ዘንድ ከጨቅላ ዕድሜያቸው ጀምሮ በቅጡ መኮትኮት የእኛ የወላጆች ሃላፊነት ይመስለኛል፡፡ ያኔ ልጄ እንዳለው መለስን ማስነሳት እንችላለን…ያውም አንድ መለስ ሳይሆን ብዙ መለሶችን ማስነሳት፤ መፍጠር ይቻለናል፡፡ እኒህ ህፃናት የዘመናቸው (የትውልዳቸው) መለስ ይሆኑልናል፡፡ በዚህ ቅንጣት አትጠራጠሩ፡፡ ዋናው ነገር ልጆቻችን ላይ በቅጡ ኢንቨስት ማድረግ ነው፡፡ (ያልተዘራ አይታጨድማ!)

ዛሬ በአበሻ የቆየ ተረታችን መሰረት ከህልፈታቸው በኋላ “ጀግናው አልሞተም!” እያልን ያመሰገናቸውና ያወደስናቸው መለስ፤ ለዚህ ሁሉ ክብርና አድናቆት የበቁት በበረሃ ስለታገሉ ብቻ አይደለም፡፡ ያደነቅናቸው ለራዕያቸው፣ ለጠሊቅ ሃሳባቸው፣ ለአርቆ አሳቢነታቸው፣ ለዕውቀታቸው፣ ለብልህነታቸው፣ ለአንደበተ ርዕቱነታቸው፣  ለድፍረታቸው፣ ለማሳመን ችሎታቸው፣ ለአንባቢነታቸውም ጭምር ይመስለኛል፡፡ እኒህ ሰው በጉርምስና ዕድሜያቸው በትምህርታቸው “ሰቃይ” እንደነበሩም እናውቃለን - ከታሪክ ዶሴያቸው፡፡ (ከህፃናቱ ብዙ መለሶችን ለመፍጠር የሚጠብቀንን የቤት ሥራ አያችሁልኝ አይደል!) በስንፍና ተዳክመን ለልጆቻችን በቂ ትምህርትና ዕውቀት ካልሰጠናቸው ግን እነሱም ባዶ፤ አገሪቱም ባዶ ይሆናሉ (ሁሉም ዜሮ ዜሮ!)

ከጠ/ሚኒስትሩ ህልፈተ ህይወት ጋር በተያያዘ የአንድ ታዋቂ ደራሲ ልጅ አለ የተባለውን ደግሞ ልንገራችሁ (ለሠማችሁም ላልሰማችሁም) ታዳጊው እያለቀሰ ለአባቱ እንዲህ አለው “ከአሁን በኋላ ማን ከድህነት ያወጣናል?” አሪፍ የልጅ ጥያቄ ነው፡፡ መለስ በህፃኑ ውስጥ የፈጠሩትንም ተፅዕኖ ያሳየናል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ግን ማን ከድህነት እንደሚያወጣን ደግመው ደጋግመው ተናግረዋል፡፡ (ራሳችን ብቻ ነን!!) ልጆቻችንም ይሄን አውቀው ነው ማደግ ያለባቸው፡፡ ያኔ ከድህነት እስር ነፃ የወጣ ትውልድ እንፈጥራለን (ድህነትን ማጥፋት ከአስተሳሰብ ይጀምራል እንዲሉ)

ለሁለት ዓመት ከህመማቸው ጋር እየታገሉ ለአገራቸው ሲለፉ ያለፉት ጠ/ሚኒስትሩ በአንድ ወቅት ወጣቶችን ሰብስበው ለሥራና ለትጋት የሚነሽጥና የሚያነቃቃ (Inspire የሚያደርግ) ንግግር አድርገዋል “…እነ አሞራውና ባለቤቱ ዋናውን ጠላት ሳያገኙት የድህነት ዘበኛ የነበረውን ስርዓት ሲፋለሙ አልፈዋል፡፡ እናንተ ዋናውን ጠላት ድህነትን ለመፋለም ዝግጁ ናችሁ” ብለዋል (ቃል በቃል ባይሆንም በጥቅሉ) እርግጠኛ ነኝ የቱንም ያህል የተለየ የፖለቲካ አቋም ቢኖረንም፤ የቱንም ያህል ኢህአዴግን ብንጠላውም ይሄንን እርቃኑን የወጣ ሃቅ ግን ልንክደው አንችልም (ኢህአዴግን መጥላት ሌላ፤ ሃቅን መካድ ሌላ)

እንዴ የኑሮ ውድነቱ፣ ግሽበቱ ወዘተ የሚጫወቱብን ለምን ሆነና? በድህነታችን አይደለ እንዴ! እናላችሁ… በሰሞኑ ሃዘን ልባቸው የተሰበሩ ሁሉ ቂማችንን በድህነት ላይ እንወጣለን ቢሉ እውነት አላቸው፡፡ ድህነት ቀንደኛ ጠላታችን እኮ ነው - ነፃነታችንን የቀማን፤ አንገታችንን ያስደፋን፡፡

ይሄውላችሁ…ምናልባት ለጠ/ሚኒስትሩ ውዳሴ ያበዛሁ ከመሰላችሁ “ሰው ካልሞተ አይመሰገንም” የምትለዋን የአበሻ ተረት አስታውሱና ይቅርታችሁን በዛ አድርጋችሁ ስጡኝ፡፡ ለነገሩ የዛሬው ፖለቲካዊ ወጌ ውደሳ ብቻ ሳይሆን ወቀሳና ትችትም ያካትታል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ላይ ሳይሆን ኢህአዴግ ላይ፡፡ ለምን መሰላችሁ … እሳቸው አረረም መረረም የቻሉትን ሁሉ ጥረው ግረው በአርአያነት እስከወዲያኛው አሸልበዋል (ታጋይ እንጂ ትግል አይሞትም እንዲሉ!)

አሁን እንግዲህ ጣታችንን ወደ ጠ/ሚኒስትሩ መጠቆም አከተመ፡፡ አሁን ወደ አውራው ፓርቲ ብቻ ነው - ወደ ኢህአዴግ፡፡ ለምን የተባለ እንደሆነ … አውራ ፓርቲ እንኳንስ አውራ መሪውን አጥቶ ሳያጣም እንኳን የሚያሳድገውና የሚያፋፋው እንዲሁም የብርሃኑን መንገድ የሚያሳየው ትችትና ነቀፋ እንደሆነ ኢህአዴግም አሳምሮ ያውቀዋል (ፓርቲውም እኮ ግለሂስ፣ ግምገማ ወዘተ ይለዋል)

አያችሁ… ለተወሰኑ ጊዜያት ኢህአዴግ የመገማገሚያ ጊዜ ስለሌለው እኛ እየገመገምነው ቢያዘግምስ ብያለሁ፡፡ (ይበጀዋል እንጂ አይጐዳውም እኮ)

እኔ የምለው…ህዝቡ በጠ/ሚኒስትሩ ድንገተኛ ህልፈተ - ህይወት በተሰማው ጥልቅ ሀዘን ኢህአዴግ ምን ተሰምቶት ይሆን? በኢቴቪ ለህዝቡ ያቀረበውን ምስጋና ዘንግቼው እንዳይመስላችሁ፡፡ ሌላ ያልነገረንን ውስጣዊ ስሜቱን ማወቅ ፈልጌ ነው (ኢህአዴግ ቆቅ እኮ ነው!) እንዴ ሳያስበው ህዝቡ በሃዘን ስሜት የመዲናዋን ጐዳና ሲያጥለቀልቀው እንዴት አይደናገር … እንዴት ግራ አይጋባ! (እንደ 97ቱ ዓይነት ዱብዕዳ ስሜት ቢፈጠርበት እኮ አንፈርድበትም) በነገራችን ላይ ህዝቡ (ደጋፊውም ተቃዋሚውም፤ ፖለቲካ የገባውም ያልገባውም) እንዲህ ልቡ የተሰበረው ለኢህአዴግ ሳይሆን ለታላቁ መሪ ይመስለኛል፡፡ ኢህአዴግ ይሄን ያህል ድጋፍ ያገኘ ዕለት ህዝቡ በቀን ሦስት ጊዜ መብላት ጀምሯል ማለት ነው፡፡ ያኔ በኑሮ ውድነት ማዕበል ከመላጋት ተርፏል ማለትም ነው፡፡

አንዳንዴ ሳስበው … ኢህአዴግ 21 ዓመት ገዝቶንም በቅጡ የሚያውቀን አይመስለኝም (ትንግርት ሆነንበታል) እንዲያ ባይሆንማ ኖሮ የጠ/ሚኒስትሩን ህመም ሳይነግረን ቆይቶ “ምነው ምነው ይህን ፈጣሪስ ይወደዋል?” ስንለው፤ “ምን ላድርግ ወድጄ እኮ አይደለም፤ የፓርቲው ባህል ስለሆነብኝ ነው” አይለንም ነበር፡፡ እንዴት ገዢ ፓርቲ ከመረጠው ህዝብ ምስጢር ይደብቃል - ያውም የገዛ መሪውን፡፡ እንዲህ ደም እንባ የሚያፈስለትን አርአያውን! ይሄውላችሁ… ኢህአዴግ ምስጢራዊነት ባህሌ ነው በሚል ተልካሻ ምክንያት የጠ/ሚኒስትሩን ህመም ባይደብቀንና በየጊዜው ስለጤንነታቸው ሁኔታ ቢያሳውቀን ኖሮ ሃዘናችን ባይቀርም ዱብዕዳነቱ ግን ይቀንስልን ነበር፡፡

አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት፤ ኢህአዴግ አንዳንዴ የሚመራውን ህዝብ (80 ሚሊዮን የተባልነውን) ትቶ ቀልቡ ሁሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ ያርፋል (ፈርዶበት እኮ ነው!)

ለምሳሌ ከጠ/ሚኒስትሩ ህልፈት ቀደም ብሎ በህመማቸው ዙሪያ የተለያዩ የማህበረሰብ ድረገፆች ሲያናፍሱት የነበረውን ወሬና አሉባልታ አስመልክቶ ጥያቄ የቀረበላቸው የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስትሩ ክቡር አቶ በረከት ስምኦን ሲመልሱ፤ “እያንዳንዱን አሉባልታ እየተከታተልን መልስ አንሰጥም” ብለው ነበር (በደምሳሳው) ግን እኮ አሉባልታውን ችላ ብለው ለእኛ ለሚመሩን ህዝብ መረጃ ቢሰጡን ችግሩ ይቃለላል፤ ግልጽነትም ይሰፍን ነበር፡፡ ግን ደግሞ ልንፈርድባቸው አንችልም (እውነቱን ነግረውናላ!) የቆየ የምስጢራዊነት ባህል ምንም ቢሆን በአንድ ጀንበር ሊለቃቸው አይችልም - እሳቸውንም ፓርቲያቸውንም፡፡ በእርግጥ ነገርዬውን በእሳቸው ቦታ ሆኜም ልመለከትላቸው መሞከሬ አልቀረም፡፡

በፌስ ቡክ የጠ/ሚኒስትሩን ክፉ ክፉ ሲያሟርቱ የነበሩ ዳያስፖራዎችም እርር ድብን እንደሚያደርጉ አላጣሁትም፡፡ እሳቸውም ሆኑ ፓርቲያቸው ያላወቀው ግን እዚህ አገሩ ምድር ላይ ያለ የአቢሲኒያ ዘር ሁሉ ምን መሪውን አምርሮ ቢጠላ፤ ምን በመሪው የግፍ አገዛዝ ተሰላችቶ እንባውን ወደ ሰማይ ቢረጭ፤ ምናልባት ከሥልጣን እንዲወርድለት ጓዳው ተደብቆ ለፈጣሪው ይማፀን ይሆናል እንጂ “እሰይ ታመመልኝ፤ እሰይ ሞተልኝ” የሚል ክፉ ህዝብ አይደለም፤ እንዲያ ሆኖም አያውቅም፡፡ እንኳን ለመሪው ለግለሰብ ባላንጣው እንኳ እንዲህ ዓይነት ክፉ ምኞት የሚመኝ ህዝብ አይደለም፡፡ ለምን ቢባል? ጨዋ ባህል ያለው ህዝብ ነዋ! (እኛ ያነሰን እኮ ጨዋ የፖለቲካ ባህል ብቻ ነው!) ለዚህ ነው የመሪውን ህመም ከሰማ ጀምሮ ከህመማቸው እንዲፈወሱ ለየፈጣሪው ሲፀልይ የሰነበተው፡፡ ህልፈተ ዜናቸውን ሲሰማም ልቡ በሀዘን የተሰበረው፡፡ (ፖለቲካ ሌላ ሰብዓዊነት ሌላ!)

እንግዲህ ገዢያችን (መሪያችን ቢሆንልን እንመኛለን) ኢህአዴግ ነፍሴ ካለፈው ስህተቱ ተምሮ የበረሃ ባህሌ ነው ያለንን የምስጢራዊነት ባህሉን እርግፍ አድርጐ እንዲተውልን በሰማይ በምድር አደራ እንለዋለን (ምን እናድርግ? ቢጨንቀን እኮ ነው!)

እናላችሁ… ጠ/ሚኒስትሩ ለሁለት ዓመት ከህመማቸው ጋር እየታገሉ ለአገር ሲሰሩ እንደነበር የተነገረን ከህልፈታቸው በኋላ ነው፡፡ እኔ የምለው … ለምንድነው ይሄ ሁሉ የበዛ መስዋዕትነት በእሳቸው ላይ የተጫነው፡፡ በቃኝ ልረፍ ሲሉስ ለምንድነው “ይሄማ ከትግል መሸሽ ነው” የተባሉት? ከምሬ ነው ኢህአዴግ በጣም አጥፍቷል፡፡ በአንድ ወቅት ጠ/ሚኒስትሩ ለጋዜጠኛ በሰጡት ቃለ ምልልስ ዕረፍት ምን እንደሆነ አላውቅም፤ ዕረፍት ናፍቆኛል ማለታቸው ይታወሳል (ኢህአዴግን ትዝብት ላይ የሚጥል ነው) መለስ ፓርቲውንም አገርንም ሆነ ህዝብን የበለጠ ይጠቅሙ የነበረው በህይወት ቢኖሩልን እኮ ነበር!

አሁንም ቢሆን እረፍት የሚያስፈልጋችሁ የኢህአዴግ አመራሮች በወቅቱ እረፍት ትወስዱ ዘንድ በትህትና እንጠይቃለን (መተካካት የተባለው ለዚሁ መስሎኝ!) የሆኖ ሆኖ የፈሰሰ ውሃ አይታፈስምና ጠ/ሚኒስትሩን አጥተናቸዋል፡፡ (ነፍሳቸውን በመንግስተ ሰማያት ያኑርልን፤ ለቤተሰቦቻቸውና ለኢትዮጵያ ህዝብ ፈጣሪ መጽናናትን ይስጥልን!) በእሳቸው ሞት የተንገበገበውና የተቆጨው ህዝብ ግን አንድ መጽናኛ ያገኘ ይመስለኛል፡፡ ይኸውም የእሳቸውን ራዕይ ከግብ በማድረስ እሳቸውን ህያው ማድረግ፡፡ ማለፊያ መጽናኛ ነው (ግን ከልባችን ይሁን!) ድህነት ይወገዳል ስንል ከልባችን፡፡ አባይ ይገደባል ስንልም ከልባችን፡፡ በኢኮኖሚ እንመነደጋለን ካልንም ከምራችን!

የጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ህልምና ራዕይ ይሄ ብቻ እንዳልሆነ ግን ልናውቅ ይገባል፡፡ ሙስናን ካላጠፋን የአገር ዕድገት አይታሰብም ብለው ነበር (የመንግስትና የግል ሌቦች ያሏቸው እንዳይዘነጉ) የመድብለ ፓርቲ ሥርዓትን በጽኑ መሰረት ላይ ለማቆም የተጉ መሆናቸውም እንዳይረሳ (እንዳሰቡት ባይሳካም) የዜጐች ሰብዓዊ መብት እንዲከበርም ፈር ቀደዋል (ገና ቢዙ ቢቀርም) ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ፣ የመሰብሰብ፣ የመደራጀት ህገመንግስታዊ መብቶችን ማስከበርም የህይወት ዘመን ዓላማቸው ነበር (ብልጭ ድርግም እያለ ቢያስቸግርም) እሳቸው ከታመሙ ወዲህ ጭልጭል ማለት የጀመረው የፕሬስ ነፃነትም ቦግ ብሎ ሊበራ የግድ ይላል፡፡ ሌላም የመለስ ራዕይ አለ - ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መፍጠር (አሁን ኢህአዴግ ይፈተንበታል) እኒህን እውን ስናደርግ ነው ጠ/ሚኒስትሩ ህያው የሚሆኑት!) በአካል ቢለዩንም በመንፈስ አብረውን ይኖራሉ ማለት ያኔ ነው፡፡ ያኔ አፋችንን ሞልተን ጠ/ሚኒስትሩ አልሞቱም፤ ህያው ናቸው ማለት እንችላለን -  ድምፃችንን ከፍ አድርገን፡፡

ህዝቡ የመለስን ራዕይ ለመፈፀም ቃል እንደገባው ሁሉ ኢህአዴግም ከዚህ በኋላ ወደፊት እንጂ ቅንጣት ታህል የኋሊት እንደማይጓዝ አሁኑኑ ቃል ይግባልን -በፖለቲካውም፤ በኢኮኖሚውም፡፡ ይሄ ጨዋ ህዝብ ዳቦም ዲሞክራሲም ሊጠግብ ይገባል፡፡

ልብ አድርጉ! ጠ/ሚኒስትሩ፤ ዲሞክራሲ ለኢትዮጵያ ህዝብ የህልውና ጉዳይ ነው ብለው ነበር፡፡ ኢህአዴግ ይሄንን እውን ያድርግ! ይሄን የምንጠይቀው የጠ/ሚኒስትሩም ራዕይ እውን እንዲሆንና እሳቸውም ህያው እንዲሆኑ ጭምር ነው፡፡ ይሄን ካልቻለ ግን የኢህአዴግ አመራሮች ብቻ ሳይሆኑ ፓርቲውም እረፍት ያስፈልገዋል፡፡ (ድሃ አገር የሚመራው እኮ አረፍ እየተባለ ነው)

 

 

Read 3450 times Last modified on Saturday, 01 September 2012 10:38