ይህ ነበር ሂደቱ - የፍጥረታት ምሱ
ከአፈርም ወደ አፈር - አፈር የመልበሱ!
ዋ በዚች ፍልሰታ - በክረምቱ ሰማይ
በጊዜ የሞተ - ሞቶ በጊዜው ላይ
ለካ እጠብቅ ነበር አንድ ጀግና እስከማይ - አንድ ሰ’ማት እስካይ፡፡
እኮ ማነህ አንተ…
እንደ ልጅ ያልኖርከው - ዘለህ ያልጠገብከው
የፍቅር ቄጠማ - ያልቀነጣጠስከው
ኮበሌ ተብለህ - በወግ ያልተዳርከው…?
እኮ ማነህ አንተ…
በአረር ጫጫታ - በመድፍ ጉምጉምታ
በጥይት እሩምታ - በባሩዱ ሽታ
በዚያ ሁሉ መዓት…
ግብግብ የያዝከው - ከኪታብ ጋጋታ
ራስክን የቀበርከው - በፊደል ገበታ
ሽሪታ የወጣኸው - ዕውቀትን ሸመታ…?
እኮ ማነህ አንተ…?
ተስፋይቱን ምድር - ከሰው ሁላ ቀድመህ
ሩቅ ልምላሜን - ከሩቅ አስተውለህ
ማርና ወተቷን - በነፍስ አጣጥመህ
አንድ ስንዝር ቢጤ - ርቀት እንደቀረህ
በግሮችህ ሳትረግጣት - መንገድ የወደቅኸው
ሳትደርስ የቀረኸው - ቀድመህ የገባኸው…?
እኮ ማነህ አንተ…?
ላጠናህ ብሞክር - አንዴ እንኳን እንደ ሰው
ልክ እንደ ሰፊው ሕዝብ - ብዙ ህልም እንዳለው
እንደ ራስ ወዳዱም - ለራሱ እንደኖረው
ውልደት ሞትክን እንጂ - መኖርን ላጣኸው
ሳ’ትኖር በመሞትህ - ኑሮዬን አፈርኩት
ሞተህ በመኖርህ - ዋ ሞቴን ፈራሁት፡፡
እኮ ማነህ አንተ… ሞተሃል የሚሉኝ?
እኮ ማነኝ እኔ…የምለው ቋሚ ነኝ?
ቢሰንድቅ ዋልታችን - ቢሰየም አምባችን
ቢነገር ውላችን - ቅሪት መጠሪያችን
እኔ ነኝ የኖርኩት - አንተ ሞተህ ስትኖር
እኔ ነኝ የሞትኩት - በሞትህ ስትኖር፡፡
ጥላሁን አ. (ወለላው)
ለ - መለስ ዜናዊ አስረስ