Wednesday, 26 May 2021 00:00

በ2020 ወደ አገር ቤት የተላከው ገንዘብ ብዙም አልቀነሰም

Written by 
Rate this item
(0 votes)

      በውጭ አገራት የሚኖሩ የተለያዩ አገራት ዜጎች ወደ አገር ቤት የሚልኩት ገንዘብ (ሬሚታንስ) ከኮሮና ወረርሽኝ ቀውስ ጋር በተያያዘ ባለፈው የፈረንጆች አመት 2020 በአለማቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል ተብሎ የተጠበቀውን ያህል ቅናሽ አለማሳየቱንና በአመቱ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ወዳላቸው የአለማችን አገራት በድምሩ 540 ዶላር ያህል መላኩን የአለም ባንክ ከሰሞኑ ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡
በአመቱ ከተለያዩ የአለማችን አገራት ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ወዳላቸው አገራት የተላከው ገንዘብ በ2019 የፈረንጆች አመት  ከተላከው የቀነሰው በ1.6 በመቶ ያህል ብቻ ነው ያለው ሪፖርቱ፣ አገራቱ በአመቱ ከሬሚታንስ ያገኙት ገንዘብ ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና ከልማት ድጋፍ ከውጭ አገራት ካገኙት አጠቃላይ ገንዘብ በላይ እንደሆነም ገልጧል፡፡
የሬሚታንስ ገንዘብ በላቲን አሜሪካና ካረቢያን የ6.5 በመቶ፣ በደቡብ እስያና በመካከለኛው ምስራቅና ሰሜን አፍሪካ በ2.3 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን የጠቆመው ዘገባው፣ በአንጻሩ ደግሞ በምስራቅ እስያና ፓሲፊክ በ7.9 በመቶ፣ በአውሮፓና መካከለኛው እስያ በ9.7 በመቶ፣ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ደግሞ በ12.5 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱንም አመልክቷል፡፡
በዘንድሮው የፈረንጆች አመት 2021 ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ወዳላቸው አገራት የሚላከው ገንዘብ በ2.6 በመቶ በመጨመር ወደ 553 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ይላል ተብሎ እንደሚጠበቅም የአለም ባንክ ሪፖርት ትንበያውን አስቀምጧል፡፡

Read 2492 times