Print this page
Saturday, 05 June 2021 14:16

TradEthiopia.com የኦንላይን ኤክስፖ ያዘጋጃል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  የዛሬ ስድስት ዓመት የተመሰረተውና ንግዶችን ለማስተሳሰርና ለማቀላጠፍ ዓላማ የተመሰረተው TradEthiopia.com የኦንላይን ፕላት ፎርም፤ ከ30 በላይ የሀገር ውስጥና የውጪ አገራት የተውጣቱ ከ600 በላይ ኩባንያዎች የሚሳተፉበት የኦንላይን ኤክስፖ ሊያዘጋጅ መሆኑን አስታወቀ፡፡ ኩባንያው ባለፈው ሳምንት አጋማሽ በኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤  ኤክስፖውን በመጪው ሀምሌ ወር 2013 እና ህዳር 2014 ዓ.ም እንደሚያዘጋጅ፣ ለዚህም ከ30 የውጪና የሀገር ውስጥ ሀገራት የተወጣጡ 600 ኩባንያዎች መመዝገባቸውን የ”TradEthiopia” መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ በርናባስ ወ/ገብርኤል ተናግረዋል፡፡ እንደ ስራ አስፈጻሚው ገለጻ የTradEthiopia.com  ዋና ዓላማ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት፣ የውጪ ምንዛሬ እጥረትን ለመቅረፍና ስራ አጥነትን ለመቀነስ የሚሰራ ሲሆን ለምሳሌ ወሳኝ የማህበረሰቡ ፍጆታዎችን ከአምራች አርሶ አደሩ በቀጥታ በመሰብሰብ፣ መሃል ያሉ የተጋነነ ትርፍ የሚፈልጉ ነጋዴዎችን በማስወጣት ሻጩ አርሶ አደርም ሆነ ተጠቃሚው ማህበረሰብ በቀጥታ እንዲገበያዩና ሚዛናዊ ተጠቃሚነትን እንዲያገኙ በማድረግ የኑሮ ውድነትን ማረጋጋት እንደሚቻ ገልፀው የኢትዮጵያን ምርቶች የሚገዙ የውጭ ኩባንያዎችን በቀጥታ ከአቅራቢ ጋር በማገናኘት የኢትዮጵያ ምርቶች ሳይባክኑና ሳይበላሹ ቀጥታ ለውጭ ገዢዎች ቀርበው ትክክለኛ የሆነ የውጪ ምንዛሬ እንዲያመጡ ማድረግ ይቻላል ብለዋል፡፡ አቶ በርናባስ አክለውም ገበሬው፣ ቆዳና ሌጦ አምራቹ የቅባትና ጥራጥሬ ላኪው ትክክለኛ ዋጋ ሲያገኝ ምርታማነት ይጨምራል፣ ያኔ እንቅስቃሴ  ይኖራል፡፡ እንቅስቃሴ ሲኖር የሚሰራ የሰው ሀይል ይፈልጋል በዚህም ስራ አጥነትን መቅረፍ ይቻላል ሲሉ አብራርተዋል፡፡
TradEthiopia.com  እንደ  ትሬድ ቻይና ዶት ኮም፣እንደ ኢንዲያ ትሬድ ዶት ኮምና እንደ ኮሪያ ትሬድ ዶት ኮም ሁሉ ግብይትን በኦን ላይን በማስተሳሰር ቀልጣፋና የዘመነ የገበያ ትስስር በመፍጠር ለአርሶ አደሩ ያለ ኢንተርኔት አገልግሎት የሚሰጡ የአጭር ጽሁፍ መላኪያ ኮድ፣ በየአካባቢው የገበያ ትስስር ኮርነሮችን በመክፈት፣ የማህበረሰብ ሬዲዮኖችንና በየአካባቢው ያሉ የህብረት ስራ ማህበራትን በመጠቀም ያመረተው ምርት ድካሙን በሚያካክስ መልኩ ለትክክለኛ ገበያ እንዲያቀርብ ቅድሚያ ለአርሶ አደሩ ይሰጣል ብለዋል ዋና ስራ አስፈጻሚው፡፡
ኩባንያው እስካሁን ከ1ሺህ በላይ ቋሚ አባል የሀገር ውስጥና የውጪ ኩባንያዎችን ያቀፈ ሲሆን የሚተዳደረው በአባላት የአባልነት ክፍያ እንጂ ስራ ባስተሳሳረ ቁጥር  የኮሚሽን ክፍያ እንደማይቀበል የገለጹት አቶ በርናባስ፣ ኩባንያቸው የሚሰራው በሚመለከተው የመንግስት አካል ፈቃድና እውቅና ካላቸው፣ ትክክለኛ አድራሻ ካላቸውና ለመንግስት ትክክለኛውን ግብር ከሚከፍሉት ጋር እንደሆነ ገልፀው፣ ከሚሊዮን በላይ ኩባንያዎች በቋታቸው ይዘው ከላይ የተዘረዘሩትን መስፈርቶች ያሟላሉ አያሟሉም የሚለውን እያጣሩ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
ሀምሌ 2013 እና ህዳር 2014 ዓ.ም በሚካሄዱት የኦን ላይን አለም አቀፍ ኤክስፖዎች ብዙ ልምዶች፣ እውቀቶችና፣ ግብይቶች ያካሄዳሉ ብለው እንደሚጠብቁም አቶ በርናባስ ወ/ገብርኤል ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡

Read 1984 times
Administrator

Latest from Administrator