Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 01 September 2012 11:19

ካንሰር ዝምተኛው ገዳይ በሽታ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በካንሰር ህመም ምክንያት ህይወቱን የሚያጣው ሰው ቁጥር በHIV ከሚሞተው በእጥፍ ይበልጣል

ከቅርብ አመታት በፊት የበለፀጉት አገራት ችግር እንደነበር የምናውቀው የካንሰር በሽታ ዛሬ ዛሬ የደሀ ሀገራትም አሳሳቢ ችግር ሆኗል፡፡  ይኸው በሽታ በዓለም ላይ ካሉትና የሰውን ልጅ ህይወት በማጥፋት ከሚታወቁት ዋና ዋና ገዳይ በሽታዎችም አንዱ ነው፡፡ ዓለም አቀፉ የካንሰር ድርጅት እ.ኤ.አ በ2007 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት መሠረት በዓለም በየዓመቱ 7 ሚሊዮን ህዝብ በካንሰር በሽታ ምክንያት ህይወቱን ያጣል፡፡ ወደ አስራ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋው ደግሞ በየዓመቱ በካንሰር ይያዛል፡፡ እንደ ሪፖርቱ ችግሩ በዚሁ ባለበት ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ እ.ኤ.አ በ2020 በካንሰር የሚሞተው ህዝብ ቁጥር 10 ሚሊዮን የሚደርስ ሲሆን በየዓመቱ በካንሰር የሚያዘው ሰው ቁጥር ደግሞ 16 ሚሊዮን ይደርሳል፡፡

የበለፀጉት አገራት የካንሰር በሽታን በመከላከሉና በመቆጣጠሩ ረገድ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው በመሥራታቸው ችግሩን ለመቆጣጠርና የበሽታውን መስፋፋት ለመቀነስ ችለዋል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ በታዳጊ አገራት ህክምናው በበቂና በተሟላ ሁኔታ ስለማይገኝና ለመከላከሉና ለመቆጣጠሩ ተግባር በርካታ ገንዘብ የሚጠይቅ በመሆኑ የካንሰር በሽታ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ ይገኛል፡፡ እንደ አለም አቀፉ የጤና ድርጅት (WHO) ጥናት በአሁኑ ወቅት በየዓመቱ በታዳጊ አገራት ውስጥ በካንሰር ህመም ምክንያት ህይወቱን የሚያጣው ሰው ብዛት በኤችአይቪ ኤድስ ከሚሞተው ሰው በእጥፍ ይበልጣል፡፡

ካንሰር ከሌሎች በሽታዎች የሚለይበት ሁኔታ ከቁጥጥር ውጪ በሆነ ሁኔታ በማደጉና ሴሎችን በመውረሩ ነው፡፡ ለካንሰር መነሻ ምክንያቱ በሰውነታችን ውስጥ ያሉ ሴሎች ባልተለመደ ሁኔታ መራባትና ማደግ ነው፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ሴሎች ከተፈጥሮአዊው መንገድ ውጪ ልንቆጣጠረው በማንችለው ሁኔታ እየተባዙ ይሄዳሉ፡፡ ይህ ሒደት በሣይንሳዊ አጠራሩ ሜታስታሲስ (metastasis) ተብሎ ይጠራል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በኬሚካል፣ በቫይረስ፣ በሲጋራ ማጨስ፣ በፀሐይ ብርሃንና በመሳሰሉ አካባቢያዊ ተጽዕኖዎች ምክንያት የሰውነታችን ሴሎች ሊጠቁና ሊጐዱ ይችላሉ፡፡ ይህም የሴሎቹን ትክክለኛ ሥራ የመቆጣጠር አቅም ያዳክማል ወይንም ጨርሶውኑ እንዳይኖር ያደርጋል፡፡ በዚህ ጊዜም የካንሰር ሴሎች ይፈጠራሉ፡፡ እነዚህን የካንሰር ሴሎች ዕድገት ለመቆጣጠር የሚችል DNA ስለሌላቸው ሴሎቹ ራሳቸውን ከቁጥጥር ውጪ በሆነ ሁኔታ በማብዛትና በደምና በሌሎች የሰውነታችን ፈሳሾች አማካኝነት በሰውነታችን ውስጥ እንዲሰራጩ በማድረግ በመጀመሪያ ሴሎቹ በተነሱበት አካባቢ ህመሞች እንዲፈጠሩ ያደርጋል፡፡ የካንሰር ህመም በሰውነታችን ውስጥ መከሰት የሚጀምረው ሴሎች ከቁጥር ውጪ በሆነ ሁኔታ ማደግ ሲጀምሩ ነው፡፡ በዚህ ወቅት የተፈጠሩት ሴሎች እያደጉና እየተባዙ ሲሄዱ ሌሎቹን ጤናማ ሴሎቹን በማስጨነቅ መደበኛ ሥራቸውን እንዳይሰሩ ያደርጓቸዋል፡፡ ህመሙ እያደገና እየተስፋፋ ሄዶ በመገጣጠሚያ አካላት፣ በነርቭ፣ በአንጀትና በውስጥ አካላት ላይ ተጽዕኖ ማሳደር ይጀምራል፡፡ በዚህ ወቅትም ህመምተኛው የተለያዩ ምልክቶችን ማሳየትና ክብደቱም መቀነስ ይጀምራል፡፡

የካንሰር በሽታ ስርጭትን በአልትራሳውንድ፣ በሲቲ ስካን፣ (MRI)፣ በኤክስሬይ እና ቦን ስካን በተባሉ የምርመራ ዘዴዎች ማወቅ ይቻላል፡፡ ህመሙ ካንሰር መሆን አለመሆኑ ለመለየት የሚረዳው ዘዴም የፓቶሎጂ ምርመራ እየተባለ ይጠራል፡፡ በካንሰር ህመም የተያዙ ሰዎች ታክሞ የመዳን ዕድላቸው እንደ ህመሙ ዓይነት፣ ሕመሙ የሚገኝበት ደረጃ፣ የታማሚው ሰው ዕድሜና ህክምናው በተሟላ ሁኔታ መስጠት አለመስጠቱ ላይ የተወሰነ ነው፡፡

ካንሰርን እንደማንኛውም ህመም ማዳን፣ መከላከልና መቆጣጠር ይቻላል፡፡ በቶሎ ከተደረሰበትና በቂ ህክምና ካገኘም ይድናል፡፡ ለካንሰር በሽታ ከሚሰጡ ህክምናዎች መካከል ቀዶ ህክምና፣ የጨረር ህክምና፣ ኬሞቴራፒ፣ የሆርሞን ቴራፒና፣ ባዮሎጂካል ቴራፒ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ለካንሰር ህሙማን የሚሰጠው የቀዶ ህክምና ካንሰሩን በቀዶ ህክምና ዘዴ አውጥቶ በካንሰር በሽታ የተያዘውን ሴል የማስወገድ ዘዴ ነው፡፡

የጨረር ህክምና የምንለው ደግሞ ከፍተኛ ኃይል ያለውን ጨረር በመጠቀም የካንሰር ሴሎችን የመግደል ህክምና ነው፡፡ ኬሞቴራፒ የምንለው የህክምና ዘዴ ደግሞ ብዛት ያላቸውን የካንሰር መድሃኒቶች በአንድ ጊዜ በመጠቀም በሰውነት ውስጥ የሚገኙ የካንሰር ሴሎችን ለመግደል የሚሰጥ የህክምና ዘዴ ነው፡፡ በዚህ የህክምና ሂደት ውስጥ ጤነኛ የሆኑ ሴሎች አብረው የሚሞቱበት ሁኔታ አለ፡፡ ሆርሞንቴራፒ የምንለው በሆርሞን ላይ ጥገኛ የሆኑ የካንሰር ህመም አይነቶችን ለማከም የምንጠቀምበት ዘዴ ነው፡፡ እነዚህ ህክምናዎች ግን በአገራችን እንደ ልብና በስፋት ሊገኙ የሚችሉ የህክምና አይነቶች አይደሉም፡፡ በካንሰር ህመም የተያዘ ሰው ከሚያሳያቸው ምልክቶች መካከል ከፍተኛ የክብደት መቀነስ፣ በሰውነት ላይ አዳዲስ ነጠብጣብ መታየት፣ በአንጀትና በኩላሊት ላይ የህመም ስሜት መቀስቀስ ተከታታይና ደረቅ ሣል ማሳል፣ በጡት (በሰውነት ክፍሎች) ላይ ጠጠር ያለ ወይም ላላ ያለ እብጠት መከሰት፣ በቶሎ የማይድን የጉሮሮ ህመም መከሰት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ከዚህ ለወራት ብሎም ለዓመታት በዝምታ ቆይቶ ህይወትን ከሚያሳጣ ገዳይ በሽታ ለመጠበቅ ሁላችንም ለራሳችን ትኩረት ማድረግና በሰውነታችን ላይ የሚታዩ ለውጦችን በማስተዋል ወደ ህክምና ተቋማት መሄድ ዐቢይ ጉዳይ ነው፡፡

 

 

Read 10559 times Last modified on Saturday, 01 September 2012 11:29