Saturday, 17 July 2021 14:44

‹‹ድጋፋችንን የቀጠልነው ባለን የቆየ ትስስር የኢትዮጵያን ስፖርት ለማሳደግ ነው›› ሄኒከን ኢትዮጵያ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)


           የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽንና ሀይኒከን ኢትዮጵያ ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት አብረው ለመስራት ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን በዋልያ ቢራ ምርት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በዓመት 15.5 ሚሊዮን ብር በአራት ዓመት ውስጥ ደግሞ 62 ሚሊዮን ብር እንደሚከፈለው ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ በፊርማው ስነስርዓት ላይ በሰጡት ገለፃ ሀይኒከን ኢትዮጵያ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ በመስራት መቀጠሉን አድንቀው ለብሄራዊ ቡድኑ ያደረገው የስፖንሰርሺፕ ድጋፍ ከበፊቱ ውል በ6 ሚሊዮን ብር ጭማሪ አሳይቷል ብለዋል፡፡ ሀይኒከን ኢትዮጵያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስፖንሰር በመሆኑ እጅግ ደስተኛ ነው ያሉት የኩባንያው ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሚስተር ሁበርት ኢዜ ናቸው፡፡ ‹‹ብሄራዊ ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ በማለፉ እንኳን ደስ አላችሁ፤ እግር ኳስ ህዝቦችን ያስተሳስራል፡፡ ስለዚህም ወደፊት በጋራ እየሰራን እንቀጥላለን፤ አዳዲስ የስኬት ማማዎችንም አብረን እንወጣለን፡፡›› በማለት የተናገሩት ማኔጂንግ ዲያሬክተሩ የኢትዮጵያን እግር ኳስ ለማሳደግ የምንሰራበትን ጠንካራ ስምምነት ያደረግንበትን እድል በድጋሜ  በማግኘታችን እናመሰግናለን ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ከቡድኑ ቅፅል ስም እና ከስፖንሰሩ ስም ጋር በተገናኘ ጥያቄ ቀርቦላቸው በሰጡት ምላሽ “ካልተሳሳትኩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋልያ ቅፅል ስሙ ስለሆነ አይደለም ስፖንሰር ያደረጉን። ስፖንሰር ማድረግ ስላለባቸው እንጂ። ብሔራዊ ቡድኑ በሌላ ስምም ቢጠራ የሚያደርጉት ይመስለኛል። ፌዴሬሽናችን ጋር የስም መብት ክፍተት ነበር። ቀድሞ የስም መደራረብ እንዳይመጣ ስራ መሰራት ነበረበት። በሆነ አጋጣሚ የስም መመሳሰል መጥቷል። ይህ ደግሞ በአጋጣሚ የመጣ ነው እንጂ ታስቦበት አይደለም።” ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፉ ለዋልያ ቢራ መልካም አጋጣሚ መሆኑ ን የገለፁት ፕሬዝዳንቱ ዋልያዎቹ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ሲያልፉ  ፌዴሬሽኑ ለቡድኑ አባላት ከሰጠው 6 ሚሊዮን  ብር  1.5 ሚሊዮን ብሩን ለማበረታቻ በፍቃደኝነት የሰጠው ሄኒከን ኢትዮጵያ እንደነበር ጠቁመዋል።
ብሄራዊ ቡድኑን አስቀድመን ስፖንሰር ያደረገነው በበደሌ ቢራ ስም ነበር ያሉት የሄኒከን ኢትዮጵያ ከፍተኛ የስረ ሃላፊ ሲሆኑ በዋልያ ብራንድ ድጋፋችንን የቀጠለነው ባለን የቆየ ትስስር የኢትዮጵያን ስፖርት ለማሳደግ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ከእግር ኳሱ ባሻገር ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ጋር በ30 ሚሊዮን ብር የአራት አመታት ስፖንሰርሺፕ መፈረሙንና  ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት በጋራ ለመስራትም ስምምነት መደረጉንም ጠቁመዋል፡፡

Read 1074 times