Saturday, 01 September 2012 11:47

የእናት ሞት!

Written by  አንድነት ግርማ
Rate this item
(5 votes)

እናቴን እወዳታለሁ፡፡ ማን እናቱን የማይወድ አለ እንዳትሉኝና እንዳንጣላ፡፡ ስለሷ ሳስብ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ምቾት ይሰማኝ ነበር፤ ደስታ እና በራስ መተማመን፡፡ እሷን ሊቆጣና ሊሳደብ ይነሳ በነበረ ጊዜ ሁሉ ከአባቴ ጋር ተጣልቼያለሁ፡፡ ይህ ማለት ግን እሱን ለመቋቋም የሚያስችል አካላዊ ብቃት ነበረኝ ማለት አይደለም፡፡ የማደርገው ነገር ግልጽ ነው፡፡ ክፉኛ ሲቆጣት አሊያም ሊመታት ሲቃጣ ወደ በር እስፈነጠርና ቅልጥ ያለ የድረሱልኝ ጩኸት አሰማለሁ፡፡ የለቅሶዬን ምክንያት የተረዳው የሰፈር ሰው ተሰብስቦ አባቴ አደብ ከገዛ በኋላ እንኳ ለቅሶዬን አላባራም፡፡ አባቴን ከፀቡ ከመመለስ ይልቅ ጐረቤቶቻችን የሚያቅታቸው እኔን ለቅሶዬን እንዳቆም ማባበል ነው፡፡ እናቴ ምንም እንዳልሆነች እየነገረች እንኳን ብታግባባኝ አልመለስም፡፡

መፍትሔው በእናቴ ላይ እጅ ያለማንሳት ብቻ ነበር፡፡ አሁን አሁን ሳስበው ለቅሶዬ ከኔም ቁጥጥር ውጭ የሚሆን ይመስለኛል፡፡ ይህን ባህሪዬን የሰፈሩ ሰው ሁሉ አውቆልኝ አሁን እንኳ እናቴን እኔ ባለሁበት በድፍረት አይን የሚመለከታት የለም፡፡

“የሱስ ፍቅር አይጣል ነው” ብለው እውቅና ሰጥተውኛል፡፡ እሷን የሚመታ ሰው ዋና አላማው እኔን ደም እምባ ማስለቀስ መሆን አለበት፡፡

ለሷ ያለኝ ፍቅር ሌላም መገለጫ አለው፡፡ እሷ ስታዘኝ ደስ ይለኛል፡፡ ታዝዣት አልጠግብም፡፡ ያዘዘችኝን የምፈፀመው ደግሞ እሷ የተፋችው ሳይሆን እኔ የተፋሁት ትንሽዬ ምራቅ ሳይደርቅ ነው፡፡ እሷ ልካኝ ብርር ብዬ ስሄድ፣ ቱር ብዬ ስመለስ በአየር ላይ የምንሳፈፍ ያህል ደስታ ይሰማኛል፡፡ አንዳንዴ በሷ እና በምትፈልጋቸው ቦታዎች መሀል የተጠመደ የሸማኔ መወርወሪያ ብሆን እንኳ እርካታ የሚሰማኝ አይመስለኝም፡፡ አንዳንዴ ደግሞ የምታዘዛት ከሷ ቃል እንኳ ሳይወጣ ነው፡፡ ለምሳሌ ገበያ የምትሄድ ከሆነና እኔ ትምህርት ቤት ካለብኝ ትምህርት ቤት እንደምቀርና ዘንቢል እንደምይዝላት እነግራታለሁ፡፡ በዚህ የማትስማማ ከሆነ ትምህርት ቤት እንደሚሄድ ከቤት እወጣና መንገድ ላይ እጠብቃታለሁ፡፡ በዚህ የማትስማማ ከሆነ ትምህርት ቤት እንደሚሄድ ከቤት እወጣና መንገድ ላይ እጠብቃታለሁ፡፡ ከዛም ዘንቢሉን ይዛ ጐተት ጐተት ስትል ከኋላዋ እመጣና ዘንቢሉን እወስድባታለሁ፡፡ ይህንን ካደረግኩ በኋላ ግን መንገድ ላይ ክርክር የለም፡፡ ደብተሬን ዘንቢል ውስጥ ከትቼ በሰላም እንሄዳለን፡፡ እሷ ለዚህ አይነት ነገር አልተዘጋጀችም፡፡ የታማሚ ድምፁዋን አሰምታ ስልኩን ዘጋችው፡፡ ያኔ እኔን ስትወልድ ያሰማችው የምጥ ድምጽ ዛሬ ሙታንን በመቀላቀያ ጣር ይተካ? ምን አለ እኔና እሷ ሞት በሌለበት ለዘለአለም እናትና ልጅ ብንሆን? ስለእሷ ሳስብ እንደገና አምጣ ብትወልደኝ ወይ አምጬ ብወልዳት ደስ ባለኝ፡፡ ማህፀኗ እንዴት ይሞቅ ይሆን? ሙሉ ለሙሉ በሷ ሥር እርፍ ማለት እንዴት የሚያጓጓ ነገር ነው? ከሆዷ ውጭ ሆኜ እንዲህ የሞቀችኝ…

*** ***

ከልጅነቴ ሞትን የማውቀው ሠፈራችን ድንኳን እያስተከለ ኳስ እንዳናባርር ሲከለክለን፤ ኳስ እንዳንጫወት ሲያግደን ነው፡፡ አሁን ደግሞ በህይወት መንገድ ላይ ቆሞ አገኘሁት፡፡ በፍቅሬ መንገድ ላይ ተደንቅሮ ተገናኘን፡፡ ከእግሬ ስር የእናቴን ህይወት ሊያስተፋኝ ነው፡፡ እናቴን በምን መልኩ ማስመለጥ እችላለሁ? የሱ ሀሳብ የሷንም ጉዳይ ቢሆን በአንድ ድንኳን ለመደምደም አይደል? ከሷ ጋ እንዳልጫወት… ምን አይነት ደንቃራ ነው!

*** ***

የማደርገው አጣሁ፡፡ የተፈጥሮ ሀቅና ሚዛን መጠበቂያ ነው በሚል ሞትን ላደንቀውና ላሞጋግሰው፣ ከዚያም ልታረቀውና ስምም ልሆን ፈለግሁ፣ እንደ አማራጭ፡፡ እናም ልለው አሰብኩ፤

“ሞት የአባቴ ሀገር

ሞት የአያቴ ሀገር

ሞት የቅድመ አያቶቼ መንደር…”

ሆኖም አልተዋጠልኝም፡፡ በእናት ሀገር ላይ የወራሪን ሠንደቅ አላማ ለመስቀል እንደመገደድ ሆነብኝ፣ ሰላቶ የሆንኩ መሰለኝ፤ ባንዳ፡፡ እናቴን አልሰጥም!

*** ***

ይህ ወደ ላይ ሲወጣና ወደ ታች ሲወርድ የሚታየው ሰው ሁሉ በተለያየ አቅጣጫ ወደ መቃብር ቦታው የሚጓዝ ይሆን? በእርግጥ መቃብሩ ጋ ከመድረሱ በፊት ትንሽ ሊያወራ፣ ትንሽ ሊጫወት፣ ትንሽ ሊቆይ ይችላል፡፡ ግን በቶሎ ይደርሳል - ወደ መቃብሩ፡፡ ከእስር ቤት ተራ

“የምን ሞት አመጣህብኝ?” በእጇ የያዘችውን እቃ ለቀቀች፡፡

“ምን እንደማያውቅ ትሆኛለሽ፡፡ ሞት ሂድ ሂድ ባለው በማንኛውም ቀን ይመጣና አንጠልጥሎሽ ይበራል፡፡ ያኔ እኔ ልጅሽ ከሆንኩ ከሀዘን ክርን ሥር መዋሌ አይቀርም፡፡ ይደቁሰኛል፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ አልፈቅድም፡፡ ስለዚህ ከአሁኑ እርምጃ መውሰድ አለብኝ” ቅላፄዬ አማራጭ እንዳጣሁ ይናገራል….፡፡

“የምን እርምጃ?”

“ፈርሚልኝ፡፡ እናቴ እንዳልሆንሽ ማረጋገጫ ስጭኝ”

“ሂድልኝ ወዲያ! እናት ያሳጣህ፡፡” በጥፊ ልታጮለኝ ተጠጋችኝ፡፡

ከኩሽና በርሬ ወጣሁ፡፡ ድምፄ ግን ከራቅኩኝ በኋላ እንኳ የሚሰማት ይመስለኛል፡፡

“አሜን እናት ያሳጠኝ፡፡ አሜን እናት የለኝም፡፡ እናት የለኝም፤ ሞትን አልፈራም፡፡ ሞትን አልፈራም…”

 

 

 

 

 

Read 5181 times Last modified on Saturday, 01 September 2012 11:50