Sunday, 27 June 2021 18:54

ማራኪ አንቀፅ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

እንደ አውሮፓያኑ ዘመን ቆጠራ በ2017 ዓ.ም በኮሪያ ለሁለት ሳምንታት የሚካሄድና የበርካታ አገራት ዜጎች የሚታደሙበትን ትልቅ ጉባኤ የመካፈል ዕድል አገኘሁ፡፡ አገሪቱን መውደድ ከጀመርኩ ጊዜ ወዲህ በአካል የመጎብኘት ከፍተኛ ምኞት ነበረኝና ግብዣው በጣም አስፈነጠዘኝ፡፡
ከአገራችን ከመነሳታችን በፊት በዚያ ስለሚኖረን ቆይታ ማብራሪያ ተሰጠን፡፡ የመጀመሪያዎቹ አራት ቀናት ጉባኤ በሶኡል ከተማ የሚካሄድ በመሆኑ፣ እኛ የመርሐ ግብሩ ታዳሚዎች ፍቃደኛ በሆኑ ኮሪያውያን መኖሪያ ቤት እንደምናርፍ ተነገረን፤ ደስታዬ ወደር አጥቶ ነበር! በድራማ ሳየው በኖርኩት የኮሪያውያን ቤተሰብ ውስጥ ተቀላቅዬ አኗኗራቸው ምን እንደሚመስል ለማየት መቻሌን እንደ ታላቅ ዕድል ነበር የቆጠርኩት፡፡ ቀኑ ደረሰና ወደ ኮሪያ አቀናን፡፡ ከአውሮፕላኑ ወርደን ከአዲስ አበባ አብረውኝ ከሄዱ ሰዎች ጋር በመሆን ሰፊውን አየር ማረፊያ አቋርጠን፣ ወደ ሚጠብቁን ሰዎች አመራን፡፡ በውብ አበቦች የታጀበ፣ በጣም ማራኪና ደማቅ አቀባበል ተደረገልን፡፡ ለእያንዳንዳችን በተዘጋጀልን ዘመናዊ መኪና ወደ ተመደቡልን ቤተሰቦች ሊወስዱን፣ በተቀናጀ ሁኔታ ይዘውን ከአየር ማረፊያው ወጡ፡፡
ለመግለጽ የሚከብድ ውበት እያየሁ መደመም የጀመርኩት ወደ ከተማው ከመግባታችን ነበር፡፡
የመንገዶቹ ዳርቻዎች ፍጹም ማራኪና ታይቶ በማይጠገብ ሁኔታ የተሰሩ ናቸው፣ ህንፃዎቹ እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ተባብለው እይታውን አይረብሹም፣ ቀለማቸው ተዋህዶ የጋራ ውበት ይፈጥራሉ፣ በመኪና መንገድና በህንፃዎች መሃል በሚገኙ ክፍት ስፍራዎች ላይ ሌላ ህንፃ ለመገንባት አልተሽቀዳደሙም፤ ይልቅ የሚያምር የሳር ንጣፍና ውብ አበቦች መስኮች ይታያሉ፣ ሁሉም ነገር የዓይን ምግብ ሆኖ ስለተሰራ ንጽህናውንም ጥራቱንም በማየት መረዳት ይቻላል፡፡
በመኪናው መስታወት ግራ ቀኙን እያየሁ ወደ ማረፊዬ ቤት ደረስኩና መኪናው ቆመ፡፡
እኔ የማርፍባቸው ቤተሰቦች የሚኖሩበትን አፓርትመንት ዘመናዊነት እያደነቅሁኝ የሚመሩኝን ተከትዬ ወደ አሳንሰሩ (ሊፍቱ) ገባሁ፡፡ አስተናጋጅ ቤተሰቦቼ ሞቅ ያለ ሰላምታ ከትህትና ጋር ሲያቀርቡልኝ፣ እኔም የማውቃትን የኮሪያኛ ሰላምታ ሞከርኩ። በደንብ የምችል መስሏቸው ሲደሰቱ፣ ከሰላምታ የዘለለ የቋንቋቸው ዕውቀት እንደሌለኝ ነገርኳቸው፡፡ በመኪና ያደረሱኝ ሰዎች በማለዳ መጥተው ወደ ዝግጅቱ እንደሚወስዱኝ ነግረውኝ ተሰናበቱኝና የገባሁበትን ቤት መቃኘት ጀመርኩ፡፡ በድራማዎቻቸው ላይ እመለከታቸው የነበሩ ቤቶች ግነት እንዳልነበራቸው አረጋገጥኩ፡፡ ጽዳትና ዘመናዊነታቸው ልክ በቲቪ እንዳየሁት ነበር።
ባልና ሚስቱ ከአንድ ወንድና ከአንዲት ሴት ልጆቻቸው ጋር ይኖራሉ፡፡ እንደ ብዙ ኮሪያዊያን ሁሉ ሚስቶቹ እንግሊዝኛ አይናገሩም፤ ወንዱ ልጃቸው ግን በጣም ተጣጥሮ ለመናገር የሚሞክረውን እንግሊዘኛ ከአፉ ለማውጣት የሚያየውን ስቃይና የፊት መጨማደድ ለተመለከተው፤ ቃላትን እየተናገራቸው ሳይሆን አምጦ እየወለዳቸው ስለሚያስመስል ይፈጥራል፡፡
የመኝታ ክፍሌን ሲሳዩኝ ባልና ሚስቱ የራሳቸውን ክፍል እንደለቀቁልኝ ተረዳሁ። ለእንግዳ መኝታ ክፍልን ለማስተናገድ በአገሬ ዱሮ እየተባለ የሚነገረን መሆኑን አሰብኩ፡፡ አሳማኝ በመሆኑም ባልሆኑም በርካታ ምክንያቶች፣ ዛሬ አገሬ ላይ የእንግዳ አቀባበል ሁኔታ ተቀይሯል፡፡
በአስተርጓሚው ልጃቸው አግባቢነት ታግዤ፣ ሻንጣዬን ይዤ ወደ ውስጥ ዘለቅሁና ጥቂት እንደቆየሁ በሩ ተንኳኳ፤ የቤቱ ባ፣ቤት ነበረች፡፡ ሰውነቴን መታጠብ እፈልግ እንደሆነ በምልክት ስትጠይቀኝ፣ እኔም መፈለጌን በምልክት ነገርኳት፤ አስከትለኝ የመታጠቢያ ቤቱን በር ከፈተችው፡፡ በዚህ ጊዜ እንግሊዘኛ የሚሞክረው ልጅ ወደ ውጪ ወጥቶ ስለነበረ ከከባድ የመግባባት ችግር ጋር ተጋፈጥኩ፡፡
ግድግዳው ላይ የተለጠፈውን ሳጥን ከፈተችና በክብ በክብ ተጠቅልለው በስርዓት የተደረደሩ ፎጣዎችን እያሳየችኝ፣ በቋንቋዋ ማውራት ጀመረች፡፡ ለማለት የፈለገችው እንዳልገባኝ በምልክት ነገርኳት፡፡ እጇን ወደ ፎጣዎቹ ሰደደችና ከተደረደሩት ፎጣዎች አንድ አውጥታ መሬት ላይ ጣለችው፤ አሁንም አልገባኝም፡፡ ደጋግማ በምልክት ልታሳየኝ ሞክራ ስላልገባኝ ወደ አምስት የሚደርሱ ነጫጭ ፎጣዎችን እመሬት ላይ እየጣለችና በቋንቋዋ እያወራች መሬት ላይ እንደ ቄጠማ ጎዘጎዘቻቸው፡፡ የአእምሮ ችግር ያለባትም መሰለኝ፡፡ ሙከራዋ እንዳልተሳካላት ሲገባት፣ ስልኳን አወጣችና ወደ ቤቷ ያመጡኝ ሰዎች ጋ ደውላ፣ ሳቅ የተቀላቀለበት ወሬ ካወራቻቸው በኋላ ስልኳን ሰጠችኝ፡፡ ተቀብዬ “ሃሎ” ስል ሴትየዋ ለማለት የፈለገችውን አስረዱኝ። ሰውነቴን ታጥቤ የተጠቀምኩባቸውን ፎጣዎች መሬት ላይ እንድጥላቸው እየነገረችኝ እንደነበረ አስረድተውኝ ስልኩን ተሳስቀን ዘጋንና እንደገባኝ በምልክት፣ ስነግራት መሬት ላይ የጣለቻቸውን  ነጫጭ ፎጣዎች ስብሰባ ወጣች፡፡
በተፈጠረው አጋጣሚ እየሳቅሁኝ ሰውነቴን ታጥቤ ጨረስኩና ወደ ሳሎኑ ስመለስ ጠረጴዛው በምግብ ተሞልቷል፡፡
ወንዱ ልጅ ከሄደበት ስለተመለሰ የመግባባት ችግሬ በመጠኑ ተቀርፎ ለእራት አብሬአቸው ተቀመጥኩ፡፡ ኬቢኤስ ወርልድ በድራማዎቹ ላይ በደንብ አስተዋውቆኛልና፣ አብዛኞቹ ምግቦች ለእኔ እንግዳ አልሆኑብኝም፡፡ አንዳንዶቹን ደግሞ አዲስ አበባ በሚገኝ የኮሪያ ሬስቶራንት ቀምሻቸዋለው፡፡ በልጁ አስተርጓሚነት ጥቂት እያወራን መመገብ ጀመርን፤ በጣም ጣፋጭ እራት ነበር፡፡ አመስግኜአቸው ወደ መኝታ ክፍሌ ገባሁ፡፡
አልጋው አጠገብ ካለው ወንበር ላይ ተቀምጬ ስልኬ ላይ ያለውን መጽሐፍ ቅዱስ ለማንበብ ብከፍትም ሐሳቤን ለመሰብሰብ ግን በጣም ተቸገርኩ፡፡ ከኤርፖርት ጀምሮ የነበረውን አቀባበል፣ በመንገድ ላይ ያየሁት ዘመናዊ ከተማ፣ የመኖሪያ ሕንፃዎቻቸውን… ከማሰብ መቋረጥ አልቻኩም፡፡ ምንም አንኳን አገሪቱ መሰልጠኗን ባውቅም፤ በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ወታደሮች መጥተው በጦርነት የደገፏትና ስለ ድህነቷ ጥልቀት የሰማሁላት አገር ናት ብሎ ለማመን የከበደውን አዕምሮዬን ለማሳመን ስታገል ቆየሁ፡፡ የጓጓሁላትን አገር ለማየት ዕድሉን ስለሰጠኝ በርከክ ብዬ አምላኬን አመስግኜ ተኛሁ፡፡
(ምንጭ፡- በእንግዳወርቅ ተፈራ ከተፃፈው “ኢትዮጵያዊው ፓርክ” መፅሐፍ የተቀነጨበ)

Read 2308 times