Saturday, 01 September 2012 10:36

“እኔ ስሰራ ስሰራ ደከመኝና ተኛሁ፡፡ እናንተስ?” ሰውየውና ፖለቲከኛው መለስ ለየቅል ናቸው!

Written by  ኤሊያስ
Rate this item
(3 votes)

ባለፈው ሳምንት የፖለቲካ ወጌ ልገልጽላችሁ እንደሞከርኩት ይሄ ህዝብ ደስ የሚል ህዝብ ነው፡፡ ደስ የሚል ብቻ ሳይሆን ጨዋም ህዝብ ነው፡፡ ታላቅ ህዝብ፡፡ (ለመሪው ክብር የሚሰጥ ነው ያለው ገጣሚው) በብዙ የአፍሪካ አገራት መሪ ሲሞት የሚፈጠረውን ምስቅልቅልና ትርምስ እናውቅ የለ…እዚህ ግን ሀዘንና ለቅሶ ብቻ ያውም የሰከነና የተረጋጋ፡፡ በእርግጥ ግርግር ለሌባ ይመቻል እንዲሉ… በአጋጣሚው ለመመዝበር፣ ውለታ ለማስመዝገብ፣ ያለአግባብ ለመክበር የሚታትሩ አይጠፉም፡፡ ሰፊው ህዝብ ግን (አብላጫው) ለዚህ ከንቱነት ሳይበገር በጨዋነቱ ገፍቶበታል- ህልፈተ ዜናው ከተሰማበት ዕለት አንስቶ እስከዛሬ፡፡

ለነገሩ ዓይን እያላቸው አያዩም፤ ልብ እያላቸው አያስተውሉም ሆኖ ነው እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ ትልቅነቱንም ጨዋነቱንም ሲያስመሰክር የአሁኑ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ ለምሳሌ በ92 ዓ.ም የኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት ወቅት የኢህአዴግ ደጋፊም ሆነ ተቃዋሚ አንድነቱን አስመስክሮ ነበር - በእማማ ኢትዮጵያ ቀልድ የለም ብሎ ወደ ጦር ሜዳ በመትመም (ፖለቲካ ሌላ የአገር ጉዳይ ሌላ ማለቱ እኮ ነው!)

አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ኢህአዴግ አይገመቴ (unpredictable) ፓርቲ ነው እያሉ ሲያሙት ሰምታችሁ ይሆናል፡፡ እኒሁ ተንታኞች አሁን ደግሞ አይገመቴ የሆነብንስ የኢትዮጵያ ህዝብ ነው እያሉ ነው - በጠ/ሚኒስትሩ ሞት ከምር ማዘኑን አይተው (የህዝቡን ባህል ካለማወቅ የመነጨ ነው ብዬዋለሁ)

ለእኔ ግን ከማንም በላይ አይገመቴ (Unpredictable) የሆኑብኝ አንዳንድ የዳያስፖራ ፖለቲከኞች ናቸው  (የብሎግ ታጋዮች)፡፡

እውነቴን ነው የምላችሁ… እነዚህ ፖለቲከኞች አንድም የፖለቲካ ሀሁ (Politics 101) አያውቁም፤ አሊያም እንታገልለታለን ከሚሉት ህዝብ ጋር ፈጽሞ አይተዋወቁም፡(ወይስ የሚታገሉለት ህዝብ የላቸውም) እንዲያ ባይሆንማ ኖሮ በጠ/ሚኒስትሩ ህልፈት አገር ሲያዝን እነሱ ደስታቸውን አይገልፁም ነበር (በእነሱ ቋንቋ እልልል…አይሉም) እንግዲህ በመሪያችን ሞት እስካሁን በይፋ ደስታውን የገለፀው አልሸባብ ብቻ ነው (ወይ አለመታደል ብያቸዋለሁ!) ይኸውላችሁ…ሰብዓዊነቱ ቢቀር እንኳ ነገርዬውን ከፖለቲካ አንፃር ሊያዩት ይገባ ነበር፡፡  ፈጽሞ አዋጩ እኮ አይደለም! እንዴ… የህዝቡን ስሜትና የልብ ትርታ የማያዳምጥ ፖለቲከኛ ምኑን ፖለቲከኛ ሆነው? ለነገሩ የዳያስፖራ ፖለቲከኞች ሁሌም “ማኖ” እንደነኩ ነው (ምን እያቀመሷቸው ይሆን?)

ትዝ ይላችኋል…የ2002 ምርጫ ጊዜ! የኢህአዴጉ ሊ/መንበር አቶ መለስ ዜናዊ ከተቃዋሚ ፓርቲው ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ሃይሉ ሻውል ጋር ተጨባበጡ ብለው ቀውጢ እንደፈጠሩ! (ደግነቱ በዌብሳይትና በብሎግ ነው) እንዴ…ግራ ገባን እኮ! የዳያስፖራ ፖለቲከኞች ምንድነው የሚፈልጉት? ኢህአዴግ ከተቃዋሚ ጋር መስራት አይፈልግም እያሉ አገር ሲቀውጡ ኢህአዴግ “ጉዳቸውን ልይ” ብሎ ነው መሰለኝ ከአንዳንድ ተቃዋሚዎች ጋር እሰራለሁ በሚል የምርጫ ሥነምግባር ኮድ ተፈራርሞ እጅ ለእጅ ሲጨባበጥ አገር ይያዝልን አሉ (ተሙለጨለጩብን እኮ!)

ሰሞኑን በብሎግ ታጋዮች ምላሽ (reaction) በጣም የበሸቀባቸው የ60ዎቹ ፖለቲከኛ ወዳጄ ምን እንዳለ ታውቃላችሁ? አንዳንድ የዳያስፖራ ፖለቲከኞች ራሳቸውን በራሳቸው እያጠፉ ነው (Suicide እየፈፀሙ ነው እንደማለት) ሲል ሹክ ብሎኛል፡፡ ፖለቲካዊ ህይወታቸው ህልውናቸውን እያጠፉ ነው ለማለት ፈልጐ መሰለኝ፡፡ እውነቱን እኮ ነው፡፡ ይሄ እኮ በእርግጥም ትልቅ የፖለቲካ ኪሳራ ነው (ብታምኑም ባታምኑም ቀልጠዋል!) ለዚህ ኪሳራ የዳረጋቸው ደግሞ ሌላ ሳይሆን አጉል ቅብጠትና ግልብነት ነው፡፡ ፖለቲካንና ሰብዓዊነትን የመደባለቅ ቅብጠት! እንዴ በሃገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንኳን ነቄ ብለዋል እኮ! እኔ እኮ የዳያስፖራ ፖለቲከኞች በጠ/ሚኒስትሩ ህልፈት የግድ ይዘኑ ወይም ማቅ ይልበሱ አልወጣኝም (አለማዘን ህገመንግስታዊ መብታቸው አይደል!) ግን ደግሞ መለስን በመሪነታቸው ባይወዷቸውም እንኳ ሞታቸው ፈጽሞ እልል ሊያስብላቸው አይገባም ባይ ነኝ (ምን ሊጠቀሙ?) ደግሞ እኮ የበደልና የአፈናው ገፈት ቀማሾችም እኮ የአገር ውስጥ ተቃዋሚዎች እንጂ ዳያስፖራዎቹ እንዳልሆኑ አሳምረን እናውቃለን፡፡

በሽብርተኝነት ተከሰው እስር ቤት የተወረወሩት የዳያስፖራ ፖለቲከኞች ሳይሆኑ ሎካሎቹ ተቃዋሚዎች ናቸው (የምጣዱ እያለ የእንቅቡ ተንጣጣ አሉ!) ሆኖም የአገር ውስጥ ተቃዋሚዎች የዳያስፖራዎቹ ዓይነት ጭካኔና ኢ-ሰብዓዊነት ፈጽሞ አላሳዩም (ሰው ከአገሩ አፈር ከተለየ እርባና የለውም እንዳልል… ስንት ውሃ የሚያነሱ ዳያስፖራዎች አሉ መሰላችሁ!) እኔ የምላችሁ…ጠ/ሚኒስትሩ በመሞታቸው ዳያስፖራዎቹ ፖለቲካዊ ትርፋቸው ምንድነው? ኢህአዴግ እንደሆነ ቁርጡን ተናግሯል - በጠ/ሚኒስትሩ ህልፈተ - ህይወት ሳቢያ ከቀድሞው የሚለወጥ አንዳችም ነገር እንደሌለ (ኢህአዴግ እኮ አልሞተም!)

ለጊዜው የዳያስፖራ ፖለቲካን ድርብርብ ኪሳራ ለባለቤቶቹ እንተውላቸውና (ምን ያገባናል!) ስለ ቀድሞው የአገራችን ጠ/ሚኒስትር አንዳንድ ነገሮች እናውጋ፡፡ ይሄውላችሁ… ሰውየው ከሞቱ በኋላ በቅርብ ወዳጆቻቸው የሚሰጡ ምስክርነቶች ጥያቄ እንድናነሳ የሚያደርጉን ሆነዋል - “ሰውየውን አናውቃቸውም ነበር እንዴ?” የሚል እናም ፖለቲከኛውንና ሰውየውን (The politician and The man እንዲሉ) መለስ በቅጡ፤ መመርመርና መፈተሽ ሳይኖርብን አይቀርም፡፡

አሁንማ ሳስበው የኢህአዴጉ ሊ/መንበር መለስ፤ በፓርላማ ተቃዋሚዎችን አንዳንዴ ሲተርቡ ሌላ ጊዜ በነገር ሲሸነቁጡ፤ ባስ ሲልም ሲያስጠነቅቁ የምናውቃቸው መለስ፤ ከሰውየው፤ (ከሰብዓዊው መለስ) ጋር ተቃራኒ ይመስሉኛል፡፡  ይሄን የምለው እኮ በግምት አይደለም - በመረጃና በማስረጃ ላይ ተመስርቼ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት በወጣው አዲስ አድማስ ላይ ያገኘሁትን ማስረጃ ተመልከቱልኝ፡፡

ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ ስለ ጠ/ሚኒስትሩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ “አቶ መለስ ውጤትና ሰላም ፈላጊ … ምክር ተቀባይ ነበሩ፡፡ ይሁን ያልናቸውን ተቀብለው ሂደቱን ያሳውቁናል፡፡ እንደዚህ እናድርግ፤ እንደዚህ ይሁን ይላሉ፡፡ ከትግል ሜዳ ጊዜ ጀምሮ የኦነግ፣ የኤርትራ፣ በቅርብም የቅንጅት ጉዳይ በተነሳ ጊዜ መልካም ምላሽን በመስጠት አክብረውናል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ (እርግጠኛ ነኝ አብዛኞቻችን እኚኛውን መለስ አናውቃቸውም) በ97ቱ የፖለቲካ ቀውስ ወቅት ስለነበረው ሁኔታ ሲያስታውሱም፤ “እንደተነጋገርነው ፓርላማ ገብተው ቦታቸውን እንዲይዙ፤ የአዲስ አበባ መስተዳድር ቦታቸውን እንዲወስዱ፤ እኛ ደግሞ ኢትዮጵያን ማስተዳደራችንን እንቀጥላለን፤ እናንተ ምክራችሁ ይቀጥል” ሲሉ ጠ/ሚኒስትሩ ደብዳቤ እንደፃፉላቸው ገልፀዋል - ፕሮፌሰሩ፤ እኔም አዲስ አበባ ደውዬ ከሽማግሌዎቹ ጋር ተነጋገርኩ ያሉት ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ፤ ጠ/ሚኒስትሩ ነገሩ መካረሩን አይተው በድጋሚ ደብዳቤ እንደላኩላቸው አውስተዋል “ይፍጠኑ! አሁን በቅርቡ ትልቅ ሰላማዊ ሰልፍ ይደረጋል፤ ይሄ ከሆነ ደግሞ ግጭት ሊፈጠር ይችላል፡፡ ፓርላማ ገብተው ሥራቸውን እንዲሰሩና  ነገሩ እንዳይባባስ ያድርጉ” የሚል ማሳሰቢያ ያዘለ ነበር የጠ/ሚኒስትሩ ደብዳቤ፡፡ አይገርምም! ጠ/ሚኒስትሩ፤ በመንግስትና በቅንጅት ፓርቲ መካከል የተፈጠረው ግጭትና አለመግባባት በሰላምና በእርቅ እንዲፈታ ይጥሩ ነበር እያሉን ነው - ፕሮፌሰሩ፡፡ ለዚህ እኮ ነው እኛ ፖለቲከኛውን መለስ እንጂ ሰውየውን መለስ አናውቃቸውም ነበር የምለው፡፡

እንዴ … እኛ የምናውቃቸው መለስ እኮ ተቃዋሚዎችን ሲያስፈራሩና ሲያስጠነቅቁ እንጂ ሲያባብሉና እሹሩሩ እያሉ ለመደራደር ሲታትሩ አይደለም፡፡ እናላችሁ…እኛ እስከ ዛሬ የምናውቃቸው የኢህአዴጉን መለስ እንጂ ሰውየውን (ሰብዓዊውን) መለስ አይደለም እያልኳችሁ ነው፡፡

በትሁትነታቸው የማውቃቸው ቅን አሳቢው ፕሮፌሰር ኤፍሬም ስለ አቶ መለስና ቤተሰቦቻቸው ከዚህ ቀደም ያልሰማነውንም እውነታ እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል፤ “በዓለም ላይ ብዙ መሪዎችን አውቃለሁ፡፡ ብዙዎቹ ትዕቢተኞች ናቸው፤ ይኩራራሉ፡፡ በአቶ መለስ ዘንድ ግን ይህን አይቼ አላውቅም፡፡ ቅን፣ ሰው አክባሪና ትሁት ናቸው፡፡ ቤተሰቦቻቸው ሁሉ እንደተራው ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡ … ከባለቤታቸውና ከልጆቻቸው ጋር ቅርበቱ አለኝ፡፡ በጣም ስብር ያሉ የእግዚብሔር ሰው ናቸው” (ዘይገርም ነው!) እውነቴን ነው የምላችሁ … እኔ ይሄን ምስክርነት የሰማሁት ከኢህአዴግ ሰው ቢሆን ኖሮ “ምን ይተረተራል!” ነበር የምለው፡፡ ግን የማምናቸው ትልቅ ሽማግሌ የሰጠሁት ምስክርነት ነው፡፡ እናም እውነተኛውን መለስ  አናውቃቸውም ማለቴ ትክክል ነው፡፡  ይታያችሁ … ይሄኛውን መለስ ቀደም ሲል ብናውቅማ ኖሮ አገር ከዚህም የባሰ ይቀወጥ ነበር  (በሃዘንና በለቅሶ!) አስቤ አስቤ ታዲያ ምን አልኩ መሰላችሁ … መለስ እንዲያ የነበሩት (ከሰብዓዊ ማንነታቸው ፍፁም የተለዩብን ማለቴ ነው) ምናልባት ለፓርቲያቸው ሲሉ ሳይሆን አይቀርም፡፡

የፓርቲ ዲስፕሊን ጠፍሮ ይዞአቸው፡፡ ለእኛ ግን ከኢህአዴጉ ወይም ከፖለቲከኛው መለስ ይልቅ ሰውየው መለስ ይሻሉን ነበር፡፡ (አሁንማ አልፏል!) በነገራችሁ ላይ አንዳንድ በጠ/ሚኒስትሩ ህልፈት ልባቸው የተሰበረ ኢትዮጵያውያን ሰሞኑን ለእሳቸው ማስታወሻ ይሆኑ ዘንድ የተለያዩ ሃሳቦች ሲሰነዝሩ ሰንብተዋል፡፡ አንዳንዶቹ ታላቁ የህዳሴ ግድብ በስማቸው ይሰየም ባይ ናቸው - “ታላቁ የመለስ ግድብ” በሚል፡፡ ሌሎች የአቶ መለስ ምስል ያለበት ድፍን 500 ብር እንዲታተም ሃሳብ ሰንዝረዋል - ለመለስ መታሰቢያነት፡፡ የአሁኑ የ100 ብር ኖታችን ላይ የመለስ ምስል እንዲታተም ሃሳብ የሰጡም አልጠፉም፡፡ እኒህ ሁሉ በሃሳብ ደረጃ የተሰነዘሩ ናቸው፡፡ አንድ የክልል ዩኒቨርስቲ ግን ጣጣ ፈንጣጣ ሳያበዛ አንዱን የትምህርት ዲፓርትመንት በእሳቸው ስም መሰየሙን በመገናኛ ብዙሃን ሰምቻለሁ (ቀድሞ መገኘት ይሏል እንዲህ ነው!) ሃውልት እንዲሰራላቸው ሃሳብ ያቀረቡም አሉ፡፡

በነገራችሁ ላይ የግልና የመንግስት ድርጅቶች በጠ/ሚኒስትሩ ህልፈት የተሰማቸውን ሃዘን በየጋዜጦቹ ላይ እንደጉድ እየገለፁ ነው፡፡ የሃዘን መግለጫዎቹ ተመሳሳይና Creativity የጐደላቸው ቢሆኑም! (ሃዘንም እኮ በፈጠራ ጥበብ ይገለፃል!)

እኔ የምለው … ሁሉም የጠ/ሚኒስትሩን ራዕይና ህልም እናሳካለን እያሉ ነው አይደል? (ገብቷቸው ከሆነ ጥሩ  ነው) አንድ ነገር ግን ላሳስባቸው እወዳለሁ ይኸውም ጠ/ሚኒስትሩን ራዕይ ማሳካት ማለት ሌላ ሳይሆን በተሰማራንበት የሥራ መስክ ጠንክረን መስራት ማለት መሆኑን ነው፡፡ (እሳቸው እኮ የግል ራዕይ የላቸውም የአገር እንጂ!) እናም ዶክተሩ በህክምናው፣ መምህሩ በማስተማሩ፣ ኢንቨስተሩ በንግድ ዘርፉ፣ መንግስት በአመራሩ ወዘተ… ሁሉም ሥራውን በትጋት ሲሰራ ብቻ ነው አገር የምታድገውና የምትበለጽገው፡፡ ያኔ እንቅልፍ የነሳን ድህነት ከጦቢያ ምድር ይጠፋል፡፡ ድህነት ሲጠፋ ደግሞ የጠ/ሚኒስትሩ ህልምና ራዕይ ተሳካ ማለት ነው፡፡ (ሌላ ተዓምር እንድንፈጥር አይጠበቅብንም እያልኳችሁ ነው) እኔን ካለመናችሁኝ ግን ራሱን ኢህአዴግን ጠይቁት፡፡ ይሄንኑ ነው የሚደግምላችሁ!

የዛሬውን ፖለቲካዊ ወጌን ከመቋጨቴ በፊት ከዚሁ ከጠ/ሚኒስትሩ ሃዘን ጋር በተያያዘ ኢህአዴግ የሚታማበትን ድርጅታዊ አሰራር የምትጠቁም ነገር በፌስ ቡክ ላይ አግኝቻለሁና ላጋራችሁ (ሃሜቱ ኢህአዴግ ሃዘኑን ድርጅታዊ አድርጐታል የሚል ነው) እንግዲህ የፌስ ቡክ መረጃዎች እንደሚሉት… የአለቃቀስ ግምገማ በየቀበሌው ይካሄዳል (መቼም ኢህአዴግ አያደርገውም አይባልም!) እናላችሁ… ለዚሁ ግምገማ የተዘጋጀ ቅፅ አለ አሉ፡፡ የአልቃሹ ሽም   ------  ቀበሌ ------ ያለቀሰበት ቋንቋ ------ ወዘተ በሚል የተዘጋጀ፡፡ እኔ በበኩሌ ይሄ ነገር የፌስቡክ ፈጠራ ሳይሆን አይቀርም ብዬ አልፌዋለሁ፡፡

እውነት ከሆነ ግን ኢህአዴግን እንደተለመደው እታዘበዋለሁ ማለት ነው፡፡ እንዴ… ልባዊ ሃዘናችንማ እንዲገመገምብን አንፈልግም፡፡ ለማንኛውም ግን ኢህአዴግ “ህዝብ አዋሽ ነው፤ የአዋሽ ማዕበል” የሚለውን ግጥም እንዲያነብ ጋብዤዋለሁ - ባለፈው ሳምንት እዚሁ ጋዜጣ ላይ የወጣውን ማለቴ ነው፡፡ እንግዲህ ነገ የጠ/ሚኒስትሩ የቀብር ሥነ ስርዓት ይካሄዳል፡፡

የታላቁ ሰው የስንብት ቃል ምን ይሆን እያልኩ ሳሰላስል ባለፈው ሳምንት በወጣው የአዲስ አድማስ ዕትም ላይ “ታላላቅ ሰዎች በሞታቸው የመጨረሻ ሰዓት ካሉት” በሚል ከሰፈረው ውስጥ አንደኛው ትዝ አለኝ - “እኔ ስሰራ ስሰራ ስሰራ ደከመኝና ተኛሁ… እናንተስ?” ይላል - ፓስተር አንድሩ ቺፕስ የተባሉት ግለሰብ የተናገሩትን በመጥቀስ፡፡ የጠ/ሚኒስትሩ የስንብት ቃልም ይሄው ይመስለኛል “እናንተስ?” የሚለውም ጥያቄ ለእኛ የተሰነዘረ መሆኑን እንዳትዘነጉት፡፡ ግን መልሳችን ምን ይሆን?

 

 

Read 2977 times Last modified on Saturday, 01 September 2012 10:38