Print this page
Saturday, 19 June 2021 16:59

“ያንተ ቤት ሲንኳኳ ይሰማል እኔ ቤት!”

Written by 
Rate this item
(7 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አያ ጅቦ አራት ልጆቹን፤ ማለትም - መዝሩጥን፣ ማንሾሊላን፣ ድብልብልን እና ጣፊጦን ይዞ በለሊት መንገድ ይሄዳል፡፡ እየተጓዙ ሳለ ድንገት አንዲት ከቤቷ የወጣች አህያ ያገኛሉ፡፡ ይሄኔ አባት ጅብ፤
 “ልጆቼ ሆይ! እንግዲህ እኔ በጣም አርጅቻለሁና ይቺን አህያ እኔ ነኝ የምበላት! እናንተ ራቅ ራቅ ብላችሁ ትጠብቁኛላችሁ” አለ፡፡
ይሄኔ መዝሩጥ፤ “አባዬ ኧረ አንድ ብልት እንኳን አጋራን?” ይለዋል፡፡
 “አይሆንም! ምንም አላቀምስህም” ይላል ጅቦ፡፡
 ይሄኔ ማንሾላ ይነሳና፤ “ለእኔስ አባቴ?” ይላል፡፡
 አያ ጅቦም፤ “እንካ ጆሮዋን ብላው” ይለዋል፡፡
ቀጥሎ ድብልብል ይመጣና፤ “ለእኔስ አባቴ?” ይለዋል፡፡
“አንተ ሽሆና ይደርስሃል” ይላል አያ ጅቦ፡፡
ቀጠለና ጣፊጦ ጠየቀ፡- “አባዬ የእኔንስ ነገር ምን አሰብክ?” አለ፡፡
 “አንተ ቆዳዋን ካገኘህ ያጠግብሃል” አለ፡፡
ልጆቹ አባታቸው አህያዋን ዘርጥጦ ጥሎ ሲበላ ዘወር አሉ፡፡ አያ ጅቦ ዋና ዋናውን የአህያዋን ብልት እንደበላ፤ ድንገት የአህያዋ ጌታ ሲሮጥ መጣ፡፡ አያ ጅቦ ፈርጥጦ መውጫ የሌለው የጫካ ጥግ ውስጥ ገብቶ ይሰረነቅና እየጮኸ ልጆቹን ይጠራል፡፡ ልጆቹ ቀርበው ወደ ጫካው ይጠጉና፤ “አባታችን ምነው ትጮሃለህ?” ሲሉ ይጠይቁታል፡፡
አያ ጅቦም፤ “አድነን ልጄ መዝሩጥ?” ይላል፡፡
 መዝሩጥም፤ “አባቴ ምን ሰጥተኸኛል እንደበላህ እሩጥ!”
#ልጄ ማንሾለላ!” ይላል አያ ጅቦ፡፡
 “ምን ሰጥተኸኛል ካንድ ጆሮ ሌላ!?” ይለዋል ማንሾለላ፡፡
“አድነኝ ልጄ ድብልብል?”
 “አይ አባት! ሸሆና ለማን ውለታ ይሆናል?!”
 ቀጥሎ አያ ጅቦ ጣፊጦን ጠየቀ፤ “አድነኝ ልጄ ጣፊጦ?!”
“ማን የጎረሰውን ማን አላምጦ?” አለ ጣፊጦ፡፡
መላወሻም አጋዥም ያጣው አያ ጅቦ፤ እዚያው ተወጋና ሞተ፡፡
 * * *
 ዛሬ እኔ ነኝ ዋናው ጅብ ማለት አይሠራም! ቀድመው ያላሰቡበት ግለኝነትና ሆዳምነት ምን ላይ እንደሚጥለን አለማሰብ፣ የማታ ማታ ያላጋዥ ያለመጠጊያ ያስቀራል፡፡ ከካፒታሊዝም ምርኮኛነታችን ጀምሮ ስግብግብነት፣ በዝባዥነት፣ ዘረፋና ግፍ ይበረክታል፡፡ ያላየነው የገንዘብ ትርፍ ማህበራዊ መልካችንን ያዥጎረጉረዋል፡፡ እንኳን ሊያተርፈን ራሳችንን ያጎልብናል፡፡ “አድነኝ ልጄ እገሌ?” ቢባል ምላሽ አይኖረውም፡፡ ዛሬ ከመቼውም ጊዜ በላይ እርስ በርስ መግባባትና መስማማት ያለብን ሰዓት ነው፡ ፡ ስለ ምርጫ መግባባታችን፣ ስለ ሃይማኖት መግባባታችን፣ ስለ አንድነት መግባባታችን፣ ስለ ድንበር ጉዳይ መግባባታችን፤ ስለ ውሃ ፖለቲካ መግባባታችን፣ ስለ ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴዎች መግባባታችን፤ ስለ ዓለም ዲፕሎማሲ መግባባታችን… ስለ ሃያላኑ ፉክክር መግባባታችን፣ ብርቱ ጥረት ማድረግን የሚጠይቅ ዘመን ነው፡፡ የሳሱ ድንበሮችና መንግስት አልባ አገራት ወደ አሰቃቂ እልቂት ሊያመሩ እንደሚችሉ፤ ሶማሊያም፣ የመንም፣ ሊቢያም፣ ኢራቅም ሶሪያም  ለመነሻ አስረጅነት የቆሙ ተጨባጭ ምሳሌዎቻችን ናቸው! ነገ በየአገሩ ይሄው ሁኔታ ላለመከሰቱ ምንም አስተማማኝ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህልውና የለም፡፡ በትናንሽ የፖለቲካ አታካራ ተሞልተን፣ ትናንሽ ሙሾ በማውረድ ጊዜያችንን ከምናባክን፣ ትልቁን የዓለም አቀፍም አገር አቀፍም ስዕል (The Bigger Picture) የምናይበትን ዐይናችንን እንክፈት፡፡
 ምዕራባውያን፤ ባህል፣ ሃይማኖትና ጥናታዊ ታሪክ ያላቸውን አገሮች ኢራቅ፣ ኢራን፣ ሶርያ፣ የመን፣ ግብፅ፣ ህንድ፣ ጃፓን፣ ቻይና … አሁን ደግሞ የእኛው አገር ኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠሩት ያለ ነገር አይደለም፡፡ ግሎባላይዜሽንን ይነቅፋሉ የሚለው አጀንዳ የዋዛ አይደለም፡፡ ባህል የሌላቸው ባለ ባህሎቹን እየገደሉ ነው፡፡ የቅርቦቹ ሶማሊያና ሊቢያ በመንግሥት-አልባ ሁኔታ ውስጥ መሆን፣ በማንም ይሁን በማን ለመጠቃታቸው ሰፊ በር ከፍቷል፡፡ ወደ ሊቢያ በጣሊያን አዛዥነት ስለዘመተው ያለዕዳው ዘማች የኤርትራ ወጣት (ደራሲው አበሻ ይለዋል) እንዲህ የሚል ሀሳብ ይገኝበታል፡፡ ስለ ሊቢያ በረሀ ነው፡- “የመሸበር ስሜት፣ ሐዘን፣ ተስፋ ቢስነት እና ፀፀት ፊታቸው ላይ ይነበባል፡፡ የበረሀው ስዕል አሰቃቂ ነው፡፡ አንዲት ዛፍ አትታይም፡፡ አንዲትም የሳር አገዳ የለችም፡፡ የውሃ ነገርማ ባይነሳ ይሻለዋል፡፡ ወደየትም አቅጣጫ መንቀሳቀስ አይታሰብም፡፡ ግራ፣ ቀኝ፣ ወደ ፊት፣ ወደ ኋላ፣ ወደ የትም መሄድ አይቻልም፤ ምክንያቱም የትም ይሁን የት ህይወት በአሸዋ ተከባ ነው የምትገኘው፡፡ በየትም ቢዞሩ ጠጠር ኮረት ድንጋይ፣ እና የአቧራ ክምር! ያ በረሀ እንደ ባህር ሰፊ፣ ግን በጥላቻ የተሞላ! ባህሩ ውስጥ ቢያንስ ዓሣ ማየትና የማዕበል ድምፅ ማዳመጥ ይቻላል፡፡ እዚህ ሊቢያ በረሃ ግን አንዲትም ወፍ አትዘምርም፡፡ አትበርምም፡፡ ያ ክፍቱ ደመና አልባ ሰማይ የጋለ ምድጃ ነው፡፡ በዚያ ጠራራ ንደድ ውስጥ ያለ ሰው፣ ያ መሬት፣ የህይወት ይሁን የሞት መለየት ይሳነዋል፡፡ ይሄን መሬት ከአረንጓዴው፣ ከንፋሳማው እና ከለሙ የኢትዮጵያ ምድር ጋር ማነፃፀር ከንቱ ድካም ነው! የሲዖልና የገነት ነው ልዩነቱ!?”
ስለ አበሻ የጦርነት ብቃት የሚገርም ትንተናም አለው - በሊቢያ በረሐ፡- አበሻ፣ ጣሊያንና አረብ የውጊያ መንፈሳቸው ምን ይመስላል? “ለአበሻ፣ ጦርነት ውጤቱ ምንም ዋጋ ያስከፍል ወደፊት መግፋት ነው፡፡ (ግፋ በለው እንደማለት) ለጣሊያኖች፤ አዛዥህ እንዳለህ ተዋጋ ነው፡፡ ጠላት ግንባር ለግንባር ቢፋጠጥህም ካልታዘዝክ አትተኩስም፡ ፡ ካልታዘዝክ ብትታረድም ፀጥ በል ነው! ለዐረቦች ወደ ጠላትህ ፈጥነህ ሩጥ፡፡ ሁኔታው የሚያዋጣ ከመሰለህ ነብስህን ለማዳን ፈርጥጥ ነው፡፡ የየተዋጊውን ባህሪ ለእኔ ብሎ መስማት የእኛ ፈንታ ነው፡፡ ጊዜው አስጊ ነው፡፡ ጎረቤቶቻችንን በቅጡ እናስተውል፡፡ ሩቅ የሚመስሉንን ዕጣ ፈንታ ስናይ፣ “ያንተ ቤት ሲንኳኳ ይሰማል እኔ ቤት!” እንበል፡፡ “ጎረቤትክን ሲያማ ለእኔ ብለህ ስማ!” ማለት የአባት ነው!!


Read 23530 times
Administrator

Latest from Administrator