Saturday, 12 June 2021 00:00

የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ህብረት ለምርጫ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የመራጮች ምዝገባ ትዝብት ግኝት መግለጫ


           በቅርቡ የሚከናወነው 6ኛው አገራዊ ምርጫ በ2010 ዓ.ም የተጀመረው የፖለቲካ ለውጥ ስር እንዲሰድ እንዲሁም በሀገራችን ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት ወሳኝ እርምጃ ነው። የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ህብረት ለምርጫ፣ ከአባል ድርጅቶቹ የተውጣጡ ታዛቢዎች መልምሎ በማሰልጠንና የምርጫ ሂደቱ አካታች፣ ግልፅ እንዲሁም ተዓማኒነት ያለው መሆኑን እንዲታዘቡ በማድረግ ለመጪው ምርጫ የበኩሉን አስተዋፅኦ በማድረግ ላይ ይገኛል። የምርጫ ትዝብት ዓላማ በምርጫ ሂደት ለዜጎች፣ ለዕጩ ተወዳዳሪዎች፣ ለሚዲያ ተቋማትና ጋዜጠኞች፣ ለምርጫ አስፈጻሚዎች፣ ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና ለተለያዩ የመንግስት አካላት ከፓርቲ ወገንተኝነት ነፃ የሆነን መረጃ የማሰባሰብና የማቅረብ ሲሆን ይህን መረጃ መሰረት በማድረግ እያንዳንዱ ባለድርሻ አካል የምርጫውን አካታችነት፣ ግልጽነትና ተዓማኒነት እንዲገመግም ያስችላል።
ህብረቱ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከመጋቢት 16 ቀን 2013 ዓ.ም እስከ ግንቦት 6 ቀን 2013 ዓ.ም (በአንዳንድ አካባቢዎች እስከ ግንቦት 13 ቀን 2013 ዓ.ም) ድረስ የመራጮች ምዝገባን ባከናወነባቸው ሥፍራዎች ታዛቢዎችን አሰማርቶ ሂደቱን ሲታዘብ ቆይቷል። የመራጮች ምዝገባን ለመታዘብ ከሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ 144 ታዛቢዎችን ከአባል ድርጅቶቹ በመመልመል የምዝገባ ሂደቱ ላይ የጐላ ተፅዕኖ ሊያሳርፉ የሚችሉ አሳሳቢ ኩነቶችን ጨምሮ ህብረቱ ባዘጋጃቸው የመራጮች ምዝገባ ሂደትን የሚገመግሙ ልዩ ልዩ መጠይቆች ላይ በመመርኮዝ፣ ከመራጮች ምዝገባ ሂደት ጋር የተያያዙ መረጃዎችን እንዴት እንደሚሰበስቡ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል። ሆኖም በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት በተወሰኑ አካባቢዎች የመራጮች ምዝገባ በተያዘለት ጊዜ አለመጀመሩ ወይም በጭራሽ አለመከናወኑ፤ እንዲሁም ቦርዱ ለታዛቢዎች የሚሰጠው የእውቅና ፈቃድ (ባጅ) በመዘግየቱ ሳቢያ ህብረቱ ካሰለጠናቸው ታዛቢዎቹ መካከል ማሰማራት የቻለው 117ቱን ብቻ ነው። የህብረቱ ታዛቢዎች መታዘብ በቻሉባቸው ሥፍራዎች ሁሉ የመራጮች ምዝገባ ጣቢያዎችን በተመረጡ ቀናት ውስጥ ከመራጮች ምዝገባ መክፈቻ ሰዓት አንስቶ እስከ መዝጊያ ሰዓት ድረስ ታዝበዋል። በዚህ መግለጫ ላይ የቀረቡት መረጃዎች የህብረቱ ታዛቢዎች ከሚያዝያ 2 ቀን እስከ  ግንቦት 13 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተዘዋውረው በጎበኟቸው 1,190 የምርጫ ምዝገባ ጣቢያዎች ላይ የተመሰረተ ነው።
የህብረቱ የመራጮች ምዝገባ ሂደት ትዝብት ግኝቶች
ህብረቱ ከአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር የመራጮች ምዝገባን ማካሄድ ለኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ከባድ የቤት ሥራ እንደነበር እንደሚገነዘብ አስቀድሞ ሊገልፅ ይወዳል። የመራጮች ምዝገባ ምንም እንኳን ዘግይቶ መጋቢት 16 ቀን 2013 ዓ.ም ቢጀመርም፣ በፀጥታ ችግሮች እንዲሁም ከምርጫ አስፈፃሚዎች በቀረቡ የተለያዩ ቅሬታዎች ምክንያት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተደጋጋሚ ተቋርጦ የነበረ ሲሆን በአንዳንድ ቦታዎች በጭራሽ አልተካሄደም ነበር። ነገር ግን የመራጮች ምዝገባ ጣቢያዎች ከተከፈቱና ምዝገባው ከተጀመረ በኋላ የህብረቱ ታዛቢዎች በታዘቧቸው 1,192 ጣቢያዎች የተሰበሰበው መረጃ ምዝገባው ቦርዱ ያወጣቸውን ህግጋት ከሞላ ጐደል የተከተለ እንደነበር ያሳያል።

የምርጫ ጣቢያዎች አወቃቀርና ተደራሽነት
የምርጫ ምዝገባ ጣቢያዎች ሊከፈቱ የሚገባው መራጮች በቀላሉ ተጉዘው ሊያገኟቸው በሚችሏቸው ሥፍራዎች እንደሆነ ይታወቃል። ይህ የዜጎችን የመምረጥ መብት ከማረጋገጥ አንፃር ወሳኝ ሚና ይጫወታል። ህብረቱ በታዛቢዎቹ አማካኝነት የሰበሰበው መረጃ እንደሚያሳየው 96 በመቶ የሚሆኑት የመራጮች ምዝገባ ጣቢያዎች (ማለትም ከ1,192 ጣቢያዎች ውስጥ 1,147) መራጮች በቀላሉ ተጉዘው ሊያገኟቸው በሚችሉበት ርቀት ላይ የተከፈቱ ነበሩ። ህብረቱ ከታዘባቸው 1,192 የምዝገባ ጣቢያዎች መካከል በአማካይ 9 በመቶ ያህሉ ለመጓዝ ለሴቶች ይበልጥ አስቸጋሪ ሲሆን ይህ ቁጥር በገጠር በሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች 12 በመቶ እንዲሁም በከተማ በሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች 6 በመቶ ያህል ነው። በተጨማሪም ታዛቢዎች ከጎበኟቸው ጣቢያዎች 12 በመቶ ያህሉ ለአካል ጉዳተኞች ወይም ለመንቀሳቀስ እርዳታ ለሚያሻቸው ዜጎች (አዛውንቶች፣ ጨቅላ ህፃናትን የያዙ እናቶች፣ ነፍሰ ጡር እናቶች፣ ወዘተ..) ያለረዳት ገብተው መስተናገድ የማይችሉባቸው ነበሩ።
በአብዛኛው የመራጮች ምዝገባ የምርጫ ህጉ በሚፈቅዳቸው ቦታዎች የተከናወነ ሲሆን፤ የህብረቱ ታዛቢዎች በ45 ቦታዎች የምርጫ ቦርድ በህግ በከለከላቸው ቦታዎች ማለትም በፖሊስ ጣቢያ፣ በግል መኖርያ ቤት፣ የፖለቲካ ፓርቲ ፅ/ቤት በሚገኝበት ህንፃ፣ በጦር ካምፕ ውስጥ ምዝገባ እንደተካሄደ ሪፖርት አድርገዋል። ምንም እንኳን የምርጫ ቦርዱ ምዝገባ የሚካሄድባቸው ሥፍራዎች ዜጎች ከዝናብና ፀሀይ የሚከላከል ጥላ ባለበት ሥፍራ መሆን እንዳለበት ቢደነግግም፣ ህብረቱ ከታዘባቸው የምዝገባ ጣቢያዎች 57 በመቶ ያህሉ የምዝገባ ጣቢያዎች ምንም አይነት ከዝናብ ወይም ከፀሀይ ዜጎችን የሚከላከል ጥላ አልነበራቸውም።
በምርጫ ቦርድ የመራጮች ምዝገባ አፈፃጸም መመሪያ ቁጥር 06/2013 መሠረት፤ አንድ የምርጫ ጣቢያ ቢያንስ ሶስት የምርጫ አስፈፃሚዎች ሊኖሩት እንደሚገባ ተደንግጓል። ይህን በተከተለ መልኩ ህብረቱ ከታዘባቸው ጣቢያዎች በ71 በመቶ ያህሉ ቢያንስ ሶስት አስፈፃሚዎች መኖራቸው አበረታች ምልከታ ነው። በተጨማሪ ታዛቢዎች በጎበኟቸው አብዛኞቹ ጣቢያዎች የምርጫ ምዝገባ ቁሳቁሶች በአብዛኛው ተሟልተው ነበር። ነገር ግን በ40 የምርጫ ጣቢያዎች በጣት ላይ የሚቀባ ቀለም እንዳልነበረ ታዛቢዎች ሪፖርት ያደረጉ ሲሆን ይህ በድምጽ መስጫ ዕለት ሊፈጠር የሚችልን በተደጋጋሚ የመምረጥ ስጋት ለማስቀረት ከሚኖረው ሚና አንፃር ሊታሰብበት እንደሚገባ ህብረቱ ያምናል። በተጨማሪም የህብረቱ ታዛቢዎች ከታዘቧቸው ጣቢያዎች ውስጥ በ16ቱ ምዝገባ ጣቢያዎች መዝገብ (Polling Station Journal) እንዳልነበረ ሪፖርት ያደረጉ ሲሆን በ12 ጣቢያዎች ደግሞ የምስክርነት ቅፅ (Testimony Form) እንዳልነበር ሪፖርት ተደርጓል።
አካታችነት  
የአንድን የምርጫ ሂደት ፍትሀዊነትና ተዓማኒነት ለመመዘን በምርጫ ሂደቱ ውስጥ የሴቶችን፣ የወጣቶችንና የአካል ጉዳተኞችን ተሳታፊነት ማረጋገጥ አንዱና ዋነኛው መለኪያ ነው። የህብረቱ ታዛቢዎች ከታዘቧቸው 1,192 የምዝገባ ጣቢያዎች በ928ቱ ማለትም 77 በመቶ ከነበሩት የምርጫ አስፈፃሚዎች ቢያንስ አንዷ ሴት የነበረች ሲሆን፣ አብዛኞቹ የምርጫ አስፈፃሚዎችም በወጣትነት የእድሜ ክልል የሚገኙ ነበሩ። ምንም እንኳን ይህ የሚበረታታ ቢሆንም፣ 23 በመቶ ያህሉ የምዝገባ ጣቢያዎች ሁሉም የጣቢያው ሠራተኞች ወንዶች ነበሩ። የአካል ጉዳተኞች በምርጫ አስፈጻሚነት የተሳተፉበት በ5 በመቶ ጣቢያዎች ብቻ ነበር። ይህም ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነጥብ እንደሆነ ህብረቱ ያምናል።
ደህንነት
ህብረቱ ካሰማራቸው ታዛቢዎች መካከል የመራጮች ምዝገባ በተደረገባቸው የመራጮች  ምዝገባ ጣቢያዎች ወይም አቅራቢያ የተከሰቱ የፀጥታ ችግሮችን ሪፖርት ያደረጉት በጣም ጥቂቶች (3 በመቶ ያህሉ) ቢሆኑም፣ በአገሪቱ ውስጥ የፀጥታ ችግር በተከሰተባቸው አካባቢዎች የመራጮች ምዝገባ በከፊል ወይም በጭራሽ አለመካሄዱ ለቁጥሩ ዝቅተኛ መሆን አስተዋፅኦ ሊኖረው እንደሚችል መገንዘብ ያስፈልጋል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ የሚገኙት የመተከል እና ካማሺ ዞኖች እንዲሁም በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ አንዳንድ የጸጥታ ችግር ያለባቸው አካባቢዎች ለዚህ እንደማሳያነት ሊጠቀሱ ይችላሉ። በተጨማሪም የምርጫ ቦርድ ባወጣው መመሪያ መሠረት የመራጮች ምዝገባ በሚከናወንበት እያንዳንዱ ሥፍራ ቢያንስ አንድ የፀጥታ አካል ሊገኝ እንደሚገባው ቢደነግግም፣ የህብረቱ ታዛቢዎች ከታዘቧቸው የመራጮች ምዝገባ ጣቢያዎች መካከል 61 በመቶ ላይ ምንም ዓይነት የፀጥታ አካላት እንዳልተገኙ የተሰበሰበው መረጃ ያሳያል። በሌላ በኩል የፀጥታ ሀይሎች በተገኙባቸው ቦታዎች በአብዛኛው ሳይጋበዙ ወደ ምርጫ ጣቢያው አለመግባታቸው አበረታች ነው። ነገር ግን በ31 አጋጣሚዎች  የፀጥታ ሀይሎች ያለምርጫ አስፈፃሚዎች ፈቃድ ወደ ጣቢያዎች መግባታቸውን ታዛቢዎች  ሪፖርት አድርገዋል።
የመራጮች ምዝገባ ህግጋትንና ሥነ ሥርዓቶችን ማክበር
ምዝገባ በተካሄደባቸውና የህብረቱ ታዛቢዎች በተመለከቷቸው የምርጫ ጣቢያዎች በአብዛኛው የምርጫ አስፈፃሚዎች የምርጫ ቦርድን የመራጮች ምዝገባ የአሰራር ህጎች የተከተሉ እንደነበሩ መረጃዎች ያሳያሉ። ታዛቢዎች ከተመለከቷቸው የምዝገባ ጣቢያዎች ቢያንስ በ96 በመቶ ያህሉ በታዛቢዎች፣ ፓርቲ ተወካዮች ወይም ጋዜጠኞች ላይ ምንም አይነት ገደብ ያልተጣለ ሲሆን ይህም አበረታች ምልክት ነው። በመራጭነት ከተመዘገቡ ዜጐች መካከል የ99 በመቶ ያህሉ ተመዝጋቢዎች መረጃ በመራጮች መዝገብ ላይ በአግባቡ የሰፈረ ሲሆን የመራጭነት ካርድ መቀበላቸውንም ታዛቢዎች አረጋግጠዋል። ይህም ምልከታ መልካም እንደሆነ ህብረቱ ቢያምንም፣ አንዳንድ ችግሮች እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል። ለምሳሌ ያህል ታዛቢዎቻችን በተመለከቷቸው ጣቢያዎች ቢያንስ 3 በመቶ ያህሉ ማንነታቸውንና አድራሻቸውን አረጋግጠው እንዲመዘገቡ ያልተፈቀደላቸው ሲሆን ህብረቱ ከታዘባቸው ጣቢያዎች 8 በመቶ ያህል በሚሆኑት ከመዝጊያ ሰዓት በፊት በሰልፍ ላይ የነበሩ ዜጎች ሳይመዘገቡ ጣቢያዎቹ መዘጋታቸው አሳሳቢ ጉዳይ ሆኖ አግኝቶታል። በተጨማሪም ምንም እንኳን የህብረቱ ታዛቢዎች ከ90 በመቶ በላይ በሚሆኑት ጣቢያዎች ከጠዋት እስከ ማታ እንዲታዘቡ ቢፈቀድላቸውም፣ በ6 በመቶ ያህሉ ግን በህግ በተፈቀደው መሰረት የመራጮች መዝገብ ላይ የሰፈሩ መረጃዎችን ማየት አልተፈቀደላቸውም።
የመራጮች ምዝገባና የኮቪድ-19 ወረርሺኝ
6ኛው አገራዊ ምርጫ የሚካሄደው የኮቪድ-19 ወረርሺኝ እየተስፋፋ በሚገኝበት ወቅት ላይ እንደመሆኑ ህብረቱ በመራጮች ምዝገባ ወቅት አተኩሮ ከታዘባቸው ጉዳዮች መካከል ቫይረሱን ለመከላከል የተደረጉ ጥረቶችና አፈፃፀማቸው አንዱ ነው። የሚከተሉት በመራጮች ምዝገባ ወቅት ህብረቱ ኮቪድ-19ን በተመለከተ ከሰበሰባቸው ግኝቶች መካከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
- የፊት መሸፈኛ ጭንብሎች (face masks) እና የእጅ ማጽጃዎች (sanitizers) አቅርቦት በአብዛኞቹ የምዝገባ ጣቢያዎች መሟላቱ ተስፋ ሰጪ ቢሆንም፣ 52 በመቶ ያህል በሚሆኑ የመራጮች የምዝገባ ጣቢያዎች የእጅ መታጠቢያ ቦታዎች አልነበሯቸውም፤
- 60 በመቶ የሚሆኑ ህብረቱ የታዘባቸው የምዝገባ አስፈፃሚዎች የእጅ ጓንቶች (Gloves) አልነበሯቸውም፤
- ህብረቱ ከጎበኛቸው ጣቢያዎች መካከል 13 በመቶ በሚሆኑት ጣቢያዎች የምርጫ አስፈፃሚዎች የፊት ጭምብሎችን ያላደረጉ ሲሆን፤ 28 በመቶ የሚሆኑ የምርጫ አስፈፃሚዎች በአንፃሩ በምዝገባ ወቅት የፊት ጭምብሎችን ያደረጉ ነበሩ፡፡
- ህብረቱ ከጎበኛቸው ጣቢያዎች 23 በመቶ በሚሆኑት የምዝገባ ቦታዎች ዜጎች የፊት ጭምብሎችን ያላደረጉ ሲሆኑ 48 በመቶ በሚሆኑት ጣቢያዎች መራጮች የፊት ጭምብሎችን ያደረጉት በከፊል ብቻ መሆኑ ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ነው።
- ከላይ እንደሚታየው በምዝገባው ወቅት ከቫይረሱ ጋር የተያያዙ የተለያዩ የጥንቃቄ ክፍተቶች ያሉ ሲሆን 89 በመቶ ያህል በሚሆኑት የምርጫ ጣቢያዎች የኮቪድ-19 ባለሙያዎች አለመገኘታቸው ለሚታዩት ክፍተቶች ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደነበረው ታይቷል።
ምክረ ሀሳቦች
ከላይ በተጠቀሱት ቅድመ-ግኝቶች ላይ በመመስረት፣ የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ህብረት ለምርጫ፤ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ከሚካሄደው ምርጫ አስቀድሞ ከላይ የተጠቀሱትን ክፍተቶች ለማስተካከል ይረዳ ዘንድ የሚከተሉትን ምክረ ሀሳቦች አስቀምጧል፡-
- ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን የሚያካሂደው በዝናባማው የአገሪቱ ወቅት እንደመሆኑ፤ በምርጫ ቀን በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች ድምፃቸውን ለመስጠት ለሚመጡ ዜጎች ከፀሀይና ከዝናብ የሚከላከል ጥላ መዘጋጀቱን ሊያረጋግጥ ይገባል።
- ቦርዱ በምርጫ ቀን ለሂደቱ የሚያስፈልጉ እንደ ጣት ቀለም የመሳሰሉ ቁሳቁሶች በሁሉም ጣቢያዎች መሟላታቸውን ማረጋገጥ አለበት።
- ከምርጫ ጣቢያዎች የመዝጊያ ሰዓት ጋር በተያያዘ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ በምርጫ ቀን ከመዝጊያ ሰዓት በፊት በጣቢያው ተገኝተው ለተሰለፉ ዜጎች የመምረጥ ዕድል አለመነፈጉን ሊያረጋግጥ ይገባል። ቦርዱ አስፈፃሚዎችን በሚያሰለጥንበት ወቅት አስፈፃሚዎች በዚህ ረገድ በቂ ግንዛቤ መያዛቸውን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል።
- ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሚመለከታቸው የፌዴራል፣ የክልልና የከተማ አሰተዳደሮች የፀጥታ ሃይሎች ጋር በመወያየትና በመተባበር በምርጫ ቀን በሁሉም ጣቢያዎች በህግ በተደነገገው መሰረት የፀጥታ አስከባሪ አካላት እንደሚገኙ ሊያረጋግጥ ይገባል። በተጨማሪም የፀጥታ ሀይሎች በምርጫ ጣቢያዎች በሚገኙበት ወቅት ከቦርዱ የሚሰጣቸውን መመርያዎች በማክበር ሊሰሩ እንደሚገባ ህብረቱ ሊያስታውስ ይወዳል።
- የዜጎችን ጤና ከማስጠበቅ አንፃር ቦርዱ በድምፅ መስጫ ዕለት በሁሉም ጣቢያዎች የኮቪድ ባለሙያዎች እንዲገኙ አተኩሮ ሊሰራ ይገባል። በተጨማሪም ህብረቱ፤ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የጤና ሚኒስቴር እንዲሁም በመራጮች ትምህርት ላይ የተሰማሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ በቀረው አጭር ጊዜ ውስጥ በቫይረሱ ዙርያ ለዜጎች በቂ ግንዛቤ ሊሰጡ ይገባል ብሎ ያምናል።
መደምደምያ
ህብረቱ፤ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በተለያዩ ውጫዊ ተግዳሮቶች መሀል የመራጮች ምዝገባን በአገሪቱ የተለያዩ ስፍራዎች ማካሄድ መቻሉን ያደንቃል። ከ45,000 በላይ የመራጮች ምዝገባ ጣቢያዎችን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከመክፈት አንስቶ ወደ 135,000 የሚጠጉ አስፈፃሚዎችን አሰልጥኖ እስከማሰማራት ድረስ ቦርዱ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሰራው ስራ በመልካም ጐኑ የሚጠቀስ ነው። ምንም እንኳን የመራጮች ምዝገባን የማደራጀትና የማካሄድ ተግባርን ውስብስብነት ህብረቱ ቢረዳም፣ በምዝገባ ሂደቱ ወቅት የበርካታ ኢትዮጵያውያንን የመምረጥ መብት ሊያጣብቡ የሚችሉ ችግሮች መከሰታቸውን መካድ ግን አይቻልም። ከእነዚህ ችግሮች መካከል በአንዳንድ ስፍራዎች የነበረው የምዝገባ ጅማሮ መዘግየት ወይም በጭራሽ አለመካሄድ አንዱ ሲሆን የምዝገባ ቀናት በተራዘመባቸውም ሆነ ምዝገባ ዘግይቶ በተጀመረባቸው ስፍራዎች ስለ ምዝገባው በቂ መረጃ አለመሰጠቱ አሳሳቢ ነው፡፡ ህብረቱ ከላይ የጠቀሳቸው ግኝቶች እንዲሁም ያስቀመጣቸው የመፍትሄ ሀሳቦች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በትኩረት እንደሚታዩ ተስፋ እያደረገ፣ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ሊካሄድ ቀን በተቆረጠለት ምርጫ ላይ ሁሉም የተመዘገቡ ዜጎች መምረጥ እንዲችሉ ተግቶ ሊሰራ እንደሚገባ ያሳስባል።
(የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ህብረት ለምርጫ (CECOE)፤ ከ175 በላይ በምርጫ ዙርያ የተለያዩ ስራዎችን የሚሰሩ አገር በቀል የሲቪል ማህበራት ስብስብ ነው።)

Read 1198 times