Saturday, 01 September 2012 11:00

“የታማህበት ባንዲራ፣ ዝቅ ብሎ ያነባልሃል”

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(2 votes)

በ1919 ዓ.ም በቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ የተፃፈው የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር ለንጉሱ አክብሮቱን ገልፆ፣ አርበኞቹን አድንቆ፣ የአገሪቱ ነፃነት እንደማይደፈር አጽንኦት ሰጥቶ፣ ለዚህም የአገሪቱ መልክዓ ምድር አቀማመጥ ተራራው ሸንተረሩ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ አመልክቶ ሲያበቃ

ድል አድራጊው ንጉሣችን

ይኑርልን ለክብራችን፡፡ …ይላል፡፡

በ1968 ዓ.ም በአሰፋ ገብረማርያም በተፃፈው የደርግ ዘመን የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር ኢትዮጵያን አስቀድሞ፣ ኅብረሰብአዊነትን አስከትሎ፣ ስለ ጀግኖች፣ ወንዝና ተራሮች፣ ስለ ድንግል መሬት፣ ስለ አንድነትና ነፃነት፣ ስለ ጥበብ አንስቶ ሲያጠቃልል

የጀግኖች እናት ነሽ -  በልጆችሽ ኩሪ

ጠላቶችሽ ይጥፉ - ለዘላለም ኑሪ

በ1984 ዓ.ም በደረጀ መላኩ ተዘጋጅቶ አሁን በማገልገል ላይ ባለው የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር ውስጥ ዜግነት፣ ሕዝባዊነት፣ ሰላም፣ ፍትሕ፣ ነፃነትና ባህልን አንስቶ ሲቋጭ

እንጠብቅሻለን፣ አለብን አደራ

ኢትዮጵያችን ኩሪ፣ እኛም ባንቺ እንኩራ - ይላሉ፡፡

በቀዳሚው ሁለት መዝሙሮች ሰንደቅ ዓላማ ሲሰቀልና ሲወርድ የሚዘመሩ መዝሙሮችም አሉት፡፡ በእነዚህም መዝሙሮች ውስጥ የሥርዓቱን ፍላጎትና ዓላማ የሚያንፀባርቁ ስንኞች ይገኛሉ፡፡

ብሔራዊ መዝሙርና ሰንደቅ ዓላማ ጥብቅ ቁርኝት አላቸው፡፡ ወይም የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ በሚለው አንድነት ሊገለጽም ይችላል፡፡

ሁሉም መንግሥታት ባወጡት መዝሙር የሚነቀፉበት ነገር እንዳለው ሁሉ ሦስተኛውና በኢህአዴግ ዘመን የወጣው ብሔራዊ መዝሙርም የሰንደቅ ዓላማ መስቀያና ማውረጃ መዝሙርን ባለማካተቱ ተተችቶበት ነበር፡፡

በሌላ በኩል ኢህአዴግ መራሹ መንግሥት የሰንደቅ ዓላማ ቀን በአዋጅ ደንግጐ በማውጣት የተለየ ታሪክ መሥራት ችሏል፡፡ አዋጁ የወጣበት ሦስተኛ ዓመት ነሐሴ 22 ቀን 2004 ዓ.ም በያዝነው ሳምንት ነበር ያለፈው፡፡

ኢህአዴግና ሰንደቅ ዓላማ ብዙ ያነጋገረ ታሪክ እንደነበራቸው ይታወቃል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ህልፈትን ተከትሎ በገጣሚ ነቢይ መኮንን ተጽፎ ባለፈው ሳምንት በአዲስ አድማስ ጋዜጣ በወጣው ግጥም ውስጥ “የታማህበት ባንዲራ፣ ዝቅ ብሎ ያነባልሃል” የሚለው ስንኝ ያለፈውን ታሪክ ያመለክታል፡፡ በየትም አገር ቢሆን ሰንደቅ ዓላማ የሕዝቦችን ስሜትና ቀልብ የሚገዛ ትልቅ ጉዳይ ነው፡፡

ትንስንስ-ንስንስ፣ ንስንስ - ንስንስ

ስስ-የደስደስ-ስስ

ተውለብላቢ

የጠላት ዐይኖች ለብላቢ

***

ንፋስ የሚያጨዋውታት

የኔ ብሉዋት፡፡

አራት ማዕዘን ቅድ

ቅንጣት

ዘላለም-ዓለም-ውድ፡፡

***

ቀለማማ! - ቀለማማ!

ሥልሱዋን

አረንጉዋዴ - ብጫ - ቀይማ

የሕልውናችን ግርማ - ሞገስ ማማ፡፡

“ውስጠት” በሚል ርዕስ ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው በ1981 ዓ.ም ባሳተሙት የግጥም መጽሐፍ ውስጥ “ቀለም ድምቄ” በሚል ርዕስ ከተፃፈው ግጥም የተወሰዱ ስንኞች ናቸው - ከላይ የቀረቡት፡፡ ግጥሙን መቼ፣ ለምንና እንዴት እንደፃፉት ገጣሚው በመጽሐፋቸው ውስጥ መረጃ አላኖሩም፡፡ ሰንደቅ ዓላማ የብዙዎችን ትኩረት ስለሚስብ አንዱ ክስተት ግጥሙን እንዲጽፉ አነሳስቷቸዋል ብሎ መገመት ግን አይከብድም፡፡

የኪነጥበብ ባለሙያዎችን ስሜት ከሚያነሳሱ ርዕሰ ጉዳዮች መሐል አገር፣ ጀግንነት፣ ሰንደቅ ዓላማ፣ ፍቅር፣ ሰላም፣ ውልደትና ሞት፣ ክፋትና ደግነት ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ ይባላል፡፡

የባለሙያዎቹን ስሜት የሚያነሳሳ ክስተት ከተፈጠረ፤ በወቅቱ ባዩት ነገር ላይ ብቻ ሳይሆን መቶና ሺህ ዓመታት ወደ ኋላ ሄደው ቴአትር ሊያዘጋጁ፣ ግጥም ሊጽፉ፣ ሐውልት ሊቀርጹ፣ ስዕል ሊሰሩ፣ ልቦለድ ሊጽፉ ብዙም አይቸገሩም፡፡

ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን፤ በአቡነ ጴጥሮስ የተጋድሎ ታሪክ ላይ ግጥም የፃፈው ክስተቱ ካለፈ ከብዙ ዓመታት በኋላ ነው፡፡

“ህንደኬ” ቴአትር ለመድረክ የበቃው በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታትን ተሻግሮ መጥቶ ነው፡፡ የአፄ ቴዎድሮስ አገር ወዳድነት፣ ጀግንነት፣ የፍቅር ሕይወትና አሟሟት በመጽሐፍ፣ በግጥም፣ በድራማ፣ በስዕል (ያውም በተለያዩ ሰዎች) ተዘጋጅቶ የቀረበው፣ እየቀረበም ያለው ከመቶ ዓመት በኋላ ነው፡፡

በፀሐፊ ትዕዛዝ ማዕረግ የነገሥታትን ታሪክ ተከታትለው በመዘገብ የሚታወቁ ሰዎች ነበሩ - በቀድሞው ዘመን፡፡ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ደግሞ በጥቅል የአገር፣ የጀግንነት፣ የፍቅር፣ የሰላምና የመሳሰሉት ርዕሰ ጉዳዮችን ታሪክና ሂደት ተከታትለው ለትውልድ የሚያቀብሉ ፀሐፊ ትዕዛዞች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡

ይህንን እውነታ ቆየት ካሉት ሥራዎች ጋር ብቻ ሳይሆን ወቅታዊ ከሆኑ ጉዳዮች ጋር አያይዞ ማሳየት ይቻላል፡፡ በእንግሊዝ የተካሄደው 30ኛው የኦሎምፒክ ውድድር ለአገራችን ብቻ ሳይሆን ለብዙ የዓለም ሕዝቦች የደስታ ጊዜ ሆኖ አልፏል፡፡

በሴቶች የማራቶን ሩጫ አትሌት ቲኬ ገላና ያገኘችው ድል መነሳሳትን ፈጥሮላቸው ታሪኩን በሙያቸው መዝግብው ማስተላለፍ ከቻሉት አንዱ ነው ገጣሚው፡፡ ነሐሴ 5 ቀን 2004 ዓ.ም በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ከታተመው ግጥሙ ውስጥ ጀግኖች በኩራት ስለሚያውለበልቡት ሰንደቅ ዓላማ የተቋጠሩት ስንኞች እንዲህ ቀርበዋል፡-

ምን ምን ይል ይሆን ባንዲራ፣ ዓለም ፊት ሲከናነቡት?

ዕንባ ዕንባ ይላል ወርቅ ወርቅ፣ ምነው ቀምሼ ባወኩት?!

በሞቴ ንገሪኝ ቲኬ፣ ምን ምን ይላል ሲለብሱት?!

አየር ላይ ሲያውለበልቡት?

አስቀናሽኝ ለእኔ ወይኔ

ምሥጋና ይግባው ላንቺ ወኔ!

ባንዲራ ለሌለው መጥኔ!!

ገጣሚው፤ ሰንደቅ ዓላማን ለብሶ በዓለም አቀፉ አደባባይ ማውለብለብ ስለመታደል የተሰማውን የመደነቅ፣ የመገረምና የመደሰት ስሜቱን በግጥሙ ከገለፀ ከጥቂት ቀናት በኋላ ብዕሩን ለጽሑፍ የሚያነሳሳ ነገር ከሀዘን ጋር ሲመጣበትም የሰንደቅ ዓላማን ታሪክና ውለታ አመልክቷል፡

ያኔ አልበለው ዘመኑን፣ ጊዜ ባዳ ያስመስላል

እንዲህ ሞትጋ ልንጠጋ፣ ስንት የቀን - ጐደሎ አልፈናል

እንዲህ ማረፍህ ላይቀር፣ ስንቶች እረፍት ያዙልሃል

የታማህበት ባንዲራ፣ ዝቅ ብሎ ያነባልሃል!

ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሞት ጋር በተያያዘ ሰንደቅ ዓላማ ሀዘን ለመግለጽ፣ አንድነትን ለማሳየት፣ ሰላምና ተስፋን ለማመልከት … ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ “ጸጋዬ” በሚል ርዕስ በአስፋው ተፈራ ተዘጋጅቶ በ1978 ዓ.ም በታተመው የግጥም መጽሐፍ ውስጥ ስለ ሰንደቅ ዓላማ የተቋጠሩ ስንኞች፤ አገርና ሕዝብ መማርና ማወቅ ከፈለገ ባንዲራ በቀለማቱ ደምቆ ከመውለብለብ ባሻገር ብዙ ብዙ ይናገራል፤ ጆሮና ዓይን እንስጠው ይላሉ፡፡

አረንጓዴ ቢጫ፤ ቀይቱ ቀለማት

ትናገራለች፤ አገር ላይ ብንሰማት

ትናገራለች፤ ግብዞች ብንሰማት

ታነቃቃናለች፤ ብልሆች ብንሰማት፡፡

 

 

Read 52810 times Last modified on Saturday, 01 September 2012 11:05