Saturday, 05 June 2021 14:31

40 ሚ. ብር የወጣበት ዘመናዊ የአይን ቀዶ ጥገና ማዕከል ስራ ጀመረ

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(2 votes)

   በአይን ህክምና ዘርፍ አንቱታን ባተረፉና የረጅም ጊዜ ልምድ ባካበቱ የአይን ህክምና ስፔሻሊስቶች በ2002 ዓ.ም የተመሰረተው “ዋጋ የአይን ህክምና ማዕከል” በ40 ሚሊዮን ብር  ያደራጀው የአይን ቀዶ ጥገና ማዕከል ሰሞኑን ተመርቆ ስራ ጀመረ፡፡
“ዋጋ የአይን ህክምና ማዕከል” በሀገራችን የአይን ህክምናን በላቀ ደረጃ በመስጠት ከሚታወቁ ጥቂት ማዕከላት አንዱ ነው ተብሏል፡፡ ቀደም ሲል ቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ በጣም በውስን በሆነ ቦታ ይሰጥ የነበረውን አገልግሎት በ2009 ዓ.ም ወሎ ሰፈር ጎርጎሪዎስ አደባባይ አካባቢ ራሱ ወዳስገነባው ባለ 10 ወለል ህንፃ ካዛወረ በኋላ የአይን ህክምናውን ከቀድሞው በላቀ ደረጃና ጥራት መስጠት መጀመሩን ባለፈው ሳምንት  በህክምና ማዕከሉ የቀዶ ጥገና ክፍሉ ምረቃ ላይ የማዕከሉ ሃላፊዎች  ተናግረዋል፡፡
የህክምና ማዕከሉ በተለይ የአይን ቀዶ ጥገና ህክምናን በላቀና በምቹ ሁኔታ ለመስጠት በማቀድ  ከባለ 10  ወለሉ ህንፃ 5ኛውን ወለል ለአይን ቀዶ ጥገና ህክምና ብቻ በማደራጀት በአንድ ጊዜ አራት ሀኪሞች ቀዶ ጥገና መስራት የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠሩን ገልጿል፡፡
ማዕከሉን ለማደራጀት በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂና ስመጥር የአይን ህክምና መሳሪዎችን ከሚያመርተውና ከሚያቀርበው የጃፓኑ “Topcon” ኩባንያ ጋር የስራ ግንኙነት በመፍጠር፣ እጅግ የረቀቁትን የዓይን ህክምና ቴክኖሎጂዎችን ማደራጀቱን ነው የዓይን ህክምና ማዕከሉ መስራችና  ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር መላኩ ጋሜ በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ የገለፁት፡፡
የአይን ህክምና ማእከሉ “ርህራሄ፣ ጥንቃቄ አክብሮትና ስነ-ምግባር ለታካሚዎች” በሚለው መርሁ፣ የህክምና አገልግሎት እንደሚሰጥ የተናገሩት ዋና ስራ አስፈጻሚው፣ ማዕከሉ ከአገር ውስጥ  ታካሚዎች በተጨማሪ የውጭ ታካሚዎችን በመቀበልና በማስተናገድ የውጪ ምንዛሬም እያስገኘ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ወደፊትም ለአይን ህክምና ወደ ውጪ የሚሄዱትን ግለሰቦች እዚሁ በማስቀረት ታካሚዎችን ከእንግልት አገርን ከውጪ ምንዛሬ ብክነት ለማዳን ራዕይ መሰነቁን ዋና ስራ አስፈጻሚው አስረድተዋል፡፡
ዋጋ የአይን ህክምና ማዕከል በአሁኑ ወቅት በቀን ከ400 እስከ 450 ለሚደርሱ ታካሚዎች  የህክምና አገልግሎት የመስጠት አቅም መፍጠሩ የተገለፀ ሲሆን የቀዶ ጥገና ህክምና ወረፋ የሚጠብቁ ታካሚዎችን ቀጠሮ በማሳጠርም የታካሚዎችን እርካታ ለመጨመር አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ አሟልቷል ተብሏል፡፡ ማዕከሉ  የምክር ፣ የምርመራ፣ የግላኮማ ህክምና፣ የሬቲናቪሮስስ፣የጨረር (ሌዘር) ህክምና የአይን ሞራ ግርዶሽ (ካታራክት) ቀዶ ጥገና፣ ከክብደት በታች የተወለዱ ጨቅላ ህፃናት የአይን ምርመራና ህክምና እንዲሁም  አስተኝቶ የማከም አገልግሎት እንደሚሰጥ ለማወቅ ተችሏል፡፡


Read 2536 times