Sunday, 27 June 2021 19:47

ሸክም

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(8 votes)

(የአጭር አጭር ልብወለድ)

መዝገቡ እንቅልፍ በዐይኑ አልዞር ብሎ ጣሪያ ይቆጥራል፡፡ አሁንም አሁንም ይገላበጣል፡፡ ከራስጌው ያለውን መብራት አበራና ከጠረጴዛ ላይ ከደረደራቸው መጻሕፍት መካከል፣ አንዱን አፈፍ አደረገ፡፡መጽሐፍ የሚገልጠው በተካልቦ አይደለም። በእያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅጠል ላይ፣ እንደ ኒሻን የተደረደሩትን የቃላት መንጋ፣ በጥሞና  ይመረምራል፡፡ አርበ ጠባቧ ክፍል ጅምር ንባብ በዳበሳቸው መጻሕፍት ተሞልታለች፡፡ እንዲያም ሆና ብዙም የከፋ ገጽታ የላትም፡፡
ከእጁ የገባው ድርሳን፣ የሌሊቱን ሸክም የሚያስረሳ መስሎ ስለታየ፤ለማንበብ ተበራታ፡፡ ድርሳኗን የከተበው ጥበበኛ በጨዋታ እያዋዛ፣ ቋጥኝ ቁም ነገርን ማቀበልን ያውቅበታል፡፡ ጥቃቅን ገጠመኞችን እያስታከከ፣ ንቃትን የሚያበራ ስንቅ እንካችሁ ይላል፡፡ ሲጠበብ ድንቅፍቅፍ አያደርገውም፡፡ መስመር በመስመር የደረደራቸው ውብ ሽንጣም የምናብ ፍሬዎች፣ እየተስለመለሙ ይጠራሉ። አንዴ ማንበብ ከጀመሩ፣ ለማቆም ሐሞት ይጠይቃል፡፡
የመጽሐፉን ገጽ እንደገለጠ፣ እጅ ነስቶ የተቀበለው፣ የአንድ ሸክም አልባ ትሁት ሰው ገጠመኝ ነው፡፡
አብርሀም ሊንከን የአገሪቱ ቁንጮ በሆነ ማግሥት፣ የመክፈቻ ንግግር ለማድረግ ወደ ሰገነቱ ወጣ፤በዚህ ጊዜ አንድ ግርማ ሞገስ የራቀው አድሃሪ፣ ጉባኤውን በቃጭል ድምጹ ያውከው ጀመረ፡፡
“ስማ፣ በለስ ቀንቶህ መሪ ሆንክ ማለት፣ ድህነትህ ይፋቃል ማለት አይደለም። አባትህ ጫማ ጠጋኝ እንደነበረ፣ ሀገር ያውቃል። እንደውም፤ በዚህ ጉባኤ የታደምነው የምክር ቤት አባላት የተጫማናቸው ጫማዎች፣ በአንተ አባት እጅ የተበጃጁ ናቸው። እናም፤ትላንትህን አትርሳ” አለ እያፌዘ፡፡
አብርሀም ሊንከንም ይህንን ጎርባጭ  ፌዝ፣ በሚገርም ሁኔታ ወደ ቁምነገር እንዲህ ለወጠው፤
“ወዳጄ፤ የአባቴን ስራ ስላስታወስከኝ በእጅጉ አመሰግንሃለሁ። እርግጥ ነው፣ አባቴ ጫማ ሰፊ ነበር። ሲበዛ ፈጠራን የታደለ፣ ቢፈጥር ቢፈጥር የማያልቅበት፤ እኔ እንኳን እዚህ ደረጃ ላይ ደርሼ፣ የእርሱን አንድ እጅ ችሎታ ልተካከል አልችልም። በእውነት ዛሬ የምክር ቤቱ አባላት በሙሉ የተጫሙት ጫማ፣በአባቴ ታታሪ እጆች የተበጃጁ እንደሆኑ በመበሰሬ፣ ልዩ ስሜት ነው የተሰማኝ፤ ደስታዬን እጥፍ ድርብ ላደረገልኝ  ለዚህ ቀናኢ ወዳጄ፣ ደግሜ እጅ እነሳለሁ፤” አለ፡፡
ጠቢቡ ታሪኳን ተንተርሶ ያኖረውን ምልከታ ለመቃረም፤ መዝገቡ በመጣደፍ ስሜት ገጣዩን ገጽ ገለጠና በምናብ  ማነብነብ ጀመረ ፤   
“ሸክምህን እንደ አብርሃም ሊንከን ማቅለልም ሆነ ማክበድ የምትችለው አንተ ብቻ ነህ፡፡ በትላንት ማንነትህ የምትታሰር፣ በነገ ሕልምህ የምትታበይ ከሆነ፤ ሸክምህን ለመቋቋም ጫንቃህን ከወዲሁ ማወፈር ይጠበቅብሃል፡፡ ሰዎች ሸክምህን በጎነተሉት ቁጥር፣ ስሜትህ ይጎፈንናል፡፡ እላይህ ላይ በየአፍታው የሚቀያየር የአየር ጠባይ፣ እንደ መርግ ይጫንሃል፡፡ በሰዎች ተግሳጽ ቆፈን ውስጥ ትገባለህ፡፡ በሰዎች ጭብጨባ ወበቅ ትቸገራለህ፡፡ ምርጫው የአንተ ነው፡፡ ወደ እሳት ወይም ወደ ውሃ፡፡”
መዝገቡ  በውድቅት ቀስቅሶ ንቃት የሚያባራ ቁምነገርን ላቀበለው ጠቢብ እጅ ነሳ፡፡ ምልከታው በውስጡ ያደፈጠውን ጨለማ ሰብእናን፣ እንደ ባትሪ ወለል አድርጎ ሲያሳየው ይሰማዋል፡፡ ጣቱን ከመጽሐፉ መሀል እንደወሸቀ፣ የወየበው ግድግዳ ላይ ዓይኑን ማንከራተት ጀመረ፡፡ ጥቂት ጥሞና ውስጥ እንደገባ በሞት ታናሽ ወንድም ተቸነፈ፡፡  
በማግሥቱ
በሩ በኃይል ሲደቃ ይሰማዋል፡፡ መዝገቡ ድብልቅልቅ ባለ ስሜት እየተጨናበሰ መዝጊያውን እንደከፈተ፣ የሰማይ ስባሪ የሚያህል መለዮ ለባሽ ሰደፉን እላዩ ላይ አሳረፈበት፡፡
“አንተ ብሎ ተራማጅ፣ ቀጥል!” አለ ጉርድ በርሜል የመሰለው ሌላኛው ባለመለዮ፡፡
የሥጋ ጨርቅ አድርገው ከጭነት መኪናው ላይ አሰጡት፡፡
መለዮ ለበሾቹ እያዳፉ ከአስፈሪው ወህኒ ቤት ለምን እንደጣሉት ቢያወጣ ቢያወርድ፣ ወደ አእምሮው ሊመጣለት አልቻለም፡፡ ጊዜው "የአይንህ ቀለም አላማረኝም" ተብሎ የጥይት ራት የሚኮንበት ዘመን ስለሆነ፤ በእርሱ ላይ የደረሰው አልደነቀውም፡፡
በወህኒ ቤቷ የታሸገው እስረኛ ለዐይን ያስፈራል፡፡ የሚያቃስት ድምጽ እዚህም እዚያም ይሰማል፡፡ የወህኒ ቤቷ ብቸኛ መጽናኛ  የኳሏት ጥቅሶች ናቸው፡፡ “አለም ሰፊ እስር ቤት ናት፤”   “እንኳን ከእስር ወደ እስር በደህና መጣችሁ፡፡” ጥቅሶቹ በቁጥር አይገፉም፡፡
 ከጥቅሶቹ መሀል መዝገቡን የሳበው፣ “ሸክምህ እንዲቀልህ ከፈለግህ፤ሞትን እንደ ሶቅራጠስ ቅደመው” የሚለው ነው::
ከውድቅት ጀምሮ እንደ ጥላ እየተከተለው ያለው ሸክም፣ ለራሱ ገርሞታል፡፡ እግር የጣለው አውጠንጣኝ ወህኒ ቤቷን እንደተወዳጃት ገመተ፡፡ አስፈሪዋን ወህኒ ቤት በዐይኑ ከእግር እስከ ራሷ ዳበሳት፡፡ አንድ ሪዛም አዛውንት ከጥቅሱ ጋር በአይን ይነጋገራሉ፡፡ የጥቅሱ ቅኔ በብቸኝነት የገባቸው ይመስላሉ፡፡ እንደ መቃብር በሚደብት ፅልመት ውስጥ ፊታቸው እንደ ፀሐይ ያበራል፡፡ የፊታቸው ጸዳል ሲጋባበት ይሰማዋል፤ በአዛውንቱ ሰበብ እርሱም በተራው ሸክሙን ለመመርመር ተነሳሳ፡፡
“ገላዬን እንደ አውሬ ትቦጫጭቁት ይሆናል፤ነፍሴ ግን ከእናንተ አይን የራቀ ነው፡፡ እኔም እንደ ፈላስፋው ከዚህ ግኡዝ በድኔ ጋር ሰማኒያዬን ቀድጃለሁ፤”  እንዳለ እንደ  መርግ የተጫነው  ሸክም ከላዩ ላይ ሲራገፍ  ተሰማው፡፡

Read 1875 times