Sunday, 11 July 2021 17:30

ለእንግሊዝና ጣሊያን እስከ 90ሺ ተመልካች በዌምብሌይ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

 በ16ኛው የአውሮፓ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ ላይ ጣሊያንና እንግሊዝ  ተገናኝተዋል፡፡ የዋንጫ ጨዋታው የሚካሄድበት የዌምብሌይ ስታድዬም 60ሺ ተመልካቾችን እንዲይዝ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም በሙሉ አቅሙ 90ሺ ተመልካቾችን ያስተናግዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በአውሮፓ ዋንጫ ላይ ተመልካቾች በውስን ብዛት እንዲገቡ ተፈቅዶ  ከዋንጫ ጨዋታው በፊት በተደረጉ 50 ጨዋታዎች በድምሩ 1 ሚሊዮን 32ሺ 105 ተመልካቾች ስታድዬም ገብተዋል፡፡ ይህም አንድ የአውሮፓ ዋንጫ ጨዋታን በአማካይ  ከ20,642 ተመልካቾች ስታድዬም ገብተው እንደታደሙት የሚያመለክት ሲሆን  በኮቪድ 19 ተፈጥሮ የነበረውን ስጋት ያቃለለው ይመስላል፡፡
የአውሮፓ ዋንጫው በተለይ በጥሎ ማለፍ ምዕራፍ ላይ ከፍተኛ ፉክክር ታይቶበታል። ለዋንጫ ተጠብቀው ከነበሩት ቡድኖች መካከል የዓለም ዋንጫ ሻምፒዮኗ ፈረንሳይ በስዊዘርላንድ፤ የአውሮፓ ሻምፒየንነት ክብሯን ለማስጠበቅ የገባችው ፖርቱጋል በቤልጅዬም፤ ለዓለም ዋንጫ ፍፃሜ የደረሰችው ክሮሽያ በስፔን ተሰናብተዋል። ለዋንጫ ጨዋታው ለመድረስ በግማሽ ፍጻሜው ጣሊያን ስፔንን በመለያ ምቶች 4ለ2 ስትረታ፤ እንግሊዝ  ዴንማርክን ከተጨማሪ ሰዓት በኋላ 2ለ1 አሸንፋለች፡፡
እንግሊዝ በአውሮፓ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ላይ የምትቀርበው በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ሲሆን ብሄራዊ ቡድኑ በ1966 እኤአ ላይ በዌምብሊ ስታድዬም የዓለም ዋንጫን ካሸነፈ በኋላ ለዋንጫ ተጫውቶ አያውቅም፡፡ ባለፉት 55 ዓመታት በአምስት ትልልቅ የእግር ኳስ ውድድሮች ከግማሽ ፍፃሜ የተሰናበተ ሲሆን እነሱም በአውሮፓ ዋንጫ ላይ በ1968 እና በ1990 እኤአ፤ በዓለም ዋንጫ በ1990 እና በ2018 እንዲሁም በአውሮፓ አገራት ዋንጫ ላይ በ2019 ናቸው፡፡  ጣሊያን በአውሮፓ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ ላይ የምትሰለፈው ለአራተኛ ጊዜ ሲሆን  ብቸኛውን የዋንጫ ድል ታሪክ ያስመዘገበችው በ1968 እኤአ ላይ ነበር፡፡ ከአራት የዓለም ዋንጫ ድሎቿ ሁለቱን በ1994 እና በ2006 እኤአ ላይ ማስመዝገቧም  የሚታወቅ ሲሆን ፤ በ2000 እና በ2012 እኤአ ላይ በተካሄዱት የአውሮፓ ዋንጫዎች ለፍፃሜ ብትቀርብም ዋንጫውን ለማሸነፍ አልቻለችም፡፡  
በ16ኛው የአውሮፓ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ ላይ እንግሊዝና ጣሊያን የሚገናኙት ለ28ኛ ጊዜ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ሁለቱ ቡድኖች በተለያዩ ውድድሮች 27 ግጥሚያዎችን አድርገው ጣሊያን 11 ጊዜ እንግሊዝ 8 ጊዜ ያሸነፉ ሲሆን 8 ጊዜ አቻ ተለያይተዋል፡፡
በትራንስፈርማርከት ድረገፅ ላይ እንደሰፈረው የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን የተጨዋቾች ስብስብ 1.26 ቢሊዮን ዩሮ ዋጋ ሲኖረው የጣሊያን ስብስብ ደግሞ በ751 ሚሊዮን ዩሮ ይተመናል፡፡ በዝውውር ገበያው ከፍተኛው ዋጋ ያለው የጣሊያን ተጨዋች ኒኮሎ ባሬላ  በ65 ሚሊዮን ዩሮ  ሲሆን የእንግሊዝ ውዱ ተጨዋች ደግሞ በ120 ሚሊዮን ዩሮ ሃሪ ኬን ነው፡፡
ከጣሊያን ብሄራዊ ቡድን ጋር በስፖርት ትጥቅ አቅራቢነት አጋር ሆኖ የሚሰራው ከ2015 እኤአ ጀምሮ በዓመት 20 ሚሊዮን ዩሮ የሚከፍለው ፑማ ሲሆን፤ የእንግሊዝ የትጥቅ አጋር ደግሞ ከ2016 እስከ 2023 በያዘው ኮንትራት ከ465.81 ሚሊዮን ዩሮ በላይ የሚከፍለው ናይኪ ነው፡፡
ለአውሮፓ ሻምፒዮን የምትሸለመው  ዋንጫ  በእግር ኳስ ከዓለም ዋንጫ ቀጥሎ ልዩ ክብር የሚሰጣት ናት፡፡ ዋንጫዋን በኦርጅናል ዲዛይን ለመጀመርያ ጊዜ  የሰራት በ1960 እኤአ ላይ አርተውስ በርትራንድ የተባለ ቀራፂ ነው፡፡ መታሰቢያነቷም  ለቀድሞ የፈረንሳይ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንትና የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር የመጀመርያ ዋና ፀሃፊ ሄነሪ ዴላኑይ  ነው። ዋንጫዋ በመጀመርያ ስትሰራ በአንፀባራቂ ብር ማዕድን  2 ኪሎግራም ክብደትና 18 ሴሚ ርዝማኔ ነበራት፡፡ “Coupe d’Europe”, “Coupe Henri Delaunay”, and “Championnat d’Europe” የሚሉ ፅሁፎች ተቀርፀውባታል፡፡ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር አፕስሬይ ለንደን የተባለ ድርጅት በ2008 እኤአ ላይ ግን በድጋሚ እንድትስራ አድርጓል፡፡ ርዝማኔዋ ከ18 ሴሜ ወደ 60 ሴሜ ክብደቷም ከ2  ኪግ ወደ 8 ኪግ እንዲጨምር ሆኗል፡፡
በፍፃሜ ጨዋታ ላይ ከዋንጫው ሽልማት ባሻገር ለሻምፒዮኑ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች የወርቅ እንዲሁም በሁለተኛ ደረጃ ለጨረሱት የብር ሜዳልያዎች ይሰጣሉ፡፡ በ2008 እና በ2012 እኤአ ላይ በተደረጉት የአውሮፓ ዋንጫዎች ላይ በግማሽ ፍፃሜ ለተሸነፉ ቡድኖች የነሐስ ሜዳልያዎች የተሸለሙ ሲሆን ከዚያ በኋላ  ግን እንዲቀር ተደርጓል። የአውሮፓ ዋንጫ በስፖርቱ ዓለም ውድ በሚባሉ ሽልማቶችና ዋንጫዎች የደረጃ ዝርዝር ውስጥ የምትጠቀስ ሰሆን  በ15 ሺ ዶላር 9ኛ ደረጃ ተሰጥቷታል፡፡ በእግር ኳሱ ዓለም ከሚሰጡ ዋንጫዎች እና ሽልማቶች መካከል የዓለም ዋንጫ 20 ሚሊዮን ዶላር፤ የእንግሊዝ ኤፍ ኤካፕ 1.18 ሚሊዮን ዶላር፤ የወርቅ ኳስ (ባለንዶር)  600 ሺ ዶላር፤ የአፍሪካ ዋንጫ 150 ሺ ዶላር፤ የጣሊያን ሴሪኤ ስኩዴቶ 66ሺ ዶላር ዋጋ አላቸው፡፡
በአውሮፓ ዋንጫ ላይ ስፔን (1964, 2008, 2012) እና ጀርመን (1972, 1980, 1996) እኩል 3 ጊዜ በማሸነፍ ከፍተኛ ውጤት ሲኖራቸው  ፈረንሳይ በ1984 እና በ2000 እኤአ ሁለቴ አሸንፋለች፡፡ በ1960 እኤአ ሶቪዬት፤ በ1968 እኤአ ጣሊያን፤ በ1976 እኤአ ቼኮዝላቫኪያ፤ በ1988 እኤአ ሆላንድ፤ በ1992 እኤአ፤ በ2004 እኤአ ግሪክ፤ እንዲሁም በ2016 እኤአ ፖርቱጋል የአውሮፓ ሻምፒዮኖች ሆነዋል፡፡

Read 1095 times