Wednesday, 07 July 2021 19:09

ያላሻገረን ዲሞክራሲ ደራሲ፡- ምንተስኖት ጢቆ ነዲ

Written by 
Rate this item
(0 votes)


            መስፈንጠሪያ
ሐገራችን ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ታሪክ ባለቤት ብትሆንም የእድሜዋን ያህል ያላደገች፤ በስልጣኔ ወደ ኋላ የቀረች፤ ዲሞክራሲ የማይነካካት፤ ለውጥ የምትፈራ፤ ህዝቧ  በድህነት በረሃብ በችጋርና ቸነፈር የሚሰቃይባት፣ መሪ የማይወጣላት  በእልፍ አዕላፍ ችግር የተተበተበች ኋላ ቀር ሐገር ነች፡፡ የዲሞክራሲ ነገር ስሙ አይነሳ። ሕዝቡም መሪዎቹም የሚፈሩት ነገር ቢኖር ዲሞክራሲን ነው፡፡ አጠቃቀሙን አንችልበትም፡፡ አያያዙ አልሆነልንም፡፡ ቃሉ ያስፈራናል፡፡
የዚህ መፅሐፍ ዋና አላማ የሶስት ሺህ ዘመን ታሪክ አለን ብላ የምትፎክር ሐገር ለምን ዲሞክራሲያዊ የሆነ ስርዓት መገንባት ተሳናት የሚለውን ጥያቄ መፈተሽ ነው። ሐገሪቱ በጣም ብዙ ጊዜ ዲሞክራሲን አርግዛ ጽንሱ እየጨነገፈ እዚህ ደርሳለች። አንዳንዴ ደግሞ በአዋላጆቹ አላዋቂነት፣ ችኮላ፣ ትምክህት፣ ጥበት፣ እኔ ብቻ አዋቂ ነኝ ባይነት… የተገኘው የታሪክ አጋጣሚና የዲሞክራሲ ጭላንጭል ወዲያው ታይቶ ወዲያው ይጨልማል፡፡ ሕዝቡም ሌላ ለውጥን ይናፍቃል፤ ምክንያቱም ጨቋኝን እንጂ ጭቆናን አይታገልም፡፡ ለመሆኑ ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ማን አከሸፈው? ማን ቀኝ ኋላ ዙር አለው?
ቀኝ ኋላ ዙር!! ወታደራዊ ትዕዛዝ ነው፤፤ ጉዞን የሚገታ ትዕዛዝ፡፡ ወደ ኋላ መመለስ ነው- ወደ መነሻህ፡፡ ብዙም ሳትጓዝ ባለህበት ተመላለስ ነው፡፡ ኢትዮጵያም በረዥም ታሪኳ ብዙ ቀኝ ኋላ ዙር ገጥሟታል፡፡ ባለህበት እርገጥን ተለማምደነዋል፡፡ አንድ እርምጃ ወደ ፊት፣ አራት ወደ ኋላ ስንጓዝ ካለንበት ፈቅ ሳንል እዛው ስንዳክር ቆመን ተርተናል፡፡ እንደ ሐገርም፤ እንደ ሕዝብም የኋሊት ጉዞው ተጠቂዎች ነን፡፡ ወደ ደፊት መራመድ መሻሻል፣ መሰልጠንና መዘመን አቅቶን ከእነ ችግሮቻችን 21ኛውን ክፍለ ዘመን አገባደድን፡፡
***
የግራ - ዘመሞች ፍትጊያ-ፓርቲ
ወይም ሞት!!!
ከግራ ዘመሞቹም ይሁን ከደርግ ቀድሞ ቀድሞ ማን የመጀመሪያውን ጥይት  ተኰሰ የሚለውን መመለስ በጣም ያዳግታል፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ፓርቲዎችም ጣታቸውን ሌሎች  ላይ ከመቀሰርና ከመጠቆም  አልፈው እውነቱን አምነው ለመቀበልና ሃላፊነት ለመውሰድ አለመፈለጋቸው ነው። ሁሉም ክህደት  ዓለም ውስጥ ናቸው፡፡ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፣ ይህን ጣት የመጠቋቆም ፖለቲካ፤ “የቡዳ ፖለቲካ” ሲሉ ይጠሩታል፡፡
ጋዜጣ ቢያሳትሙ፣ መጽሐፍ ቢጽፉ፣ መጽሔት ቢያሰራጩ፣ ቃለ መጠይቅ ቢያካሂዱ፣ ምን አለፋችሁ፤ ምንም ቢያደርጉ አላማቸው አንድና  አንድ ነው፤ ከደሙ ነጻ መሆናቸውን ማሳመን- ከደሙ ነጻ ነኝ ለማለት፡፡ እነሱ ይሄንን ለማድረግ ብዙ ቢጥሩም ቅሉ፣ እኛ ግን ራሳቸው ከጻፉት  ተነስተን የሚከተለውን ማለት የሚቻለን ይመስለኛል፡፡
ከመነሻው ኢሕአፓ በትጥቅ ትግልና በከተማ አብዮት ልቡ የተሰለበ  ፓርቲ ነበር። መኢሶን ደግሞ የዚህን ተቃራኒ ሐሳብ ያራምዳል፡፡ ደርግ ወታደርና ነገሮችን በአፈ-ሙዝ ኃይል የመፍታት ልምድ ያካበተ፣ የታጠቀና የተደራጀ ኃይል ነበር፡፡ የኃይል አሰላለፋቸው ግራ ዘመሞቹ የነበራቸው ነገር  የሕዝብ ድጋፍ ፤ የአባላት ቆራጥነትና የበላይ አካላት ወይም የአመራሩ አይጠየቄና አይደፈሬ ውሳኔ ሰጪነት ነበር፡፡ ከዚህም ከዚያም ከለቃቀሙት ቀላል የጦር መሳሪያ ላይ ያላቸውን የተማረ ወጣት ኃይል ቢጨምሩበትም፣ ደርግ ከነበረው ኃይል ጋር መወዳደር የሚችሉ አይነቶች አልነበሩም። እነሱ በትምህርት ደርግ ደግሞ በመሳሪያ ይበላለጣሉ፡፡
ጠብ አጫሪው ማን ነበር?
ይህ ጥያቄ በቡዳ ፖለቲካ ውስጥ ባሳለፈችና እያለፈች ባለች ሐገር ውስጥ እንዲህ በቀላሉ መልስ አያገኝም፡፡ ለመመለስ መሞከሩ ግን ሀጥያት የለውምና ትንሽ አንሞክር፡፡ ኢሕአፓ የከተማ ታጣቂ ክንፍ ያዘጋጀው ገና ደርግ ወደ ስልጣን ከመምጣቱ ቀደም ብሎ ነበር- በ1966 ዓ.ም፡፡
“እነዚህ ታጣቂ አሃዶች ላለፉት ሁለት ዓመታት የረባ እንቅስቃሴ ሳያደርጉ ቆዩ” ይለናል ክፍሉ ታደሰ፡፡ ቀጠል አድርጎም “እስከ 1968 ዓ.ም መጨረሻ ወራት ድረስ የነዚህ ታጣቂ ክንፍ አሃዶች ራሳቸውን ሲያሰለጥኑና የወደፊት ኢላማዎችን ሲጠኑ ቆተዋል፡፡” በማለት ይነግረናል፡፡ ክፍሉ ወደፊት ኢላማዎች ሲለን ምን ማለቱ ነው? ወደፊት የሚገደሉትን ለማለት ይሆን? ወደ ፊት እርምጃ የሚወሰድባቸውን ሰለባዎች ለማለት ነው? የቀድሞው የኢህአፓ በኋላ የማሌሪድ መስራች ተስፋዬ መኮንን ደግሞ “ከፋሺዝም (ከደርግ) መጥፋት በፊት  መቅድም ያለባቸው “ባንዶች” ናቸው ተብሎ ይመስላል፣ የስም ሊስታቸው ወጥቶ በተገኙበት እንዲገደሉ ታዘዘ” ይለናል፡፡
እነዚህን ገዳይ አሃዶች ከማዘጋጀት ውጪ ኢህአፓ ራሱን ማጠናከሪያ ይሆኑኛል ያላቸውን ዘረፋዎች በተለያዩ ባንኮችና የመንግስት ተቋማት ላይ አካሂዷል፡፡ ለአብነትም ያህል ክፍሉ “መንጠቅ” ሲል የሚጠራው የሰንዳፋው ፖሊስ ማሰልጠኛ ተቋም የተሳካ የጥይትና የመሳሪያ ዝርፊያ ነው፡፡ ታክሎ ተሾመ በበኩላቸው፤ “በ1969 ዓ.ም የሰንዳፋ ፖሊስ ማሰልጠኛ የመሳሪያ ግምጃ ቤት ዘረፋ ተካሄደ” በማለት ያለ ምንም የዳቦ ስም በግልፅ ያስቀምጡታል። ሌላው በመስከረም ወር 1969 ዓ.ም የተከናወነውና ከ1.2ሚ ብር በላይ የሚሆን ገንዘብ የተዘረፈበት “ኦፕሬሽን” ነው። እርግጥ ክፍሉ ታደሰ የባንክ ዘረፋውን “የባንክ ገንዘብ ምርኮ” ሲል ነው የሚጠራው።  “ዘረፍን” የሚለውን ቃል ላለመጠቀም ይመስላል፡፡ “ከ1.2 ሚ. ብር በላይ የሚሆን ገንዘብ አገኘን” ይለናል፡፡ ወድቆ ያገኙት ነው የሚያስመስለው፡፡
ከስንት ዓመት በኋላም የቃላት ጨዋታውን አረሳውም፡፡ በ”እናሸንፋለን” እና “እናቸንፋለን”፣ “በወዛደር” እና “ላብ አደር” … ተመሳሳይ ነገር የሚገልጹ ቃላት መቆራቆስ የለመደ ልብ፣ በቀላሉ አመሉን ይተዋል ተብሎ ስለማይታሰብ፣ ይህ የሚገርም ነገር ላይሆን ይችላል፡፡
ሌላው የታሪክ ሀቅ፣ ኢህአፓ የመኢሶንና የደርግ ከፍተኛ አመራሮችን ለመግደል ሲያሴር የነበረው፤ ደርግ ከ60ዎቹ ውጭ በአብዮቱ ወገን በሆኑት ቡድኖች አባላት ላይም ሆነ አመራሮች ላይ ምንም አይነት እርምጃ ባልወሰደበት ጊዜ እንደነበር ነው፡፡ ይህንን ብዙ ሰበቦች ቢደረድሩም ሊክዱት የማይችሉት ሀቅ ነው፡፡ እንዲህ ያደረኩት እንዲህ ሊደረግ መሆኑን መረጃ ስለደረሰኝ ወይም ስለሆነ ነው ብሎ መከራከር ውሃ አያነሳም፡፡
ኢህአፓ አንድ ብሎ የታጣቂ ኃይሉን ብትር ያሳረፈው፣ ስኳዱን መንግስቱ ኃይለማርያምን ለመግደል መጠቀምን በተቃወመውና ጣጣው የበዛ መሆኑን አጥብቆ በተከራከረው በራሱ ሰው ላይ ነበር-ጌታቸው ማሩ፡፡ በእርጥ እሱ የመጀመሪያው የኢህአፓ መስዋዕት ነበር-ቢያንስ እስካሁን በተነገረን መሰረት፡፡
(ምንጭ፡- “ያላሻገረን ዲሞክራሲ” ከተሰኘው ከምንተስኖት ጢቆ ነዲ መፅሐፍ የተቀነጨበ)

Read 1877 times