Sunday, 11 July 2021 18:34

የግጥም ጥግ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ፈቅደን ሲመሩን፣ ችቦ ተቀባይ
ለሚነዱን ግን፣ አሻፈረን ባይ
ካልነኩን በቀር፣ ቀድመን ማንዘምት
ከጋሻ በፊት፣ ጦር የማንሸምት
ኢትዮጵያዊ ነን!
ህብር ያስጌጠው፣ ህይወት ለማብቀል
ዘር ሳናጣራ፣ የምንዳቀል
ለነዱን ሰይጣን፣ ለመሩን ሰናይ
ጌታን ከገባር ፣ ለይተን ምናይ፤
ኢትዮጵያዊ ነን!
ብዙ ህልሞችን፣ ወዳንድ ዐላማ
የሰበሰበ ገርቶ፣ ያስማማ
በደምና ላብ፤ ያቆምነው ካስማ
አገዳ አይደለም፣ የሚቀነጠስ
የዝምድናችን መተሳሰርያ
ሺ ጊዜ ቢከር፣ የማይበጠስ
ኢትዮጵያዊ ነን!
ምን ሆድ ቢብሰን፣ ምን ብንቸገር
እድር አይፈርስም፣ እንኩዋንስ አገር
ብለን በትግስት፣ የምንሻገር
ሲገፈትረን፣ ግፈኛና አጥቂ
ቁልቁል ሲሰደን፣ ሽቅብ መጣቂ
ለውርደት ሲያጩን፣ የምንጀነን
ኢትዮጵያዊ ነን!
    በዕውቀቱ ሥዩም





Read 2157 times